በ21ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለቻምፒዮንነት እየተፎካከረ የሚገኘው ሲዳማ ቡና እና ላለመውረድ እየታገለ ያለው ስሑል ሽረን ያገናኘው ጨዋታ በሲዳማ ቡና 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ባሳለፍነው ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ ሽንፈት ካስተናገዱበት አሰላለፍ የሰባት ተጫዋቾች ለውጥ ያደረጉት ሲዳማ ቡናዎች ግሩም አሰፋ፣ ዳግም ንጉሴ፣ ተስፉ ኤልያስ፣ ዮሴፍ ዮሐንስ፣ ትርታዬ ደመቀ፣ ወንድሜነህ ዓይናለም እና መሐመድ ናስርን በማሳረፍ ዮናታን ፍስሀ፣ ሚሊዮን ሰለሞን፣ ሰንደይ ሙትኩ፣ ግርማ በቀለ፣ ሚካኤል ሀሲሳ፣ ዳዊት ተፈራ እና ይገዙ ቦጋለን ተጠቅመዋል። በአንፃሩ እንግዳዎቹ ስሑል ሽረ የሁለት ተጫዋቾችን ለውጥ በማድረግ ዮናስ ግርማይ እና ያስር ሙገርዋን አስወጥተው ሙሉዓለም ረጋሳን እና ዲሜጥሮስ ወ/ሥላሴን ተጠቅመዋል።
በመጀመሪያው ግማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል አጥቅተው የመጫወት ፍላጎትን ያሳዩ ሲሆን በተለይ ደግሞ የሲዳማ ቡና የበላይነት የተስተዋለበት ነበር። ዳዊት ተፈራ መሰረት አድርገው ለአዲስ ግደይ እና ሐብታሙ ገዛኸኝ ለማድረስ ያለሙ ኳሶች ሲጠቀሙ የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች በሙከራም ቀዳሚ ነበሩ። 1ኛ ደቂቃ ላይ ከዳዊት ተፈራ የተነሳችው ኳስ አዲስ ግደይ ተቆጣጥሮ ሶስት ተጫዋቾችን አታሎ ለሐብታሙ ገዛኸኝ አቀብሎት አጥቂው ከሳጥኑ ውጭ በስተቀኝ በኩል አክርሮ ሲመታ ግብ ጠባቂው ሐብቶም ቢሰጠኝ አውጥቶበታል። በአንፃሩ ደግሞ እንግዳዎቹ ስሑል ሽረዎች ከሙሉዓለም ረጋሳ በሚነሱ ኳሶች በግራ የማጥቃት ክፍል አመዝነው አርአዶም ግብረህይትን አነጣጥረው ለመጫወት ቢሞክሩም አጥቂ ስፍራ ላይ በነበሩት ዓርአዶም፣ ሳሊፍ ፎፋና እና ቢስማክ አፒያ ሲባክኑ ተስተውለዋል። ከወትሮው በተለየ ተደጋጋሚ ስህተት ሲሰሩ የነበሩት የሲዳማ ቡና ተከላካዮችን ክፍተት በመጠቀም 12ኛ ደቂቃ ላይ ሙሉዓለም ረጋሳ ከሳጥን ውጭ ፈቱዲን ጀማል በአግባቡ መቆጣጥር ያልቻላትን ኳስ አግኝቶ ያሻገረውን ሳሊፍ ከቢስማርክ ጋር አንድ ሁለቴ ተጫውቶ የሞከራት የእንግዶቹ ቀዳሚ ሙከራ ነበር።
በ14ኛ ደቂቃ ዳዊት የሞከረው ኳስ በተከላካዮች ሲመለስ አዲስ ግደይ ተቆጣጥሮ ከርቀት አክርሮ በመምታት የግብ ጠባቂው ሐብቶም ቢሰጠኝ የአቋቋም ስህተት ታክሎበት ኳስ እና መረብን በማገናኘት ሲዳማ ቡናን መሪ ማድረግ ችሏል። ከዚህች ግብ መቆጠር ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ አዲስ ግደይ በድጋሚ ከመሀል ሜዳ በድጋሚ ዳዊት ተፈራ ያሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ስብሮ ቢገባም ከአሳሪ አልማህዲ አስጥሎታል። ሽረዎችም ለዚህች ሙከራ መልስ በመስጠት ከቢስማርክ አፒያ የተቀበላትን ኳስ ሙዓለም ረጋሳ ሞክሮ ፍቅሩ ወዴሳ ተቆጣጥሯታል።
ሲዳማ ቡና ከመሀል ክፍሉ አደጋ ፈጣሪ ኳሶች ለአጥቂዎቹ በሚገባ ሲያቀርብ የነበረው እና በዚህ ጨዋታ ድንቅ እንቅስቃሴን ያደረገው ዳዊት ተፈራ 25ኛው ደቂቃ በረጅሙ ያሻማትን ኳስ ይገዙ በግንባሩ ሞክሮ አግዳሚውን ለትማ ለጥቂት ወደውጭ ወጥታበታለች። ከሶስት ደቂቃዎች በኋላም በቀኝ መስመር በኩል የነበረው ሐብታሙ ገዛኸኝ ሶስት ተጫዋቾችን አታሎ ኳስ እየነዳ ወደ ሳጥን ውስጥ ቢገባም የሽረ ተከላካዮች ተረባርበው አውጥተውታል። 29ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻማን ኳስ አዲስ ግደይ በግንባሩ ገጭቶ ሀብቶም ቢሰጠኝ ለጥቂት በጣቶቹ በመንካት በአግዳሚው በኩል ያወጣበት ኳስም ሲዳማ ቡና ተጨማሪ ግብ የሚያገኝበት አጋጣሚ ነበረች።
44ኛው ደቂቃ ከመሀል ሜዳ በረጅሙ የተሻማችው ያልተመጠነች ኳስ ላይ ለመድረስ ይገዙ ቦጋለ በፍጥነት ወደ ስሑል ሽረዎች የግብ ክልል ሲገባ ሐብቶም ቢሰጠኝ ኳሷን ለመቆጣጠር ሲል ጥፋት በመስራቱ ምክንያት የተገኘችውን የፍፁም ቅጣት ምት በአግባቡ ተጠቅሞ አዲስ ግደይ መሪነቱን ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ሲችል የጎሎቹ መጠን 12 በማድረስም በከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት ሰንጠረዥ ከመቐለ 70 እንደርታው አማኑኤል ገብረሚካኤል ጋር መስተካከል ችሏል።
በሁለተኛው አጋማሽ ስሑል ሽረ የነበሯቸውን ስህተት አርመው በመግባት ለሲዳማ ቡና ፈተና ሆነዋል። በአንፃሩ ባለሜዳዎቹ ከመጀመሪያው ግማሽ እጅጉ ተዳክመው ሲቀርቡ በተለይ የመስመር ተከላካዮቻቸው ተደጋጋሚ ስህቶችን በመፈፀማቸውም ግቦችን ለማስተናገድ ተገደዋል። 50ኛው ደቂቃ ሳሊፍ ፎፎና ከቢስማርክ የተመቻቸለትን ኳስ የፈቱዲን ጀማልን ስህተት በመጠቀም ወደ ግብ ቀይሮ የግብ ልዩነቱን አጥብቧል። ከጎሉ በኋላም ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉት ስሑል ሽረዎች በ60ኛው ደቂቃ ሳሊፍ ፎፎና በሁለት ተከላካዮች መሐል ወጥቶ በዚህ ጨዋታ ደካማ እንቅስቃሴን ሲያደርግ ለነበረው አርዓዶም ገብረህይት አቀብሎት ሲሞክር ፈቱዲን ጀማል ተንሸራቶ ያወጣት ኳስ አቻ ለመሆን የሚያስችላቸው አጋጣሚ ነበር።.
በዚህ አጋማሽ የተቀዛቀዙት ሲዳማ ቡናዎች ስሑል ሽረዎች ለሚሰሯቸው ስህተቶች ግን መልስ ከመስጠት አልተቆጠቡም። በዚህም 72ኛው ደቂቃ ላይ ስሑል ሸረዎች ከግብ ክልላቸው መስርተው ወደፊት ለማጥቃት ሲሞክሩ የሰሩትን የቅብብል ስህተት ኳሷን ያገኛት አዲስ ግደይ ለዳዊት ተፈራ አመቻችቶ ያቀበለውን የመሀል ስፍራ ተጫዋቹ ከሳጥን ውጭ በመምታት ለሀብቶም ቢሰጠኝ ኳሷን የማዳን ምንም እድል ሳይሰጥ እጅግ ግሩም ጎል አስቆጥሮ ሲዳማ ቡና ሶስት ለአንድ እንዲመራ አስችሏል። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ 76ኛው ደቂቃ ላይ ሳሊፍ ፎፋና ከያስር ሙገርዋ ያገኛትን ኳስ የተከላካዮችን ስህተት ተጠቅሞ ግብ በማድረግ ችሎ የሽረዎች ተስፋ መልሶ ማለምለም ችሏል።
በመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎች በሁለቱም በኩል የጎል አጋጣሚዎች የተፈጠሩ ሲሆን በ81ኛው ደቂቃ ዳዊት ተፈራ የማዕዘን ምት ከማሻማት ይልቅ በቅርብ ርቀት ለነበረው ሐብታሙ ገዛኸኝ ስጥቶት ሐብታሙ ሲሞክር አግዳሚውን ለትማ ወደውጭ የወጣችበት፣ በጨዋታው መገባደጃ አከባቢ ተቀይሮ ከገባው አበባየሁ ዮሀንስ የተሻገረችለትን ጥሩ ኳስ አዲስ አብርዶ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ አገባወረ ሲባል ሳይጠቀምባት የቀረችው ሐት-ትሪክ ሊሰራበት የሚችልበት ተጠቃሽ የሲዳማ ቡና ሙከራዎች ነበሩ። በሽረም በኩል በጭማሪው ደቂቃ አቻ ሊሆኑ የሚችሉበትን እድል ፎፋና አምክኖ ጨዋታው በሲዳማ ቡና 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡