የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ በ2020 ኦሊምፒክ ማጣርያ ምክንያት ከአንድ ወር በላይ ተቋርጦ ዛሬ በተደረጉ የ18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሲጀመር ባንክ፣ አዳማ፣ መከላከያ፣ ሀዋሳ እና አዲስ አበባ አሸንፈዋል። መዲና ዐወል እና መሳይ ተመስገንም የዕለቱ ኮከቦች ሆነው ውለዋል።
የአዲስ አበባ ስታድየም ውሎ
09:00 ላይ መከላከያ ከ ኤሌክትሪክ ያደረጉት ጨዋታ በመከላከያ 5-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። መዲና ዐወልም አራት ጎል በማስቆጠር ደምቃ ውላለች። ኤሌክትሪኮች ጨዋታውን በአማካይዋ ሰሚራ ከማል የ2ኛ ደቂቃ ጎል በጥሩ ሁኔታ ቢጀምሩም በዛው መዝለቅ አልቻሉም። ኤሌክትሪኮች በተለይ በ20ኛው ደቂቃ ከመሐል ሜዳ የተሻገረላት መሳይ ተመስገን በጥሩ ሁኔታ ተቆጣጥራ ግብ ጠባቂዋ ማርታን በማለፍ ከጎሉ ፊት የመታችው ኳስ በአስገራሚ ሁኔታ ቋሚውን ለትሞ በመውጣት የግብ ልዩነታቸውን የሚያሰፉበት ወርቃማ እድል ካመለጣቸው በኋላ በመከላከያ ከፍተኛ ብልጫ ተወስዶባቸዋል።
ቀስ በቀስ ጨዋታውን በመቆጣጠር የበላይ መሆን የቻሉት መከላከያዎች በ25ኛው ደቂቃ የመዲና ዐወል ጎል አቻ ሆነዋል። ጦረኞቹ ከጎሉ በኋላም ጥረታቸውን በመቀጠል አረጋሽ ከልሳ በ35ኛው ደቂቃ ከሳጥኑ ጠርዝ ሞክራ አግዳሚ ሲመልስባት፣ መዲና በ40ኛው ደቂቃ ከተመሳሳይ ቦታ ሞክራ ወደ ውጪ ወጥቶባታል። የመጀመርያው አጋማሽ የተጠናቀቀውም በ43ኛው ደቂቃ በመዲና ዐወል አማካኝነት በተቆጠረ ጎል መከላከያዎች 2-1 መሪ በመሆን ነበር።
ሁለተኛው አጋማሽ የመከላከያ የበላይነት ይበልጥ የታየበት ሲሆን ተደጋጋሚ ሙከራዎች እና ተጨማሪ ጎሎች ታይተውበታል። በ56ኛው ደቂቃ መዲና ዐወል ከግራ መስመር በራሷ ጥረት የቀማችውን ኳስ ወደ መሐል አጥብባ በመግባት ወደ ግብነት ቀይራ ሐት-ትሪክ ስትሰራ በ69ኛው ደቂቃ ደግሞ ከብሩክታዊት በግሩ ሁኔታ የተሻገረውን ኳስ ነፃ አቋቀም ላይ በመገኘት በጭንቅላቷ ገጭታ አራተኛ ጎሏን አስቆጥራለች። በ85ኛው ደቂቃ ደግሞ ከግብ ጠባቂ የተመለሰውን ኳስ አማካይዋ አረጋሽ ከልሳ የማሳረጊያውን ጎል አስቆጥራ ጨዋታው በመከላከያ 5-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
11:00 ላይ በቀጠለው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስን የገጠመው አዲስ አበባ ከተማ 3-1 አሸንፏል። ሁሉም ጎሎች በመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎች በተቆጠሩበት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በመጀመርያው አጋማሽ ተሽለው ቢንቀሳቀሱም ወደ ማጥቃት ወረዳ የደረሱበት አጋጣሚ ጥቂት ነበር። በዚህም ምክንያት በ40ኛው ደቂቃ መልካም ተፈሪ ካደረገችው ሙከራ ውጪ ሌላ እድል መፍጠር አልቻሉም። ጨዋታው ግማሽ ሰዓት ካለፈው በኋላ የተሻሻሉት አዲስ አበባዎች ምንም እንኳን ግልፅ እድል መፍጠር ባይችሉም በ33ኛው እና 42ኛው ደቂቃ በህይወት ረጉ፣ በ42ኛው ደቂቃ በኤደን ሽፈራው አማካኝነት ከርቀት አስደንጋጭ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር።
የተሻለ ፉክክር በታየበት ሁለተኛው አጋማሽ አዲስ አበባዎች የተሻለ ሲንቀሳቀሱ ቅዱስ ጊዮርጊሶች የጨዋታው ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር ሲዳከሙ ተስተውሏል። በዚህም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ግቦች ሊያስተናግዱ ችለዋል። 84ኛው ደቂቃ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከግብ ክልላቸው ኳስ በአግባቡ ያላራቁትን ኳስ ያገኘችው ሜላት ደመቀ በቀጥታ ወደ ጎል በመምታት አዲስ አበባ ከተማን ቀዳሚ ስታደርግ በ88ኛው ደቂቃ ተቀይራ የገባችው ሔለን መለሰ ከመሐል የተሻገረላትን ኳስ ከተከላካዮች አምልጣ በመውጣች በጥሩ አጨራረስ ሁለተኛውን አክላለች። ብዙም ሳይቆይ በአአ የጎል ክልል ኳስ በእጅ በመነካቱ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ብርሀን ኃይለሥላሴ በአግባቡ ተጠቅማ መልዩነቱን ብታጠብም በጭማሪው ደቂቃ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ ሌላዋ ተቀይራ የገባችው ቤተልሄም ሰማን በግምባሯ ገጭታ በቀድሞ ክለቧ ላይ አስቆጥራ ጨዋታው በአዲስ አበባ ከተማ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ጥረት 0-2 ንግድ ባንክ
(በሚካኤል ለገሰ)
ወደ ባህር ዳር የተጓዘው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2-0 በማሸነፍ በመሪነቱ ቀጥሏል። ቀዝቀዝ ባለ እንቅስቃሴ የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የግብ ሙከራዎችን ለማስተናገድ 10 ደቂቃዎች ፈጅተውበታል። በ10ኛው ደቂቃ ብርቱካን ገ/ክርስቶስ ለብዙዓየሁ ታደሰ አቀብላት በተፈጠረ እድል ወደ ጥረቶች ሳጥን የደረሱት ተጋባዦቹ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ባለሜዳዎቹ ጥረቶች ደግሞ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ወደ ባንኮች የግብ ክልል በትመር ጠንክር አማካኝነት ደርሰው የግብ ሙከራ አድርገዋል። ከ15ኛው ደቂቃ በኋላ እየተጠናከሩ ጨዋታቸውን ያደረጉት ባንኮች በርካታ የግብ እድሎችን በመፍጠር ግብ አስቆጥረዋል። በዚህም በ24ኛው ደቂቃ የተገኘውን የመዓዘን ምት ብዙዓየሁ ታደሰ በግምባሯ በመግጨት መሪ ሆነዋል። አንዱ ግብ ያረካቸው የማይመስሉት ባንኮች በ26፣ 29 እና 32ኛው ደቂቃ ረሂማ ዘርጋ ፣ ብርቱካን ገ/ክርስቶስ እና ብዙነሽ ሲሳይ በሞከሩት አስደንጋጭ ሙከራዎች የጥረቶችን የግብ ክልል በድጋሚ ለመጎብኘት ሞክረዋል።
የመሃል ሜዳው ብልጫ ከቁጥጥራቸው የወጣው ጥረቶቸ ፈጣኑዋን አጥቂ ምስር ኢብራሂምን ከፊት በማድረግ በመልሶ ማጥቃት ተጫውተዋል። በ36ኛው ደቂቃም በመልሶ ማጥቃት የተገኘውን የመዓዘን ምት ምስር አሻምታው እየሩሳሌም ተሾመ በግምባሯ በመግጨት በሞከረችው ሙከራ አቻ ለመሆን ጥረዋል። በመጨረሻዎች የመጀመሪያ አጋማሽ ደቂቃዎች ጨዋታውን በመቆጣጠር የጨረሱት ንግድ ባንኮች ተጋጣሚያቸውን ኳስ በመንፈግ ተረጋግተው ተንቀሳቅሰዋል።
ከእረፍት መልስ በነበሩት የመጀመሪያ 5 ደቂቃዎች ተጠናክረው የቀረቡት ጥረቶች ጥሩ ጥሩ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን በመፍጠር የአቻነት ጎል ፈልገዋል። በዚህም በ47ኛው ደቂቃ የተገኘን የቅጣት ምት የተከላካይ መስመር ተጨዋቿ ሀሳቤ ሙሳ አክርራ በመምታት ጥሩ ሙከራ አድርጋለች። ከአምስቱ ደቂቃዎች በኋላ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ የተዳከሙት ጥረቶች ሙሉ ለሙሉ ብልጫ ተወስዶባቸው ታይቷል። በ51ኛው ደቂቃ ብርቱካን ከረሂማ ጋር አንድ ሁለት ተቀባብለው ለሽታዬ ሲሳይ ያቀበሏትን ኳስ ሽታዬ ያመከነችው እንዲሁም በ54ኛው ደቂቃ ገነሜ ወርቁ በመታችው ጥሩ የቅጣት ምት ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር ሞክረው መክኖባቸዋል። ግብ ለማስቆጠር አሁንም ጥረታቸውን ያላቆሙት ንግድ ባንኮች በ55ኛው ደቂቃ ሁለተኛ ግብ አስቆጥረው መሪነታቸውን አስፍተዋል። የመጀመሪያው ግብ በተቆጠረበት መንገድ የመዓዘን ምት ያገኙት ባንኮች በተመሳሳይ ረሂማ በግምባሯ በመግጨት ባስቆጠረችው ጎል ነበረ ሁለተኛ ግብ ያስቆጠሩት። በምስር ላይ የተንጠለጠለው የጥረቶች የማጥቃት እንቅስቃሴ ፍሬ ሳያፈራ ጨዋታውን ማድረግ ቀጥሏል።
ከቆሙ ኳሶች አሁንም ግብ ለማስቆጠር ሙከራ ሲያደርጉ የነበሩት የሊጉ መሪዎች በ70ኛው ደቂቃ በሰነዘሩት ጥቃት ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበረ። የአጥቂ መስመራቸውን በአንፃራዊነተ ለማሻሻል ስትጥር የነበረችው አሰልጣኝ ሰርካዲስ ቀይራ ወደ ሜዳ ባስገባቻት ተጨዋች አማካኝነት በተፈጠረ ነገር ግን ምስር ባመከነችው አጋጣሚ እጅጉን ወደ ግብ ቀርበው ነበረ። ጨዋታውን ሙሉ ለሙሉ የተቆጣጠሩት ባንኮች በ86 እና 87ኛው ደቂቃ ሽታዬ ሲሳይ በሞከረችው ጥሩ ጥሩ ኳሶች መሪነታቸውን ለማስፋት ጥረው መክኖባቸዋል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በንግድ ባንኮች 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
አዳማ ከተማ 4-2 ድሬዳዋ ከተማ
(በዳንኤል መስፍን)
በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም አዳማ ከተማን ከድሬደዋ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ አዳማዎች በሎዛ አበራና ሴናፍ ዋቁማ ሁለት ሁለት ጎሎች 4-2 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል። ከጨዋታው አስቀድሞ የሁለቱም ቡድኖች አባላት የሞገስ ታደሰ ምስል ያለበትን ቲሸርት በማድረግ ለሞገስ ያላቸውን አጋርነት በጋራ በመሆን በመግለፅ ነበር ጨዋታው የተጀመረው።
በጨዋታው ጅማሬ ወደ ፊት በመሄድ ተጭነው መጫወት የቻሉት ባለሜዳዎቹ አዳማ የተሻለ ቢሆንም ጠንካራ ለጎል የቀረበ ሙከራ በማድረግ ቀዳሚ የነበሩት ድሬዎች ነበሩ። 5ኛ ደቂቃ ላይ አይዳ ዑስማን ፍጥነቷን ተጠቅማ ከተከላካዮች መሐል አፈትልካ በመውጣት የመታችውን ኳስ የአዳማዋ ግብጠባቂ እምወድሽ ይርጋሸዋ እንደምንም ያዳነችባት የጨዋታው የመጀመርያ ሙከራ ነበር። አዳማ ጎሉን እስካስቆጠሩበት ጊዜ ድረስ በክፍት ሜዳ የግብ ዕድል አይፍጠሩ እንጂ 7ኛው ደቂቃ ሎዛ አበራ ከቅጣት ምት የመታችው ኳስ ግብጠባቂዋ አክሱማይት ገ/ሚካኤል ያዳነችባት ተጠቃሽ ሙከራ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ የአዳማዋ የግራ መስመር ተከላካይ ነፃነት ፀጋዬ ከእራሷ የሜዳ ክፍል ኳሱን እየገፋች ተጫዋች በመቀነስ ያሻማችውን ሴናፍ ዋቁማ በግንባሯ በመግጨት ጎል አስቆጥራ አዳማዎችን ቀዳሚ ማድረግ ችላለች።
ከዚህ በኃላ ሙሉ ለሙሉ ተጭነው የተጫወቱት አዳማዎች በአስገራሚ የቡድን ቅንጅት ወደ ፊት ገብተው ሴናፍ መትታ ግብጠባቂዋ አክሱማይት ያዳነችባት እንዲሁም ሎዛ እና ሰርካዲስ ሳይጠቀሙበት የቀሩት ኳሶች የአዳማን የጎል መጠን ማስፋት በቻሉ ነበር። በድሬዎች በኩል እንደ ቡድን ከመጫወት ይልቅ ያገኙትን ኳስ አይዳን ፍለጋ መሠረት ያደረገ በመሆኑ የግብ ዕድል ለመፍጠር ቢቸገሩም 20ኛው ደቂቃ የአዳማ ተከላካዮችን ስህተት ተጠቅማ ስራ ይርዳው ጎል በማስቆጠር ድሬዎችን አቻ ማድረግ ችላለች።
ጎሉ ከተቆጠረባቸው በኃላ አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት ያልዘገዩት አዳማዎች 23ኛው ደቂቃ ሎዛ አበራ ባልተለመደ ሁኔታ ከሳጥን ውጭ በግራ እግሯ አክርራ በመምታት ለአዳማ ሁለተኛ ጎል ማስቆጠር ስትችል በተጨማሪ 29ኛው ደቂቃ ሰርካዲስ ጉታ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን ፍ/ቅ/ምት ሎዛ አበራ ወደ ጎልነት በመቀየር ለራሷ ሁለተኛ፤ ለቡድኗ ሦስተኛ ጎል አስቆጥራለች። በአይዳ ኡስማን ላይ ጥገኛ የሆኑት ድሬዎች ወደ እረፍት መዳረሻ ላይ እራሷ አይዳ ከርቀት ከፈጠረችው የግበ ዕድል በቀር ምንም አይነት የጎል መጠኑን ማጥበብ የሚችሉበት አጋጣሚ መፍጠር አልቻሉም።
ከእረፍት መልስ ብዙ ሳቢ ያልነበረ፣ በሁለቱም ቡድኖች በተደጋጋሚ በሚሰሩ ስህተቶች የቀጠለ ነበር። ያም ቢሆን 55ኛው ደቂቃ ሴናፍ ዋቁማ ከሰርካዲስ የተቀበለችውን ኳስ ወደ ጎልነት በቀየር ለራሷ ሁለተኛ ለቡድኑ አራተኛ ጎል አስቆጥራለች። ሴናፍ በውድድር ዓመቱ ያስቆጠረችውን የጎል መጠንም ወደ 16 ከፍ በማድረግ የኮከብ ጎል አስቆጣሪነቷን መምራቱን አጠናክራ ቀጥላለች። በቀሪዎቹ ደቂቃዎች አዳማዎች ተጨማሪ ጎል ማስቆጠር የሚችሉበትን አጋጣሚ ሎዛ ፣ ሴናፍ እና ሰናይት ከልክ ያለፈ በራስ መተማመን በማሳየት በመጀመርያ አጋጣሚ እግራቸው የገባውን ኳስ ወደ ጎልነት ከመቀየር ይልቅ ሌሎች ተጫዋቾችን በማለፍ ጎል ለማስቆጠር በማሰብ የተነሳ በሚሰሩ ተደጋጋሚ ስህተቶች ጎሎችን መመልከት አልቻልንም።
በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ተጭነው የተጫወቱት ድሬዎች 84ኛው ደቂቃ ተቀይራ የገባችው ቤተልሔም ኪዳኔ ሁለተኛ ጎል በማስቆጠር የጎል መጠኑን አጥብባ ጨዋታው በአዳማ ከተማ 4 – 2 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ሀዋሳ ከተማ 4-1 ጌዲኦ ዲላ
(በቴዎድሮስ ታከለ)
ሀዋሳ ከተማ በሜዳው መሳይ ተመስገን ሐት-ትሪክ ታግዞ ጌዲኦ ዲላን 4-1 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡ ከተያዘለት መደበኛ ደቂቃ በጣለው ዝናብ ምክንያት 25 ደቂቃዎችን ዘግይቶ የጀመረው ይህ ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ኳስ ይዞ የመጫወት ፍላጎትን ባሳዩት እንቅስቃሴ ውስጥ መመልከት ብንችልም እንደ አጀማመራቸው መዝለቅ ያልቻሉት ጌዲኦ ዲላዎች ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር በሀዋሳ ብልጫ ተወስዶባቸው ታይቷል። በሙከራ ረገድ ቀዳሚ የነበሩት ግን ዲላዎች ነበሩ፤ 4ኛው ደቂቃ ላይ ረድኤት አስረሳኸኝ በቅብብል ስህተት ከቅድስት ዘለቀ እግር ስር በመንጠቅ አክርራ የሞከረችው ኳስ ግብ ጠባቂዋ ትዕግስት አበራ ተቆጣጥራዋለች።
በመጀመሪያው ግማሽ እጅግ በጣም በርካታ ሙከራዎችን ማድረግ የቻሉት ባለሜዳዎቹ ቅድስት ቴቃ የመሀል ክፍሉን በሚገባ በመቆጣጠር ለአጥቂዎቹ በሚገባ በማድረስ ስኬታማ የሆነን እንቅርቃሴ ማድረግ ቢችሉም የቅብብሎሽ ስህተት ግን ዲላዎችን አልፎ አልፎ ለመልሶ ማጥቃት አጨዋወት አመቺ ሆኖላቸዋል፡፡ 11ኛ ደቂቃ ነፃነት መና ድንቅ ብቃቷን ስታደርግ ከነበረችሁ ቅድስት ቴቃ የተቀበለችውን ኳስ በቀኝ ሳጥኑ ጠርዝ እየገፋች ወደ ሳጥን ገብታ በቀላሉ ያመከነችሁ ኳስ አስቆጪ አጋጣሚም ነበረች፡፡ 19ኛው ደቂቃ ቅድስት ቴቃ ከመሳይ ጋር ተቀባብላ በስተመጨረሻ መሳይ ለምርቃት አመቻችታ አቀብላት የዲላዋ ተከላካይ መንደሪን ክንዲሁን ጉልህ ስህተት አስተዋጽኦ ታክሎት ምርቃት ሀዋሳ ቀዳሚ ያደረገች ግብ አስቆጥራለች፡፡ በግራ እና በቀኝ የማጥቃት መስመሩን እያፈራረቀች ስትጫወት የነበረችው እና ለጌዴኦ ዲላ ተከላካዮች ፈተና ሆና የዋለችው መሳይ ተመስገን በ26ኛው ደቂቃ ከሜዳው አጋማሽ በረጅሙ የተለጋውን ኳስ ፍጥነቷን ተጠቅማ በድንቅ አጨራረስ የሀዋሳን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችላለች፡፡
እንደ አጀማመራቸው ቀጣይነትን ማሳያት ያልቻሉት ዲላዎች ከድንቅነሽ እና ረድኤት ግላዊ እንቅስቃሴ ውጪ ግብ ለማስቆጠር ያደረጉቴ ጥረት እምብዛም ነበር፡፡ ምርቃት ፈለቀ በተደጋጋሚ ግልፅ የግብ አጋጣሚዎችን አግኝታ ግብ ጠባቂዋ ምህረት ተሰማ ካዳነችባት ከሁለት ደቂቃዎች በኃላ ሀዋሳ ተጨማሪ ግብ አስቆጥረዋል፡፡ 42ኛው ደቂቃ ካሰች ፍሰሀ በረጅሙ ያሻገረችውን ኳስ መሳይ በግንባሯ አብርዳ ከግብ ጠባቂዋ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝታ ወደ ግብ በመለወጥ የሀዋሳን መሪነት ይበልጥ ማስፋት ችላለች፡፡ በጭማሪው የእረፍት መውጫ ደቂቃ ላይ ትርሲት እና መገርሳ በተደጋጋሚ የቅብብል ስህተት ከሚታይባቸው ሀዋሳዎች እግር ስር የነጠቀችውን ለረድኤት አስረሳኸኝ ሰታት ከግቡ በግራ አቅጣጫ ከርቀት አክርራ መታ ጌዲኦ ዲላን ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረት ያደረገች ግብ ማስቆጠር ችላ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ብዙም የግብ ዕድሎችን መመልከት ባልቻልንበት ሁለተኛ አጋማሽ ጌዲኦ ዲላዎች በበሻዱ ረጋሳ አማካኝነት መልካም የግብ ዕድልን ቢያገኙም አልተጠቀሙም። በሀዋሳ በኩል ደግሞ 58ኛው ደቂቃ መሳይ ተመስገን ከቀኝ ሳጥኑ ወደ መሀል የሰጠቻትን ኳስ ተጠቅማ ጥሩ ሙከራ ያደረገችው ነፃነት መና በጌዴኦ ዲላ ተከላካዮች ተመልሶባታል። 76ኛው ደቂቃ በግራ አቅጣጫ በግምት 40 ሜትር ርቀት ላይ የተገኘችውን የቅጣት መሳይ ተመስገን አክርራ በቀጥታ ወደ ጎል መታ በግሩም ሁኔታ በማሳረፍ ለራሷ ሐት-ትሪክ የሰራችበትን ለሀዋሳ ደግሞ አራተኛ ግብ ማስቆጠር ችላለች፡፡ በቀሪዎቹ ደቂቃዎችም ግብ መቆጠር ሳይችል በሀዋሳ 4-1 አሸናፊነት መጠናቀቅ ችሏል፡፡
ዛሬ በተካሄደ ሌላ የ18ኛ ሳምንት መርሐ ግብር አሰላ ላይ ጥሩነሽ ዲባባ ከ አርባምንጭ ከተማ ጋር 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡