ወላይታ ድቻ ተስፋዬ አለባቸውን አስፈርሟል

በሁለተኛው ዙር ያለበት ክፍተት ለመድፈን ተጫዋቾችን ወደ ክለቡ እያመጣ ያለው ወላይታ ድቻ ተስፋዬ አለባቸውን የግሉ አድርጓል።

አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለን ከቀጠረ በኋላ በዝውውር መስኮቱ በመሳተፍ የውጤት መሻሻል ያሳየው ወላይታ ድቻ አንጋፋውን አማካይ የአጋማሹ ስድስተኛ ፈራሚ በማድረግ የአንድ ዓመት ውል ማስፈረሙን አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል። ከሳምንት በፊት (ግንቦት 28) የዝውውሩ ከመዘጋቱ በፊት ፌድሬሽን ስሙ ገብቶ የነበረው አማካዩ በግል ጉዳዮች ምክንያት በወቅቱ መፅደቅ ያልቻለ ሲሆን አሁን ደግሞ በይፋ ዛሬ የክለቡ ተጫዋች መሆኑን አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

ትላንት ወላይታ ድቻ ኢትዮጵያ ቡናን በሜዳው 2-1 በረታበት ጨዋታ ላይ በስታዲየም ተገኝቶ የተከታተለው የቀድሞው የሰበታ ከተማ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወልዲያ አማካይ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ከወልዲያ ጋር ከተለያየ በኋላ ለሰባት ወራት ክለብ አልባ ሆኖ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን ወደ እግርኳስ የመመለስ እቅድ እንዳለዝ ከዚህ ቀደም ለሶከር ኢትዮጵያ መግለፁ ይታወሳል።

በሁለተኛው ዙር ስድስት ተጫዋቾችን ያስፈረመው ወላይታ ድቻ ኃይማኖት ወርቁ እና በረከት ወልዴ በሚገኙበት የተከላካይ አማካይ ስፍራ ላይ አማራጩን እንደሚያሰፋ ይጠበቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡