የአሰልጣኞች አስተያየት | ባህር ዳር ከተማ 1-0 መቐለ 70 እንደርታ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 20ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከትላንት ቀጥለው ዛሬ ሲከናወኑ በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም መቐለ 70 እንድርታን ያስተናገደው ባህር ዳር ከተማ አንድ ለምንም ካሸነፈ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል። 

” ምስጋና ለተጨዋቾቼ እና ለደጋፊዎቹ፤ ተጋግዘን አሸንፈናል።” ጳውሎስ ጌታቸው – ባህር ዳር ከተማ

ስለ ጨዋታው

” ጨዋታው ከባድ ጨዋታ ነበር። በሁለቱም ቡድኖች ላይ ጫና ያሳረፈ ጨዋታ ነበር ማለት ይቻላል። በተለይ ደግሞ እኛ ላይ በጣም ከባድ ጫና የነበረ ቢሆንም አሸንፈናል። በመጀመሪያ ያሉትን ጫናዎች ተቋቁመው ይህን ውጤት ላመጡልን ተጨዋቾቼ ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለው። በመቀጠል ለዚህ ሁሉ ደጋፊ ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለው። በአጠቃላይ ከደጋፊዎቻችን ጋር ተጋግዘን ጨዋታውን አሸንፈን ወተናል።”

ስለ ጨዋታ እቅዳቸው

” በመጀመሪያ 15 እና 20 ደቂቃዎች ተጨዋቾቼ ያልኳቸውን ነገር አድርገውልኝ ነበር። በዚህም ጎል አስቆጥረን አሸናፊ ሆነናል። ግብ ሳናስቆጥር ሰዓት እየሄደ ቢሆን ኖሮ አቻ ነበር የምንወጣው። ከጨዋታው በፊት ልምምድ ሜዳ እና ክፍል ውስጥ በሰራናቸው ስራዎች መሰረት ጨዋታውን አሸንፈናል። ከእረፍት መልስ ውጤቱንም ለማስጠበቅ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ነበር ያሰብነው። በዚህም የግብ እድሎችን ብንፈጥርም አልተጠቀምንበትም። የሆነው ሆኖ በተጨዋቾቼ እና በመጣው ውጤት ደስተኛ ነኝ።”

በሁለተኛው አጋማሽ ስለመቀዛቀዛቸው

” ጨዋታው የዓመቱ ትልቁ ጨዋታ ነው ማለት ይቻላል። ሊጉም ወደ ውበቱ እንዲመጣ እና የዋንጫው ፉክክር እንዲደም ውጤት ለማስጠበቅ ሞክረናል።”

ስለ አጥቂ መስመራቸው

” በዛሬው ጨዋታ እኛ 10ለ0 ማሸነፋችን አይደለም የሚፈለገው። ዋናው የሚፈለገው ሶስት ነጥብ ነው፤ ይህንን ደግሞ አሳክተናል። ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የአጥቂ ችግር አለ፤ እናውቃለን። ነገር ግን እኛ በየደቂቃው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል እንደርሳለን። መሻሻል ያለበት ነገር ካለ እናሻሽላለን። ነገር ግን አሁን ቡድኔ ውስጥ ጥሩ ጥሩ አጥቂዎች አሉ።”

” በምንችለው አቅም ተጭነን ብንጫወትም አጋጣሚዎች ዋጋ አስከፍለውን ተሸንፈን ወጥተናል” ገብረመድህን ኃይሌ – መቐለ 70 እንደርታ

ስለ ጨዋታው እንቅስቃሴ

” አጠቃላይ የጨዋታው እንቅስቃሴ ጥሩ ነው። የምንችለውን ያህል ጫና ፈጥረን ለመጫወት ሞክረናል። ነገር ግን በእግር ኳስ አጋጣሚዎች የሚፈጥሯቸው ስህተቶች ዋጋ አስከፍለውን ተሸንፈን ወጥተናል። እኛ በመጀመሪያው አጋማሽ ብቻ ጨዋታውን ጨርሰን መውጣት እንችል ነበር። ነገር ግን ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች መጨረስ አልቻልንም።”

ስለተደረገላቸው አቀባበል እና ስለ ባህር ዳር ደጋፊዎች

” በሜዳው መጥፎ ነገር አላየሁም። ይሄ መቀጠል ያለበት ጉዳይ ነው። ነገር ግን አልፎ አልፎ አንዳንድ ጥቃቅን ነገሮች አሉ። እኛ ግን እነዛን ጥቃቅን ነገሮች እያነሳን አናካብድም። በአጠቃላይ ግን ጥሩ ወንድማዊ ፍቅርን ሊያመጣ የሚችል ድባብ ነው የነበረው። እኔ ድሮም ቢሆን አውቀዋለው፤ ባህር ዳርን ሰውን ለማስተናገድ ያለው ባህል ጥሩ ነው።”

ስለ ዳኝነቱ

” ሊዲያ ባላት አቅም ጨዋታውን መርታለች። እንደ ሰበብ እንዳይቆጠርብኝ እንጂ ያስቆጠርነው ጎል የተሻረበት መንገድ አልገባኝም። በእሷ እና በረዳቶቿ እምነት ግብ አልተቆጠረም። ነገር ግን ለእኔ ይሄ ጎል የተሻረበት መንገድ ግልፅ አይደለም። በተጨዋቾቼ እንቅስቃሴ ደስተኛ ስለነበርኩኝ ዳኝነቱ ላይ ማተኮር አልፈልግም።”

ስለ ቀጣይ የዋንጫ ጉዟቸው

” ገና ሊጉ 10 ጨዋታዎች አሉት። አስሩንም ጨዋታዎች ከሜዳችን ውጪ አንጫወትም። ስለዚህ መልሱን ከጨዋታዎቹ እናገኛለን።”


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡