መከላከያ ከዋና አሰልጣኙ ጋር ተለያየ

ዓመቱን ወጥ ባልሆነ አቋም እየተጓዘ በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘው መከላከያ ከዋና አሰልጣኙ ጋር ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ መለያየቱ ታውቋል።

በከፍተኛ ሊግ እየተሳተፈ ከሚገኘው ሰበታ ከተማ ጋር በስምምነት ከተለያዩ በኋላ ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ ነበር አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ መከላከያን ለማሰልጠን የተረከቡት። በክለቡ የኢትዮጵያ ዋንጫ እና የኢትዮጵያ አሸናፊዎች ዋንጫን በማንሳት ዓመቱን በስኬት የጀመሩት አሰልጣኙ በአዳማ ከተማ የ5-1 ያልተጠበቀ ሽንፈት በኃላ በቡድኑ ውስጥ መረጋጋት የጠፋ ሲሆኑ በአሁኑ ወቅት በሃያ ጨዋታ አስራ ስምንት ነጥብ ይዞ 14ኛ ደረጃን በመያዝ በወራጅ ስጋት ውስጥ ይገኛል።

በክለቡ ወቅታዊ ሁኔታ ዙርያ ሰፊ ግምገማ ያደረገው የቦርድ አመራሩ ከአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ጋር ለመለያየት ከውሳኔ የደረሰ ሲሆን እንደ ምክንያት የቀረበው በሁለተኛው ዙር ቡድኑ መሻሻል አለማሳየቱ ሆኗል።

ቡድኑን በጊዜያዊነት እንዲያሰለጥኑ በቅርቡ የሴቶች ቡድን አሰልጣኝ ሆነው የተሾሙት የቀድሞው የቡድኑ አሰለልጣኝ በለጠ ገብረኪዳን ሲሾሙ ምንያምር ፀጋዬ በረዳትነት እንዲቀጥሉ መወሰኑ ታውቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡