ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና ባህር ዳር ላይ የጎል ናዳ በማውረድ የዓመቱን ትልቅ ድል አስመዝግቧል

በ21ኛው ሳምንት የሊጉ መርሐግብር እስካሁን በጨዋታ ከሁለት ግቦች በላይ ተቆጥረውበት የማያውቀው እና ከአንድ ግብ ልዩነት ባላይ ሳይሸነፍ የቆየው ባህር ዳር ከተማ በኢትዮጵያ ቡና እጅ የ5-0 ሽንፈት ደርሶበታል።

ኢትዮጵያ ቡና በወላይታ ድቻ ከተሸነፈበት ጨዋታ የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ወንድይፍራው ጌታሁን እና ሄኖክ ካሳሁንን በክሪዚስቶም ንታንቢ እና ዳንኤል ደምሴ ሲተካ ባህር ዳር ደግሞ መቐለ 70 እንደርታን የረታውን ስብስቡን ሳይቀይር ወደ ሜዳ ገብቷል።

የጨዋታው የመጀመሪያ 15 ደቂቃዎች ከቀጣዮቹ የተለዩ ነበሩ። ወደ ፊት ጫን ብለው የጀመሩት ባህር ዳሮች በተሻለ ምቾት ኳስ ይዘው በቡና ሜዳ ላይ ይታዩ የነበረ ሲሆን ተደጋጋሚ የቆመ ኳስ ዕድሎችንም አግኝተው ነበር። ቡድኑ ከኳስ ውጪም ከግብ ክልሎ ርቆ በመከላከል እና የኢትዮጵያ ቡናዎችን ቅብብሎች በቶሎ በማቋረጥ መልካም አጀማመር ማድረግ ችሎ ነበር። ነገር ግን ኳስ መስርተው ወደ ባህር ዳር ሳጥን መድረስ ያልቻሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች አልፎ አልፎ ረጅም ኳሶችን ለመጠቀም ቢገደዱም ከሀሪሰን ሄሱ እና በተከላካዮቹ መሀል የነበረውን የጣና ሞገዶቹን ሰፊ ክፍተት በተለይም በካሉሻ አልሀሰን ኳሶች ሰንጥቀው ለማለፍ ሲሞክሩ ይታይ ነበር። ይህ የባለሜዳዎቹ የማጥቃት ጥረት በጨዋታ ውጪ አቋቋም በተከታታይ ውጤታማ ሳይሆን ቢቀርም ደቂቃዎች ካለፉ በኋላ ግን ለበርካታ ዕድሎች እና ሦስት ግቦች መቆጠር ምክንያት ሆኗል።

18ኛው ደቂቃ ላይ ተካልኝ ከግራ መስመር ያደረሰውን ኳስ ባልተለመደ ሁኔታ ነፃ ሚና ተሰጥቶት ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው አቡበከር ነስሩ ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ ሲመታ ተከላካዩ አሌክስ አሙዙ አቅጣጫ አስቀይሮት በሀሪሰን መረብ ላይ አርፏል። ከግቡ በኋላ እንደቀደመው ኳስ ይዘው የሜዳውን አጋማሽ በሚሻገሩባቸው አጋጣሚዎች የአስራት ቱንጆ እና ዳንኤል ደምሴን ጥምረት ማለፍ ያልቀለላቸው ባህር ዳሮች የሚቀሟቸው ኳሶች ከተከላካዮቻቸው ጀርባ በተውት ክፍተት በኩል እንዲጠቁ አስገድዷቸዋል። ከቁጥር ብልጫ ጋር ሰፊ ሜዳ ክፍል ሸፍነው ይጫወቱ የነበሩት የቡና አማካዮችም በቶሎ ወደ ባህር ዳር ሳጥን መድረስ ቀሏቸው ታይቷል። ባለሜዳዎቹ 24ኛው ደቂቃ ላይ እያሱ ታምሩ በረጅሙ የተላከለትን ኳስ ከግራ ወደ ቀኙ የሜዳ ክፍል አሻግሮለት ካሉሻ ለአቡበከር ጥሩ ኳስ ሲያሳልፍለት አቡበከር ከሳጥን ውስጥ ያደረገው ሙከራ ወደ ውጪ ቢወጣም ከዚህ በኋላ ያገኟቸውን ዕድሎች በመጠቀሙ ግን አልሰነፉም።

29ኛው ደቂቃ ላይ ከአስናቀ ሞገስ የቀሙት ኳስ ሁሴን ሻባኒ ለአቡበከር አድርሶት ከሀሪሰን ፊት ብቻቸውን መግባት የቻሉት ቡናዎች አቡበከር ጨርሶ ያሳለፈለትን ኳስ እያሱ በቀላሉ አስቆጥሮ መሪነቱን አስፍቷል። 41ኛው ደቂቃ ላይም እንዲሁ ከደረጄ መንግስቱ ካስጣሉት ኳስ አስራት ቱንጆ ለፊት አጥቂው ሻባኒ አድርሶት ሻባኒ ወደ ግብነት መቀየር ችሏል። በተመሳሳይ ሁኔታ ቡድኑ 40ኛው ደቂቃ ላይ ከተቀማ ኳስ ሌላ የግብ ዕድል ሲፈጥር ካሉሻ አልሀሰን ብቻውን ይዞ ገብቶ ስቷል። የጨዋታ አቀራረባቸው በማጥቃት ላይ የተመሰረተ ቢሆንም ለመልሶ ማጥቃት በቀላሉ ተጋልጠው የታዩት ባህር ዳሮች የመስመር አጥቂያቸውን ዜናው ፈረደን በግርማ ዲሳሳ ቀይረው ቢያስወጡም ከወሰኑ ዓሊ 29ኛ ደቂቃ የርቀት ሙከራ እና ወደ መጨረሻ ላይ ካገኟቸው የማዕዘን ምቶች ውጪ ማገገም ሳይችሉ አጋማሹ ተተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር እንደመጀመሪያው ሁሉ ባህር ዳሮች ተነቃቅተው ታይተዋል። የቆሙ ኳሶችን ከማግኘታቸው ባለፈም ወንድወሰን አሸናፊን ማስጨነቅ ያልቻሉ ሙከራዎችን በወሰኑ ዓሉ እና ግርማ በቀለ አማካይነት ማድረግ ችለው ነበር። ሆኖም በመጀመሪያው አጋማሽ ከፍተኛ ብልጫ እንዲወሰድባቸው ያደረገውን ወደ መሀል ሜዳ ያለቅጥ የተጠጋ የመከላከል መንገዳቸውን አለማስተካከላቸው አሁንም ግቦች እንዲቆጠሩባቸው አድርጓቸዋል። ይህን በመረዳት ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ያፈገፈጉ የመሰሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች ራሳቸውን ለመልሶ ማጥቃት ዝግጁ ማድረጋቸውን አልዘነጉም። 55ኛው ደቂቃ ላይም የባህር ዳር ከተማ የተከላካይ ክፍል ገና ወደ መሀል ሜዳ በመጠጋት ላይ ሳለ ካሉሻ አልሀሰንን ቀይሮ የገባው ፍፁም ጥላሁን በግሩም ሁኔታ ያሳለፈለትን ኳስ አቡበከር ነስሩ በአስደናቂ አጨራረስ በሀሪሰን አናት ላይ ኳስን ከፍ በማድረግ አራተኛ ግብ አድርጎታል።

ጃኮ አራፋት እና ዳግማዊ አባይን በማስገባት የማጥቃት ኃይላቸውን ጨምረው አሁንም ወደ ፊት ለመጫወት ጥረታቸውን የቀጠሉት ባህር ዳሮች በተሻለ ሁኔታ አስፍተው በመጫወት በተሻጋሪ ኮሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ቢሞክሩም እምብዛም ውጣታማ አልሆኑም። ቡድኑ በሁለት አጋጣሚዎች ኳስ እና መረብን ቢያገናኝም ግቦቹ ከጨዋታ ውጪ ሆነው ልዩነቱን ማጥበብ ሳይችሉ ቀርተዋል። 66ኛው ደቂቃ ላይ ግርማ በቀለ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ደግሞ ወሰኑ ዓሊ በግንባር ሞክሮ ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል። በባህር ዳር የተሻለ ሙከራም 75ኛው ደቂቃ ላይ ዳንኤል ኃይሉ ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ አሌክስ አሙዙ በግንባሩ ሞክሮ የግቡ አግዳሚ መልሶበታል። ጨዋታው በዚህ መልኩ ቀጥሎም 73ኛው ደቂቃ ላይ ሌላ ክስተት አስመልክቶናል። አቡበከር ናስር እና ሣለአምላክ ተገኝ ለፀብ መጋበዛቸውን ተከትሎ የአሸብር ሰቦቃ የቀይ ካርድ ሰለባ ሆነዋል። አርቢትሩ ከሁለት ሳምንት በፊት በመከላከያ እና ደደቢት ጨዋታም በተመሳሳይ አበበ ጥላሁን እና ኑሁ ፉሰይኒን ከሜዳ ማስወጣታቸው ይታወሳል።

የተጋጣሚያቸው አቀራረብ በቀላሉ በመልሶ ማጥቃት ሰብሮ ለመግባት እንዲመቻቸው ያደረገው ቡናዎች በፍፁም ጥላሁን ሌላ ግልፅ የግብ አጋጣሚ አግኘተው መጠቀም ባይችሉም የቀድሞው ግብ ጠባቂያቸው ሐሪሰን ስህተት ግን የአምስተኛ ግብ በረከትን አምጥቶላቸዋል። በረጅሙ የተሻገርን ኳስ ከግብ ክልሉ ወጥቶ የተቆጣጠረው ሐሪሰን ሁለት ተጫዋቾችን አልፎ ለዳንኤል ኃይሉ በጠንካራ ምት ሲያቀብል አማካዩ መቆጣጠር ሳይችል ቀርቶ ሀሰን ሻባን ግብጠባቂው ወደ ቦታው ከመመለሱ በፊት መትቶ አምስተኛውን ግብ አስቆጥሯል። ከቀይ ካርዶቹ በኋላ በመጀመሪያው ግለቱ ያልቀጠለው ጨዋታም በቡናማዎቹ ፍፁም የበላይነት በ 5-0 ውጤት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎም ኢትዮጵያ ቡና የዛሬው ተጋጣሚውን የ6ኛ ደረጃ ሲረከብ ባህር ዳር ደግሞ በቡና በግብ ልዩነት ተበልጦ 7ኛ ሆኗል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡