ሶዶ ላይ በተደረገው የ20ኛው ሳምንት የወላይታ ድቻ እና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ በወላይታ ድቻ 2-1 አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተውናል።
“ያለንበት ደረጃ አስተማማኝ ስላልሆነ ጨዋታው ተፅዕኖ ፈጥሮብናል” አሸናፊ በቀለ ወላይታ ድቻ
ስለጨዋታው
እንደተመለከታችሁት ለመሸናነፍ የነበረው ትግል በጣም ከፍተኛ ነበር። በመቀጠል የሰራናቸው ጥፋቶች ዋጋ ቢያስከፍለንም አሸንፈን መውጣት ችለናል። ዞሮ ዞሮ እንደ ቡድን ስታየው ተስፋ ሰጪ ነገር አለው። አንዳንዴ ጉጉት ሲኖር ብዙ ነገር ያበላሽብሀል። ምክንያቱም እኛ ያለንበት ደረጃ አስተማማኝ ስላልሆነ ጨዋታው ተፅእኖ ፈጥሮብናል። ቡድኔ ተጭነው እንዲጫወቱ ነበር ሳስገድዳቸው የነበረው። ይህን ያደረኩት ተጭነን ከተጫወትን ነው ብልጫ ልንወስድ የምንችለው በሚል ነው።
በተከላካይ ስህተት የሚቆጠሩ ጎሎች መደጋገም
የድቻ የተከላካይ ክፍተት የአሁን አይደለም። ከአንደኛው ዙር እየተንከባለለ የመጣ ችግር ነው። እንደውም የደጉ ደበበ መምጣት ቡድኑን ለማረጋጋት እየሞከረ ነው። ግን የቀኝ እና የግራ ተከላካዮቻችን ላይ መረጋጋት አይታይም። ይህ ደግሞ ትልቁ የቤት ስራችን ነው።
ቡናዎች ግቦቹ አግባብ አይደሉም ስለማለታቸው
አደላ ትሉኝ ይሆናል እንጂ የመጀመሪያዋ ጎል ፀጋዬ ከግብ ጠባቂው ጋር ምንም የእጅ ንክኪ የለውም። እንደውም ግብ ጠባቂው በአንድ እጁ ማዳን የሚችለው ኳስ ነበር።
“የተሸነፍነው በሶስተኛ ወገን ነው” ገዛኸኝ ከተማ ኢትዮጵያ ቡና
ስለጨዋታው
ጨዋታው መጥፎ ነበር። ለእግር ኳሱም ጥሩ ገፅታ ይፈጥራል ብዬ አላስብም። እንዲህ አይነት ጨዋታ የሚደረግ ከሆነ እግርኳሱ ሙሉ ለሙሉ ቢቆም ነው የሚሻለው። ይህን እንደሽንፈት አልቆጥረውም፤ ምክንያቱም የተጫዋቾቼን መነሳሳት ያየሁበት ጨዋታ ነው። ያደረጉትን ነገር በጣም ነው የማደንቀው። ግን በእንደዚህ አይነት ነገር እግርኳስ የሚቀየር ከሆነ የሀገሪቷን ሊግ ያወረደዋል እንጂ የተሻለ ደረጃ አያደርሰውም። ማንኛውም ሚዲያም እንዲህ አይነት ነገር ማበረታታት የለበትም ብዬ ነው የማስበው። ከእግር ኳስ የምናተርፈው ነገር ዋጋ ስለሚያስከፍለን።
ስለ ግቦቹ እና ስለ ዳኝነቱ
በየትኛውም የህግ አተረጓጎም እንዲህ አይነት ጎሎች አይፀድቁም። በየትኛው አንግል አይቶ ግቦችን እንዳፀደቃቸው አላውቅም። የተሸነፍነው በሶስተኛ ወገን ነው።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡