ደስታ ጊቻሞ ወደ ቀደመው ከፍታው መመለስን ያልማል

እንደ ደስታ ጊቻሞ የእግርኳስ ህይወታቸው በፈጣን ሁኔታ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ ተጫዋቾች ጥቂት ናቸው። የተከላካይ መስመር ተጫዋቹ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን መለያ የለበሰው ገና የክለብ ህይወትን ሳይጀምር ነበር። ሆኖም ከዛ በኋላ ባሉት ዓመታት በጉዳት ከእግርኳሱ ርቆ ቆይቶ ዳግም በማንሰራራት በሊጉ እየተጫወተ ይገኛል።

ሻሸመኔ ከተማ ተወልዶ ሾኔ ማዞርያ በሚባል አካባቢ ነው ያደገው ደስታ የእግርኳስ ህይወቱ መጀመርያ ዓመታት ፈጣን እድገት ያሳየበት ነበር። ከወራህ በፊት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ታላቁ አሰልጣኝ ሥዩም ዓባተ ዓይን ያረፈበትም ገና ታዳጊ ሳለ ነበር። “እግርኳስ አጀማመሬ አስቸጋሪ ነበር። ምክንያቱም ተማሪ ስለነበርኩ ኳስ በሰዓቱ ስለማይታወቅ ወላጆቼ እንድጫወት አይፈቅዱልኝም ነበር። እግር ኳስን በፕሮጀክት ተጫውቼ ስላላደግኩ መነሻዬ የቀበሌ ጨዋታ ነው። ሾኔ ማዞርያ ውስጥ ለአዲሎ ቀበሌ እንጫወት ስለነበር ሾኔን በመወከል ዱራሜ ሄድኩኝ። ከዱራሜ በኃላ በክልል ደረጃ ሀዋሳ ላይ ለሚካሄደው የዞኖች ጨዋታ መመረጥ ችዬ ወደ ሀዋሳ ሄድኩ። በዛ እየተጫወትኩ ሳለው ለታዳጊ ብሔራዊ ቡድን ምልመላ ይደረግ ስለነበር በምልመላ ላይ የነበሩት አሰልጣኝ ሥዩም አባተ ወድያው እንዳዩኝ ነበር የመረጡኝ። ያኔ ነበር ኳስን በትክክል መጫወት የጀመርኩት። ለታዳጊ ብሔራዊ ቡድኑ ተመርጬ መጫወት ቻልኩኝ። ስጫወት እንኳን ክለብ አልነበረኝም። ምክንያቱም ቀጥታ ከዞን ጨዋታ ነበር ለታዳጊ ብሔራዊ ቡድን የተመረጥኩት። ” ሲል ስለ አጀማመሩ ያወሳል።

በ2008 (እ.አ.አ) ጋና ላስተናገደችው የአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሊቢያ፣ ናሚቢያ እና ኮንጎ ዲ.ሪ. ጋር ተደልድሎ የማጣርያ ጨዋታዎችን በማድረግ ላይ ነበር። ነሐሴ ወር 1998 ላይ በሜዳው ሊቢያን 1-0 አሸንፎ አጀማመሩን ያሳመረው ብሔራዊ ቡድኑ በቀጣይ ከሜዳው ውጪ መስከረም 1999 ላይ ናሚቢያን ይገጥማል። የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሥዩም አባተ ለወሳኙ ጨዋታ ልምድ እና ጥሩ ወቅታዊ ብቃት ያላቸው ተጫዋቾችን ይጠቀማሉ ተብሎ ቢጠበቅም ታዳጊው ደስታ ጊቻሞን የመጀመርያ ተሰላፊነት እድል ሰጡት። ከደስታ ጀርባም በግብ ጠባቂነት ለሌላኛው ታዳጊ ተመስገን ጮኖሬ የመሰለፍ እድል መስጠታቸው ሲሰማ ወትሮውንም ከሜዳው ውጪ የማሸነፍ ልማዱ እምብዛም የሆነው ብሔራዊ ቡድን ከጨዋታው ምን ይዞ ይወጣ ይሆን የሚለው አነጋጋሪ ሆነ።

ጨዋታው በናሚቢያ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቀቀ። ደስታ በጨዋታው ጥሩ ቢንቀሳቀስም የብቸኛዋ ጎል መነሻ የሆነችውና ኩዊንተን ጃኮብስ በ18ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት የፍፁም ቅጣት ምት የተገኘችው በእሱ አማካኝነት ነበር። ሆኖም ከሽንፈቱ ባሻገር የአሰልጣኝ ሥዩም ድፍረት የታከለበት የማሰለፍ ውሳኔ እና የልምድ አልባው ተከላካይ እንቅስቃሴ መነጋገሪያ ሆኖ ሰነበተ።

” ለታዳጊ ብሔራዊ ቡድን ተመርጬ ከሄድኩ ከአንድ ዓመት በኋላ 1999 ላይ የመጀመሪያ ክለቤ ለሆነው መድን ለሁለት ዓመት ፈርሜ መጫወት ጀመርኩ። የወቅቱ የመድን አሰልጣኝ ሥዩም አባተ ነበር እዛ እንድገባ ያረጉኝ። ከዛ በኋላ ነው ለዋናው ብሔራዊ ቡድን መመረጥ የቻልኩት። እነ አንዳርጋቸው እና ደጉ ደበበን የመሳሰሉ በጣም ትልልቅ ተጫዋቾች በነበሩበት ብሔራዊ ቡድን የክለብ ልምድ እንኳን ሳይኖረኝ ሥዩም አባተ በናሚቢያው ጨዋታ ከደጉ ጋር አጣመሩኝ። (ሳቅ) በኔ ጥፋት የናምቢያን ተጫዋች ጠልፌ ፍፁም ቅጣት ምት ተሰጠብን። ያ ጎል ሆኖ 1-0 አሸነፉን። በዚህ አጋጣሚ ምንም ልምድ ሳይኖረኝ ኃላፊነቱን ወስደው ለዚህ ያበቁኝ አሰልጣኝ ሥዩም አባተን ላመሰግናቸው እፈልጋለሁ።”

አንድም የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ሳያደርግ ለብሔራዊ ቡድን የተጫወተው ደስታ የክለብ ህይወቱ ግን አልጋ በአልጋ ሊሆንለት አልቻለም። በመጀመርያው ዓመት የመድን ቆይታው ጥሩ ጊዜ ካሳለፈ በኋላ በ2000 የውድድር ዘመን በደረሰበት የጉልበት ጉዳት ምክንያት ለቀጣዮቹ ስድስት ዓመታት ከኢትዮጵያ እግርኳስ ጠፍቶ ለመቆየት ተገዷል። ” ጉልበቴ ላይ ጉዳት ደረሰብኝ ጉዳቴ ከበድ ያለ ስለነበር በ2001 ለህክምና ወደ ደቡብ አፍሪካ አመራሁ። ከረጅም ጊዜ የህክምና ሒደት በኋላ ባገግምም ወደ ኢትዮጵያ አልተመለስኩም፤ በዛው በደቡብ አፍሪካ ከቆየሁ በኋላ 2006 ላይ ወደ ሀገሬ ተመልሼ መጣው። በዓመቱ አጋማሽ ጤንነቴ ስለተመለሰ በወቅቱ ከ አሸናፊ በቀለ ጠርቶኝ አዳማ ከተማን ተቀላቀልኩ።” የሚለው ደስታ በወቅቱ በብሔራዊ ሊግ ሲወዳደር የነበረውና ወደ ፕሪምየር ሊጉ የሚመልሰውን ድል ባሳካው አዳማ ከተማ ግማሽ ዓመት ቆይታ ካደረገ በኋላ በዛው በብሔራዊ ሊግ ቆይቶ ወደ ሻሸመኔ አመራ። በ2007 በሻሸመኔ ሙሉ ዓመት መጫወት ቢችልም በብሽሽት ጉዳት ቀጣዩን የውድድር ዓመት ከሜዳ ርቆ ቆየ። ከጉዳቱ ካገገመ በኋላም አሁን እየተጫወተበት የሚገኘው ደቡብ ፖሊስን በ2009 በመቀላቀል ቡድኑን ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዲያድግ ከመርዳቱ በተጨማሪ ከአስር ዓመታት በኋላ በድጋሚ በሊጉ ለመጫወት በቃ።

በኢትዮጵያ እግርኳስ በተለያዩ ምክንያቶች ከእግርኳስ በጊዜ የተገለሉ ተጫዋቾች በርካታ ናቸው። እንደ ደስታ ውጣ ውረዶችን በጥንካሬ እና ትዕግስት አልፈው በድጋሚ ለመጫወት የሚበቁት ደግሞ እጅግ ጥቂቶች ናቸው። ” ከደቡብ አፍሪካ ስመለስ ለምን መጣህ? ለገንዘብ ከሆነ እዚህ ከምትጫወት እዛው ብትሰራ አይሻልም ነበር ወይ ይሉኝ ነበር። እኔ ግን መጀመሪያም እግር ኳሱ በውስጤ ስላለ አላማዬ ኳስ መጫወት እንጂ ሌላ ነገር አይታየኝም ነበር። በህክምናውም እግዚአብሄር ፈውስ ሰጠኝ፤ እርሱ ስለሚጠብቀኝ እኔም በተቻለኝ መጠን ራሴን እጠብቃለሁ። ለምሳሌ ከሱስ፤ ከተወለድኩ ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ አንድም ቀን መጠጥ ጠጥቼ አላውቅም። ምክንያቱም ሁሉንም ነገር እንደርስበታለን። ቅድሚያ መስጠት ያለብን ለያዝነው አላማ ነው። አላማችንን ካሳካን በኋላ እናገኘዋለን። ምን ልሰራ ነው የምጫወተው የሚለውን ነገር ማሰብ አለብን። ማንም እስከ መጨረሻው አይጫወትም፤ እድሜ ይገድበዋል። የፈለግነውን ነገር በአግባቡ ካሳካን በኋላ ሁሉንም በጊዜው ማድረግ እንችላለን። እስከዛ ድረስ ግን ራሳችን መጠበቅ አለብን ነው የምለው። ” ሲል እግርኳስ ላይ ብቻ ማተኮሩ ወደ ሜዳ እንዲመለስ እንደረዳው ይናገራል።

ከብዙ ውጣ ውረዶች በኋላ ደቡብ ፖሊስ እና ደስታ ጊቻሞ በድጋሚ በጥሩ ጎዳና ላይ መራመድ ሲጀምሩ የመሐል ተከላካዩም ከጉዳት ነፃ ጊዜ እያሳለፈ ከመሆኑ በተጨማሪ የቡድኑ አምበል ሆኖ ቡድኑን ከወራጅነት ስጋት ለማላቀቅ እየተጋ ይገኛል። ላለመውረድ የሚያደርጉት ጥረት በስኬት እንደሚታጀብም ከፍተኛ ዕምነት አለው። “እርግጠኛ ሆኜ የምነግርህ ነገር ተጫዋቾቹ ላይ ከማየው መነሳሳት፣ ፍላጎት እና ችሎታ ተነስቼ ክለባችን እንደማይወርድ ነው። የማይሆኑ ስህተቶች ናቸው ችግር እየፈጠሩብን ያሉት እንጂ ሜዳ ላይ ያለው ነገር ጥሩ ነው። ክለቡን እንዲወጣም እንዳይወርም የምናደርገው እኛ ነን። እንዳይወርድ ተነሳሽነት ያስፈልጋል፤ ራሳችን ለማሳየት የሚጠቅመንም ክለቡ ሳይወርድ ሲቀር ነው። ያለፈውን አስከፊ ጊዜያትን ረስተናቸዋል። ገብረክርስቶስ ቢራራ ወደ ቡድኑ ከመጣ በኋላ እያደረግን ያለነው ከፊታችን ስለምናደርገው ትኩረት መስጠት እንጂ ስለሌላው ጨዋታ አናስብም። ” ይላል።

የመሐል ተከላካዩ ደቡብ ፖሊስ ባለፉት ጨዋታዎች ላይ በመከላከሉ ላሳየው መሻሻል ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። በጥሩ ወቅታዊ አቋሙ ከቀጠለም ከ12 ዓመታት በፊት ያገኘውን ለብሔራዊ ቡድን የመጫወት ዕድል መልሶ ያገኘው ይሆናል። የደስታ አላማም አረንጓዴውን መለያ መልሶ ማጥለቅ ነው። ” (ሳቅ) በድጋሚ ለብሔራዊ ቡድን መጫወት እፈልጋለሁ። ከደቡብ አፍሪካ ስመለስ እዛ የነበሩ ጓደኞቼ አርፈህ ስራህን ስራ .. ኳስ ኳስ አትበል ሲሉኝ ድጋሚ ለብሔራዊ ቡድን ስጫወት ታዩኛላችሁ እያልኩ በቁጭት እመልስላቸው ነበር። ከመጣው በኋላ እየደወሉም ይጠይቁኛል። እንዴት ነው ተሳካልህ ወይ? ይሉኛል። ጠብቁኝ ብያቸዋለው። ያን ግብም ጠንክሬ በመስራት አሳካዋለሁ። ”

በመጨረሻም ደስታ በእግርኳስ ህይወቱ ጉልህ ሚና የተጫወቱት ሁለት አሰልጣኞችን ያመሰግናል። ” በመጀመሪያ እግዚአብሄርን ማመስገን እፈልጋለሁ። ቀጥሎ የዱራሜ ዞን አሰልጣኝ የነበሩት ወንድሙ ላላጎን። ለታዳጊ ብሔራዊ ቡድን ተመርጬ አዲስ አበባ ለመሄድ የሚያስፈልገኝ 150 ብር አልነበረኝም ነበር። ቤተሰቦቼ ኳስ እንድጫወት ስለማይፈልጉ በተለይ አባቴን መጠየቅ ፈራሁ። እርሱ ግን መሄድ አለብህ ክለብም ልታገኝ ትችላለህ ብሎ 150 ብር ሰጠኝ።

” ነብሱን ይማር አሰልጣኝ ሥዩም አባተ በህይወቴ ትልቅ ቦታ እንድደርስ ያደረገኝ እና አሁን ላለሁበት ደረጃ ያበቃኝ አሰልጣኝ ነው። ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችን አስቀምጦ ለብሔራዊ ቡድንም እንድጫወት ያደረገኝ እሱ ነው። አሁን ላይ ለአሰልጣኝ ሥዩም ብዬ ነው እግር ኳስን የምጫወተው። ያኔ በልጅነቴ አይቶኝ ነው ወደ ክለብ ያስገባኝ አሰልጣኝ አሁን ከጉዳቴ ተመልሼ በህይወት ኖሮ ቢያየኝ ምንኛ ደስ ባለኝ። ”


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡