በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ሎዛ ለብቻዋ 9 ግቦች አስቆጥራለች

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ማእከላዊ ዞን የ3ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ተጀምረዋል፡፡ ደደቢት በአሸናፊነቱ ሲቀጥል ቅዱስ ጊዮርጊስም ድል ቀንቶታል፡፡

በ9፡00 እቴጌን የገጠመው ደደቢት 13-1 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፎ መሪነቱን አጠናክሯል፡፡ የደደቢት የመክፈቻ ግብ የተገኘው ገና በ50ኛው ሴኮንድ በመስከረም ኮንካ አማካኝነት ነበር፡፡ ከተቆጠሩት 13 ግቦች ሎዛ አበራ 9ኙን ስታስቆጥር ሰናይት ባሩዳ ፣ ውባለም ፀጋዬ ፣ ትበይን መስፍን እና መስከረም ኮንካ ቀሪዎቹን ግቦች ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

ደደቢት የዛሬውን ድል ተከትሎ የዞኑን መሪነት ከ3 ጨዋታ 9 ነጥብ በመሰብሰብ ከአናት ላይ ተቀምጧል፡፡ 9 ግብ ያስቆጠረችው ሎዛ አበራም በ3 ጨዋታ ብቻ ያስቆጠረችው ግብ ብዛት 12 ደርሷል፡፡ ተሸናፊው እቴጌ በ3 ጨዋታ 1 ግብ አስቆጥሮ 24 ግቦች አስተናግዷል፡፡

በ11፡00 ሙገርን የገጠመው ቅዱስ ጊዮርጊስ ድል ቀንቶታል፡፡ በክረምቱ ዳሽን ቢራን ለቃ ቅዱስ ጊዮርጊስን የተቀላቀለችው ሔለን ሰይፉ ብምት ከ35 ሜትር ርቀት በግሩም ሁኔታ ያስቆጠረችው ግብ ቅዱስ ጊዮርጊስን ለድል አብቅቶታል፡፡

2ኛ ሳምንት ጨዋታ ያለፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁለቱንም ጨዋታ አሸንፎ 6 ነጥቦች ሲይዝ የመጀመርያው ሳምንትን ያረፈው ሙገር ሲሚንቶ በሁለቱም ጨዋታ ተሸንፏል፡፡

ሊጉን ደደቢት በ9 ነጥቦች ሲመራ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና መከላከያ በ6 ነጥቦች ይከተላሉ፡፡ ማክሰኞ ጨዋታቸውን የሚያደርጉት ንግድ ባንክ እና ቅድስት ማርያም 3 ነጥቦች ይዘው ተከታዮቹን ደረጃ ይዘዋል፡፡

የከፍተኛ ግብ አግቢነቱን ሎዛ አበራ በ12 ግቦች ስትመራ የቅዱስ ጊዮርጊሷ ሔለን ሰይፉ እና የቅድስተ ማርያሟ መዲና አወል በ5 ግቦች ይከተላሉ፡፡

 

ቀጣይ 3ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ማክሰኞ እና ሀሙስ ይደረጋሉ፡፡ በዚህም መሰረት፡-

ማክሰኞ ህዳር 28 ቀን 2008

9፡00 – ቅድስተ ማርያም ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ (አበበ ቢቂላ ስታድየም)

11፡00 – መከላከያ ከ ኤሌክትሪክ (አበበ ቢቂላ ስታድየም)

 

ሀሙስ ህዳር 30 ቀን 2008

09፡00 – ዳሽን ቢራ ከ ኢትዮጵያ ቡና (ጎንደር)

የኢትዮጵያ ሴቶች የደቡብ/ምስራቅ ዞን ታህሳስ 3 እንደሚጀመር ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡

 

ያጋሩ