ከፍተኛ ሊግ ለ | ኢኮስኮ ነጥቡን ከመሪው ጋር ሲያስተካክል ሀላባ እና ሀምበሪቾም አሸንፈዋል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 14ኛ ሳምንት የምድብ ለ አራት ጨዋታዎች እሁድ ተደርገው ኢኮስኮ ሀምበሪቾ እና ሀላባ ከተማ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል።

መድን ሜዳ ላይ ዲላ ከተማን ያስተናገደው ኢኮስኮ 1-0 በማሸነፍ ነጥቡን ከመሪው መድን ጋር እኩል አድርጓል። የጨዋታው መጀመሪያ ደቂቃ ላይ ግብ ማስቆጠር የቻሉት ኢኮስኮዎች በግማሽ ውድድር ዓመት ቡድኑን በተቀላቀለው ታምሩ ባልቻ ብቸኛ ግብ ዲላ ከተማን 1-0 ማሸነፍ ችለዋል። ውጤቱን ተከትሎም ከመድን ጋር በእኩል 31 ነጥብ ላይ መቀመጥ ችለዋል።

ዱራሜ ላይ ሀምበሪቾ ከናሽናል ሲሚንት ያደረጉት ጨዋታ በባለሜዳው 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ የተገኘው ፍፁም ቅጣት ምትን ወንድሜነህ ዘሪሁን አስቆጥሮ ሀምሪች ሦስት ነጥቦች ይዞ መውጠች ችሏል።

ቅዳሜ ኦሜድላ ሜዳ ላይ ለ7 ደቂቃዎች ብቻ ተካሄዶ በጣለው ዝናብ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የአዲስ አበባ እና የነገሌ አርሲ ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታድየም እሁድ በ4:00 ሰዓት ላይ ተካሄዶ ያለ ጎል ተጠናቋል። እምብዛም የግብ ሙከራ ባልተየበት የመጀመሪያው አጋማሽ ባለሜዳዎቹ አዲስ አበባዎች በእንቅስቃሴ ተሽሎ ሲታዩ በተከላካይ ክፍሉ ይበልጥ በቁጥር በዝተው የተጫወቱት ነገሌዎች ደግሞ በመከላከል እንቅስቃሴ ላይ አተኩረዋል። በዚህም ከቆሙ ኳሶች መነሻነት ከሚደረጉ ሙከራዎች ውጪ በክፍት ጨዋታ አስደንጋጭ ሙከራ ሳይስተናገድበት ቀርቷል።

በሁለተኛው አጋማሽ ነገሌዎች ተሻሽለው በመቅረብ የጎል እድል ለመፍጠር ሞክረዋል። በ50ኛው ደቂቃ ላይም ኤርምያስ ታደሰ መትቶ ግብ ጠባቂው ያዳነበት እና በ80ኛው ደቂቃ ላይ ከኤርሚያስ የተሻገረለትን ኳስ በተመሳሳይ ብዙዓየለየሁ ሞክሮ ግብ ጠባቂው ያዳነበት ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ።

አዲስ አበባዎች እንደ መጀመርያው አጋማሽ ሁሉ የጠራ የግብ እድል ለመፍጠር ቢቸገሩም በቃሉ ገነነ እንዲሁም ሙሀጅር መኪ ከርቀት ግብ ጠባቂውን ያልፈተኑ ሙከራዎችን አድርገዋል። የጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃ ላይ የግራ ተመላላሹ ሮቤል አስራት ያገኘውን ጥሩ የግብ አጋጣሚም ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

በጨዋታው የእንግዳው ቡድን ነገሌ አርሲ ተጫዋቾች የዳኛን ውሳኔ በተደጋጋሚ በመቃወም እንዲሁም ውሳኔን ለማሳት ሲያደረረጉ የነበረው ሙከራ ሊታረም የሚገባው ነው።

ሀላባ ላይ ሀላባ ከተማ ድሬዳዋ ፖሊስን አስተናግዶ 2-0 አሸንፏል። ካሳሁን ገረመው በ28ኛው እንዲሁም አቡሽ ደርቤ በ35ኛው ደቂቃጠየሀላባን የድል ጎልች አስቆጥረዋል።

በቅዳሜ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ መድን እና ወልቂጤ ከተማ በተጋጣሚያቸው የካ እና ሶዶ በተመሳሳይ 2-1 ተሸንፈዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡