በ21ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መቐለ ላይ ደደቢትን የገጠመው ጅማ አባ ጅፋር በኦኪኪ ኦፎላቢ ብቸኛ ግብ 1-0 አሸንፏል።
ባለሜዳዎቹ ደደቢቶች ባለፈው ሳምንት በድሬዳዋ ከተማ ሽንፈት ከገጠመው ቡድናቸው ረሺድ ማታውኪል፣ እንዳለ ከበደ፣ ዳዊት ወርቁ እና ሙሉጌታ ዓምዶምን በማስወጣት በሙሴ ዮሃንስ ፣ ዳግማዊ ዓባይ፣ መድሃኔ ብርሃኔ፣ አሸናፊ እንዳለ ተክተው ሲቀርቡ ጅማ አባጅፋሮች ባለፈው ሳምንት ስሑል ሽረን ካሸነፈው ስብስባቸው ከድር ኸይረዲን፣ ኤልያስ አታሮ ፣ መስዑድ መሐመድ እና አስቻለው ግርማ በዐወት ገብረሚካኤል፣ መላኩ ወልዴ፣ አክሊሉ ዋለልኝ እና ዋለልኝ ገብሬ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።
ሁለቱም ቡድኖች ተመሳሳይ 4-4-2 ምርጫቸው አድርገው የጀመሩት ጨዋታ በርካታ ሙከራዎች ያስመለከተን ነበር። ሙከራ ለማድረግ ቀዳሚ የነበሩት እንግዶቹ ጅማዎች ሲሆኑ ዋለልኝ ገብሬ ነፃ ለነበረው ማማዱ ሲዲቤ አሻግሮለት የደደቢቱ አንቶንዮ አቡዋላ እንደምንም ወደ ውጭ አውጥቶታል።
በጨዋታው ጅማ አባጅፋሮች ምንም እንኳ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢወሰደባቸውም ከተጋጠሚያቸው የተሻለ በሦስተኛው የሜዳ ክፍል ብዙ ዕድሎች ፈጥረዋል። በተለይም በመጀመርያ አጋማሽ የዋለልኝ ገብሬ፣ ማማዱ ሲዲቤ እና ኦኪኪ ኦፎላቢ ጥሩ ተግባቦት ለበርካታ ሙከራዎች መፈጠር ምክንያት ነበሩ። ቀጥተኛ ኳስ እና በአንዳንድ አጋጣሚዎችም የመስመር አጨዋወት ለማጥቃት ጥረት ያደረጉት ጅማዎች በተጠቀሱት አጨዋወቶች በርካታ ዕድሎች ፈጥረዋል። ዲድየ ለብሪ ተጫዋች በማለፍ ከግብ ጠባቂው ሙሴ ዮሐንስ ተገናኝቶ ግብ ጠባቂው በድንቅ ብቃት ያዳነው ሙከራ እና ራሱ ዲድዬ በተቃራኒ ግብ ክልል የደደቢት ተጫዋቾችን ስህተት በመጠቀም አግኝቶ ያመከነው ኳስ በጅማዎች በኩል ከተፈጠሩት ሙከራዎች ይጠቀሳሉ።
በአንፃሩ በጨዋታው በኳስ ቁጥጥር ብልጫ የተሻሉ የነበሩት እና እንደ ብልጫቸው በርካታ ዕድሎች መፍጠር ያልቻሉት ደደቢቶች ምንም እንኳ ንፁህ የሚባል የግብ ዕድል ይፈጥሩም በርካታ አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለው ነበር። በተለይም መድሃኔ ብርሃኔ በረጅሙ የተሻገረለትን ኳስ ይዞ በመግባት መትቶ ለጥቂት የወጣው ሙከራ እና ያብስራ ተስፋዬ ከረጅም ርቀት ያደረገው ድንቅ ሙከራ ሰማያዊዎቹ ከፈጠሯቸው የግብ ዕድሎች የተሻሉት ነበሩ። በጨዋታው ከረጅም ጊዜ በኋላ የያብስራ ተስፋየ እና አቤል እንዳለ ጥሩ ጥምረት ያገኙት የደደቢቶች ከላይ ከተጠቀሱት ሙከራዎች ውጭም በዓለምአንተ ካሳ እና መድሃኔ ብርሃኔ ሙከራዎች አድርገው ነበር። በተለይም ዓለምአንተ ከያብስራ ተስፋየ ተቀባብሎ የሞከራት ኳስ ባለሜዳዎቹን ቀዳሚ ለማድረግ የተቃረበች ነበረች።
በሶስተኛው የሜዳ ክፍል የተሻለ ውጤታማ የነበሩት ጅማዎችም በማማዱ ሲዲቤ እና ዲድዬ ለብሪ ሁለት እጅግ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች አድርገው ነበር። ማማዱ ሲዲቤ በሳጥን ውስጥ ያገኘውን ኳስ መቶ ሙሴ ዮሃንስ በድንቅ ብቃት ያዳነው ኳስም በእንግዶቹ በኩል ወርቃማ ዕድል ነበር።
በሰላሳ አምስተኛው ደቂቃ ኦኪኪ ኦፎላቢ በረጅሙ የተላከለትን ኳስ ገፍቶ ወደ ሳጥን በመግባት በግቡ ቀኝ ጠርዝ በኩል ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።
የሰማያዊዎቹ ፍፁም ብልጫ እና ጥቂት የግብ ሙከራዎች የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ ተመጣጣኝ ፉክክር የታየበት ነበር። ኦኪኪ ኦፎላቢ ከቀኝ መስመር አክርሮ መቶ ሙሴ ዮሃንስ ባዳነው ሙከራ የጀመረው ጨዋታው በተለይም በመጀመርያዎቹ አስር ደቂቃዎች በርካታ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ያስመለከተ ነበር። ከነዚህም በደደቢት በኩል መድሃኔ ብርሃኔ አቤል እንዳለ ያሻማለት ኳስ ተጠቅሞ በግንባሩ ያደረገው ሙከራ እንዲሁም በጅማ አባጅፋር ኦኪኪ ኦፎላቢ በግል ጥረቱ ያደረገው ሙከራ ይጠቀሳሉ።
ከላይ ከተጠቀሱት ሙከራዎች ውጭም ሙሴ ዮሃንስ አርቃለው ብሎ በደምብ ያላራቀው ኳስ ይሁን እንደሻው አግኝቶ ወደ ግብ ቢልከውም ሃይሉ ገብረየሱስ ግብ ከመሆኑ በፊት አድኖታል።
በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የተከላካይ መስመሩ ተጫዋቹ ሃይሉ ገብረየሱስ ወደ አጥቂ ክፍል በመውሰድ የተሻለ ጫና ፈጥረው የተጫወቱት ደደቢቶች ምንም እንኳ አቻ የሚያደርጋቸው ግብ ባያገኙም በርካታ ዕድሎች ፈጥረው ነበር።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የደደቢት አሰልጣኞች ቡድን ጨዋታውን የመሩትን ዳኞች ላይ ተቃውሟቸው ሲያሰሙ ተስተውለዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡