የ21ኛው ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ሲደረግ ፋሲል ከነማ በአራት ግቦች መከላከያን ጣር ውስጥ በመክተት ድል አድርጎ ደረጃውን አሻሽሏል።
በጨዋታው መከላከያ ወደ መቐለ ተጉዞ በወልዋሎ ከተሸነፈበት ጨዋታ በአማኑኤል ተሾመ እና ፍቃዱ ደነቀ ቦታ ዳዊት እስጢፋኖስ እና ፍፁም ገብረማርያምን ተጠቅሟል። ከደቡብ ፖሊስ ነጥብ የተጋሩት ፋሲሎች በበኩላቸው ጉዳት የገጠመው ተከላካያቸው ያሬድ ባየህን ቦታ በአጥቂነት በሚጠቀሙት ሙጂብ ቃሲም የተኩ ሲሆን በሌሎች ለውጦች ጀማል ጣሰው እና ሽመክት ጉግሳ በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ሳይካተቱ ሚካል ሳማኬ ፣ ሰዒድ ሁሴን እና ኤፍሬም አለሙ ወደ ሜዳ ገብተዋል።
ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ የጀመረው ጨዋታ ብዙም ሳይዘልቅ ነበር ግብ ያስተናገደው። ፋሲሎች በግራ በኩል ከእጅ ውርወራ የተነሳውን ኳስ ይዘው ሳጥን ውስጥ ከገቡ በኋላ የተለመደውን የመከላከያ የተከላካይ ክፍል መከፈትን በመጠቀም ሰለሞን ሀብቴ ያሳለፈለትን ኳስ ኤፍሬም አለሙ የመጀመሪያ ግብ አድርጎታል። ኳስ ይዘው ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት መከላከያዎች ግቡ ከፈጠረባቸው አለመረጋጋት ጋር ተዳምሮ የሜዳውን አጋማሽ ካለፉ በኋላ ሰብረው መግባት ሲቸግሯቸው ታይተዋል። በሂደት መሻሻልን እያሳዩ ቢመጡም በብዛት በዳዊት እስጡፋኖስ እና ፍሬው ሰለሞን ቅብብሎች ላይ ተመስረተው ወደ ፋሲል ሳጥን ለመግባት የሚያደርጉት ጥረት ለፊት አጥቂያቸው ፍፀም ገብረማርያም የግብ ዕድሎችን የሚፈጥር አልሆነም። ቡድኑ አልፎ አልፎ ከጨዋታ እና ከቆሙ ኳሶች ወደ ውስጥ የሚሻግራቸው ኳሶችም የፋሲልን የኋላ ክፍል የሚፈትኑ አልነበሩም።
በጊዜ መሪነቱን ያገኙት ፋሲል ከነማዎች በአመዛኙ ተረጋግተው በራሳቸው ሜዳ ላይ ይታዩ የነበረ ሲሆን በቀላሉ የተጋጣሚያቸውን ቅብብሎች ማቋረጥም አልከበዳቸውም። ሆኖም የሚገኙትን የመልሶ ማጥቃት ቅፅበቶች መጠቀም ላይ ተቀዛቅዘው ታይተዋል። ይህ በመሆኑም ጨዋታው ለረጅም ደቂቃዎች ያለሙከራ የቀጠለ ሲሆን 30ኛው ደቂቃ ላይ ግን እንግዶቹ እጅግ አስደናቂ ጎል አስቆጥረዋል። መሀል ሜዳ ላይ ከዳዊት እስጢፋኖስ ኳስ ያስጣለው ሱራፌል ዳኛቸው ወደ ግራ መስመር ካመራ በኋላ በረጅሙ ወደ ሳጥን ያሻገረውን ለማመን የሚከብድ ኳስ እዙ አዙካ በግንባሩ ወደ ግብነት ቀይሮታል። በቀሪዎቹ ደቂቃዎች የተሻለ ጫና የፈጠሩት መከላከያዎች ወደ ፋሲል ሳጥን የመግባት አጋጣሚዎችን ቢያገኙም ተመስገን ገብረኪዳን እና በኃይሉ ግርማ ያደረጓቸው ሙከራዎች በሚካል ሳማኬ በቀላሉ ድነዋል።
ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር ፍቅዱ ደነቀን በተመስገን ገብረኪዳን ለውጠው ያስገቡት መከላከያዎች የተነቃቁ መስለው ነበር። ነገር ግን ፍሬው ሰለሞን ከሳጥ ውጪ ካደረጋት ጠንካራ ሙከራ በኋላ ምንም ያህል ሳይቆየ ሦስተኛ ግብ ተቆጥሮባቸዋል ። 48ኛው ደቂቃ ላይ ፋሲሎች የገኙትን የማዕዘን ምት በቅብብል አስጀምረው ሱራፌል ዳኛቸው ወደ ውስጥ ሲያሻማ ዓለምነህ ግርማ የነካው ኳስ መረብ ላይ አርፏል። ጨዋታውን በሰፊ ጎል መምራታቸውን የቀጠሉት ፋሲሎች እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ኳስ ይዘው ከመቆየት ይልቅ በተረጋጋ ሁኔታ ከተጋጣሚያቸው ከሚያስጥሏቸው ኳሶች መነሻነት ጥቃቶችን መሰንዘር ምርጫቸው አድርገዋል። በተቃራኒው በአመዛኙ የኳስ ቁጥጥሩን የያዙት መከላከያዎች በተሻለ ሁኔታ ወደ ግብ የቀረቡባቸው አጋጣሚዎች ቢታዩም ግብ ማስቆጠር ግን አልቻሉም።
ተጨማሪ ቅያሪዎችን በማድረግ ሳሙኤል ታዬ እና ዳዊት ማሞን ያስገቡት ባለሜዳዎቹ በፍቃዱ ደነቀ ከሳጥን ውጪ ያደረጉት እና እንዲሁም በፍፁም 67ኛው ደቂቃ ላይ ከግቡ አፋፍ ደርሰው የሞከሯቸው ኳሶች በሳማኬ ተይዘውባቸዋል። በጥቂት ቅብብሎች ወደ ግብ መድረስ ቀሏቸው የነበሩት ፋሲሎች በበኩላቸው የተመቹ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ቢያገኙም ወደ ግብነት መቀየር ሳይችሉ ቆይተዋል። በተለይም 74ኛው ደቂቃ ላይ ከሱራፌል ወደ ኢዙ በተላካ ረጅም ኳስ እንዲሁም ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ኤፍሬም አለሙ ከራሱ ሜዳ ጀምሮ ተከላካዮችን እያለፈ ሳጥን ደረስ መግባት በቻለበት አጋጣሞዎች በቀላሉ ጎል ሊሆኑ ይችሉ ነበር። ነገር ግን ቡድኑ ኤፍሬም 79ኛው ደቂቃ በተከላካዮች መሀል ባሾለከለት እና ኢዙ አዙካ ግብ ጠባቂውን ጭምር አልፎ ባስቆጠራት ግብ የጎል ልዩነቱን አራት ማድረስ ችሏል። በቀሩት ደቂቃዎች ውጤቱን ለማጥበብ የሞከሩት መከላከያዎች መጨረሻ ደቂቃ ላይ የሳሙኤል ታዬ ጠንካራ የርቀት መከራ በሳማኬ ከመመለሱ ውጪ ላይ ዕድል ሳይፈጥሩ ጨዋታው ተጠናቋል።
በውጤቱም ለአምስተኛ ጊዜ በጨዋታ ከሦስት ጎሎች በላይ ለማስተናገድ የተገደደው መከላከያ በወራጅ ቀጣና ውስጥ ሲቀር ፋሲል ከነማ ሲዳማ ቡናን በግብ ልዩነቶች በመብለጥ ወደ ሁለተኛነት ከፍ ብሏል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡