የአሰልጣኞች አስተያየት | ሲዳማ ቡና 3-2 ስሑል ሽረ

በ21ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሀዋሳ ላይ ሲዳማ ቡና ስሑል ሸረን አስተናግዶ በሲዳማ ቡና 3-2 አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ስጥተውናል።
“ጨዋታው በጣም ጠንካራ ነበር” ዘርዓይ ሙሉ (ሲዳማ ቡና)

ስለ ጨዋታው

ሽረዎችን እንዲህ አልጠበቅናቸውም ነበር። በሁለተኛው ዙር በጣም ተሻሽለው ነው የመጡት። በመጀመሪያው ግማሽ ጥሩ ተጫውተን የምንፈልገውን አሳክተናል። ሁለተኛ ግማሽ ግን ከሽንፈት ስለተመለስን በተጫዋቾቹ ላይ በራስ መተማመን አልነበረም፤ በተለይ ደግሞ የተከላካይ ክፍላችን። ከዛ ውጪ ወደፊት ስናጠቃ የነበረው ነገር ከመቸውም ጊዜ በተለየ በጣም ጥሩ ነበር፤ ብዙ ኳሶችንም ስተናል። የስሑል ሽረ አጥቂዎች በሳል እና ኳስን በአእምሮ የሚጫወቱ ናቸው። ትንሽ ክፍተት ብንሰጣቸው ኖሮ ሊጠቀሙ የሚችሉ ናቸው፤ ልዩነቱ ያ ነው። ግን ጨዋታው በጣም ጠንካራ ነበር።

የተከላካዮች ስህተት

በመጀመሪያው አጋማሽ ተከላካዮቼ ሲያጠቁም ሲከላከሉም በጣም ጥሩ ነበሩ። ግን የኋላ ተከላካዮቻችን ከጉዳት ዛሬ ስለተመለሱ እንደበፊቱ አልነበሩም። በተለይ ደግሞ ከእረፍት በኋላ በነሱ መዳከም የፈለግነውን ማድረግ አልቻልንም።

“ሁለት ጨዋታ ከሜዳ ውጭ መጫወታችን ከባድ አድርጎብናል” ሳምሶን አየለ (ስሑል ሽረ)

ስለ ጨዋታው

አጠቃላይ ጨዋታው ያው እንዳያችሁት ነው። በመጀመሪያው ግማሽ የተቆጠረብን ጎል ከርቀት ተመቶ በግብ ጠባቂያችን የአቋቋም እና ትኩረት ማጣት ችግር ነው። በሁለተኛው ግማሽ ግን ተጭነን በመጫወት ግብ ማግባት ችለናል። እኔ ከመጣው ጀምሮ ከሰማንያ ፐርሰንት በላይ አዳዲስ ተጫዋቾችን አስገብተን አዲስ ቡድን ሰርተን ነው እየተፎካከርን ያለነው። ሁለት ጨዋታዎች ከሜዳ ውጭ መጫወታችን ግን ከበድ አድርጎብናል። በቀሪዎቹ ዘጠኝ ጨዋታዎች ጥሩ ለመስራት እንጥራለን።

የመውረድ ስጋት

ከኛ ከፍ ብለው ካሉት ልዩነታችን የአራት ወይም አምስት ነጥብ ነው። አሁንም እድሉ አለን፤ እንዳላችሁት ስጋት ውስጥ ነው ያለነው። ሆኖም እስከመጨረሻው ድረስ በሕብረት ሰርተን እንተርፋለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡