ሪፖርት | የያሬድ ከበደ የመጨረሻ ደቂቃ ግብ ምዓም አናብስትን ወደ ድል መልሳለች

በ21ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መሪው መቐለ 70 እንደርታ በሜዳው አዳማ ከተማን 2-1 በማሸነፍ የነጥብ ልዩነቱን አስጠብቋል።

ከጨዋታው መጀመር በፊት የመቐለ ደጋፊ ማኅበር ለአዳማ አቻቸው እንዲሁም ለቀድሞ የቡድኑ ተጫዋቾች ዐመለ ሚልኪያስ እና ዱላ ሙላቱ ስጦታ እና የምስጋና ወረቀት አበርክተዋል።

መቐለዎች ባለፈው ሳምንት በባህርዳር ሽንፈት ከገጠመው ቡድናቸው ቢያድግልኝ ኤልያስ ፣ ጋብርኤል አህመድ እና ሄኖክ ኢሳይያስን በማስወጣት በሥዩም ተስፈዬ ፣ አንተነህ ገብረክርስቶስ እና ዮናስ ገረመው ተክተው ሲገቡ አዳማዎች በበኩላቸው በሃዋሳ ሽንፈት ከገጠመው ቡድናቸው ሱሌይማን መሐመድ እና ከነዓን ማርክነህን በቡልቻ ሹራ እና ሱራኤል ዳንኤል ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ባለፈው ሳምንት ወደ የመን ለማቅናት በባህር ላይ ሰምጠው ሂወታቸው ላጡት ኢትዮጵያውያን በተደረገው የህሊና ፀሎት የጀመረው ጨዋታው አዝናኝ እና የባለሜዳዎቹ ብልጫ የታየበት ነበር። ጎሉ እስከተቆጠረበት ደቂቃ ድረስ ይህ ነው የሚባል ወደ ግብ የቀረበ ሙከራ ያልታየበት ጨዋታው ግብ ለማስተናገድ ብዙ ደቂቃ አልፈጀበትም። በአስራ አንደኛው ደቂቃ ላይ ምኞት ደበበ በኦሴይ ማውሊ ላይ በሰራው ጥፋት የተገኝችው ፍፁም ቅጣት ምት አማኑኤል ገብረሚካኤል አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።

በጨዋታው በኳስ ቁጥጥር ብልጫ የተሻሉ የነበሩት እና ባለፉት ሳምንታት ከተከተሉት ተገማች የጨዋታ አቀራረብ ለውጥ አድርገው የተመለሱት ምዓም አናብስት ምንም እንኳ የምኞት እና የተስፋዬን ጠጣር ጥምረት አልፈው በርካታ ንፁህ ዕድሎች ባይፈጥሩም በሶስት አጋጣሚዎች ከቆመ ኳስ መሪነታቸው የሚያሰፉበት ዕድል አግኝተው ነበር። በተለይም ኦሴይ ማውሊ ሚካኤል ደስታ ከመዓዝን ያሻማው ኳስ ተጠቅሞ በግንባር ያደረገው ሙከራ እና ያሬድ ከበደ በተመሳሳይ ከማዕዝን የተሻማው ኳስ ተጠቅሞ ያደረገው ሙከራ የባለሜዳዎቹም መሪነት ከፍ ለማድረግ የተቃረቡ ሙከራዎች ናቸው።

ጨዋታውን በተቀዛቀዘ ስሜት ጀምረው የመጨረሻዎቹን ደቂቃዎች ጫና ፈጥረው የተጫወቱት አዳማዎች ጫና በፈጠሩባቸው ደቂቃዎች በርካታ ዕድሎች ፈጥረዋል። ቡልቻ ሹራ በሁለት አጋጣሚዎች በድንቅ ሁኔታ ከርቀት መትቶ የሞከራቸው ሙከራዎች በፍሊፕ ኦቮኖ ባይመክኑ ኖሮ አዳማዎችን አቻ የማድረግ ዕድልም ነበራቸው። አዳማዎች ከነዚህ ሁለት ወርቃማ ሙከራዎች ውጭም በበረከት ደስታ እና ሱሌይማን ሰሚድ አማካኝነት ሌሎች ሁለት ሙከራዎች ማድረግ ችለው ነበር።

ጥቂት የግብ ሙከራዎች እና ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ ተመጣጣኝ ፉክክር በታየበት ሁለተኛ አጋማሽ ሙከራ ለማድረግ ቀዳሚ የነበሩት እንግዶቹ ናቸው። ሱራፌል ዳንኤል ከቅጣት ምት ያሻማትን ኳስ ምኞት ደበበ ገጭቶ ባደረጋት ሙከራ ጥቃታቸው የጀመሩት እንግዶቹ ከዕረፍት መልስ በነበሩት የመጀመርያ አምስት ደቂቃዎች ጫና ፈጥረዉ ቢጫወቱም ጫናው ከነዛ ደቂቃዎች ያለፈ አልነበረም።

በአንፃሩ ከመጀመርያው አጋማሽ በተሻለ ወደ ተቃራኒ ግብ ክልል ቶሎ ቶሎ መድረስ የቻሉት መቐለዎች በኦሴይ ማውሊ አማካኝነት ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርገው ነበር። አጥቂው ከአማኑኤል የተላከለትን ኳስ ከተከላካዮች መሃል ሾልኮ ከግብ ጠባቂው ጋር ቢገናኝም ኳስና መረብ ማገናኘት አልቻለም።

በሰባ ሁለተኛው ደቂቃ ላይ ቢጫ ካርድ ካየ ሁለት ደቂቃዎች ብቻ ያስቆጠረው ሱሌይማን ሰሚድ በአማኑኤል ገብረሚካኤል ላይ በሰራው ጥፋት በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። ሱሌይማን በዘንድሮው የውድድር ዓመት ለሁለተኛ ጊዜ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል።

በጎዶሎ ለመጫወት የተገደዱት አዳማዎች ቀይ ካርዱ ከታየበት ደቂቃ በኃላ ብዙም ሳይቆዩ አቻ መሆን ችለዋል። ከመስመር የተሻገረችው ኳስ ምኞት ደበበ በጭንቅላቱ ሲጨርፋት ከጎሉ ጠርዝ ነፃ የነበረው አዲስ ህንፃ አስቆጥሯት ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኃላ ያፈገፈገውን የአዳማ አጨዋወት ተጠቅመው ወደ ተጋጣሚ ሜዳ ተጠግተው የተጫወቱት መቐለዎች በርካታ ዕድሎች ፈጥረው ነበር። በተለይም ኦሴይ ማውሊ በሁለት አጋጣሚዎች በደካማ ውሳኔ አሰጣጥ ችግር ያመከናቸው ዕድሎች ባለሜዳዎቹን መሪ ለማድረግ የተቃረቡ ሙከራዎች ነበሩ። ሆኖም በ88ኛው ደቂቃ ላይ ኦሴይ ማውሊ ከዮናስ ገረመው የተላከለትን ኳስ ወደ ሳጥን አሻግሮት ከግቡ ቅርብ ቦታ ላይ የነበረው ያሬድ ከበደ አስቆጥሮ የማታ ማታ ደጋፊዎችን ጮቤ አስረግጧል።

ውጤቱን ተከትሎ አዳማዎች ተከታታይ ሽንፈታቸው ሲያስመዘግቡ ምዓም አናብስት ደግሞ ከተከታዮቻቸው ጋር ያላቸውን ርቀት ማስጠበቅ ችለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡