የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 15ኛ ሳምንት የምድብ ሐ ጨዋታዎች ቅዳሜ እና እሁድ ተደርገው መሪው ሀዲያ ሆሳዕና እና ተከታዩ አርባምንጭ ከተማ አሸንፈዋል።
ሆሳዕና ላይ ሀዲያ ሆሳዕና ከሻሸመኔ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረ ጎል በባለሜዳዎቹ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። በውድድር ዓመቱ አጋማሽ ከአዳማ ወደ ሆሳዕና ያመራው ሱራፌል ጌታቸው ወሳኟን የድል ጎል በ88ኛው ደቂቃ በማስቆጠር ሆሳዕና ልዩነቱን አስጠብቆ በመሪነት እንዲቀጥል አድርጎታል።
አርባምንጭ ከተማ በሜዳው ስልጤ ወራቤን አስተናግዶ 1-0 አሸንፏል። የመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች በጣም የተቀዛቀዘና ብዙም ማራኪ እንቅስቃሴ ያልታየበት የነበረ ሲሆን አርባምንጮች የሦስት ጨዋታ ቅጣት የተጣለበት ቴዲ ታደሰን ማጣታቸው የመሀል ሜዳውን ክፍል ሚዛን አሳጥቶባቸዋል። በስልጤ ወራቤዎች በኩል አርባምንጭ ከተማን ለመግጠም ከመጣው ስብስብ ውስጥ አራት የሚሆኑት የቀድሞ ክለባቸውን የገጠሙ ሲሆን ለአርባምንጭ ከተማዎችም እንቅስቃሴ መዳከም የድርሻቸውን ሲያበረክቱ ታይተዋል።
በጨዋታው እንቅስቃሴ የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ስንታየው መንግስቱ የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ለወራቤ ተከላካዮች ፈታኝ ነበር። በርካታ ሙከራዎች የታዩበት ቢሆንም ኢላማቸውን የጠበቁት ግን ሁለት ሙከራዎች ብቻ ነበሩ። እነዚህንም ሙከራዎች አጥቂው ስንታየሁ መንግስቱ የሞከራቸው ሲሆኑ በስልጤ ወራቤ በኩል ደግሞ መልካሙ ፉንድሬ በግምት 20 ሜትር ገደማ ላይ የተሰጠውን የቅጣት ምት ሞክሮ የግብ አግዳሚ የመለሰበት ተጠቃሽ ናቸው። አርባምንጮች ስንታየሁ መንግስቱ በ24ኛው ደቂቃ ላይ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ የስልጤ ወራቤን ተከላካዮች አታሎ ባስቆጠራት ግብ ጨዋታው አሸንፈው ለመውጣት ችለዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ክለቦች ተጫዋቾችን ቀይረው ቢጠቀሙም የረባ እንቅስቃሴና ሙከራ ሳይደረግበት ጨዋታው በአርባምንጭ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። (በፋሪስ ንጉሴ)
በጅማ ስታድየም ላይ ጅማ አባቡና ከካፋ ቡና ያደረጉት ጨዋታ 2-2 ተጠናቋል። ካፋ ቡናን ለመደገፍ ከቦንጋ ወደ ጅማ ተጉዘው የመጡ ደጋፊዎች ከባለሜዳው ደጋፊዎች ጋር ተቀላቅለው መቀመጣቸው ተቀላቅለው መቀመጣቸው ተገቢ እንዳልሆነ የአባቡና ደጋፊ ተወካዮች ለእለቱ ኮሚሽነርና ለዋና ዳኛ ቅሬታቸው ቢያቀርቡም ደጋፊዎችን ለመለየት የተደረገው ጥረት ባለመሳካቱ የእለቱ ጨዋታ መጀመር ከነበረበት አርባ ደቂቃዎችን ዘግይቶ እንዲጀምር ተደርጓል።
በመጀመሪያው አጋማሽ በ9ኛው ደቂቃ ምስጋናው መኮንን ለአባቡናዎች ቀዳሚ ያደረገች ግብ ቢያስቆጥርም በ33ኛው ደቂቃ ኦኒ ኡጁሉ የካፋ ቡናን የአቻነት ግብ አስቆጥሮ የመጀመሪያው አጋማሽ 1-1 ተጠናቋል። ከእረፍት መልስ ተቀይሮ የገባው አድማሱ ጌትነት በ58ኛው ደቂቃ ካፋ ቡናን ወደ መሪነት ሲያሸጋግር በ64ኛው ደቂቃ በደጋፊዎች መካከል በተነሳ ግጭት ጨዋታው ለ20 ደቂቃዎች ከተቋረጠ በኋላ በድጋሚ ቀጥሎ በ71ኛው ደቂቃ ካርሎስ ዳምጠው አባ ቡናን አቻ በማድረግ ጨዋታው 2-2 አቻ ተጠናቋል፡፡ (በቴዎድሮስ ታደሰ)
ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ በሜዳው በቡታጅራ 2-1 ሽንፈት አስተናግዷል። አወዛጋቢ የዳኝነት ውሳኔ በታየበት ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ የተንቀሳቀሱት ባለሜዳዎቹ ግብ በማግባት ደረጃ ቀዳሚ ነበሩ። 7ኛው ደቂቃ ላይ ማንደፍሮ ከማዕዘን የተሻማን ኳስ በተከላካይ ተገጭቶ ሲመለስ ወደግብ በመቀየር መሪ መሆን ችለዋል። በድጋሚ 17ኛው ላይ ከግራ መስመር ከመግቢያነህ አሳየ የተሻገረለትን ኳስ ሳጥን ውስጥ ፍቃዱ ባርባ በቀጥታ ወደ ግቡ መትቶ ግብጠባቂ ያዳነበት በባለሜዳዎቹ በኩል የሚጠቀስ ነበር።
በተደጋጋሚ በመስመር የማጥቃት እንቅስቃሴ የነበሩት ጥሩ የነበሩት ቢሾፍቱዎች 19ኛደቂቃ ላይ ከግራ መስመር ከሚሊዮን ሁለት ተከላካዮች አልፎ ይዞት የመጣውን ኳስ ለጫላ ከበደ አሻግሮለት ጫላ ከሳጥን ጠርዝ ወደግብ አክርሮ ቢመታውም የግቡን አግዳሚ ታኮ የወጣበት ሌላው የሚጠቀስ ሙከራ ነበር።
በቡታጅራ ከተማ በኩል ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የተሸላ መነቃቃትን ያሰዩ ሲሆን 18ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት የተገኝውን ኳስ ጀማል በይሸ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት ሲቀር 42ኛ ደቂቃ ላይ ቢሸፍቱ ተከላካዮች አለመግባባት የተገኘውን ኳስ ክንዴ አቡቹ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ወደግብ በመቀየር ቡታጅራን አቻ በማድረግ ወደ እረፍት አምርተዋል።
እረፍት ሰዓት ላይ የተወሰኑ የቡታጅራ ደጋፊዎች ሜዳ መግባታቸውን ተከትሎ የጨዋታው የመሀል ዳኛ ሃይሌ ኪዳኔ እና ረዳቶቹ ለደህነንነታችን አስጊ በመሆኑ የፀጥታ ኃይል ሳይመጣ ጨዋታውን አንቀጥልም በማለት ከ1 ሰዓት በላይ ቆይቶ ሁለተኛው አጋማሽ ሲል ደግሞ የቡታጅራ ተጫዋቾች ወደሜዳ አንገባም በማለት የተወሰኑ ደቂቃዎች ከወሰዱ በኋላ ነበር ጨዋታው የተጀመረው ።
ከረጅም እረፍት በኋላ ወደ ሜዳ የገቡት ሁለቱ ቡድኖች የተጋጋለ እና ግጭት የበዛበት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ጨዋታው ሊገባደድ የተወሰኑ ደቂቃዎች ሲቀሩ ከማዕዘን የተሻገረለትን ኳስ ክንዴ አቡቹ በጭንቅላት በመግጨት ወደ ግብ ቀይሮ ቡታጅራን መሪ ማድረግ ችሏል።
በባለሜዳዎቹ በኩል ተጭነው ቢጫወቱም ስኬታማ መሆን አልቻሉም። በሙከራ ደረጃ 79ኛ ላይ ተቀይሮ የገባው ኢሳይያስ ዓለምሸት ወደግብ አክርሮ የመታው ኳስ ቋሚ የመለሰበት የሚጠቀስ ነበር። (በኤልያስ ኢብራሂም)
በሌሎች ጨዋታዎች ወደ ሺንሺቾ ያመራው ቤንች ማጂ ቡና 2-1 አሸንፎ ሲመለስ ቅዳሜ ዕለት በተደረገ በረቸኛ ጨዋታ ነቀምት ከተማ በሜዳው ነገሌ ቦረናን 3-0 አሸንፏል። ዳንኤል ዳዊት በ10ኛው እና በ36ኛው ደቂቃዎች ሁለት ጎሎች ሲያስቆጥር ገመችስ አማኑኤል ቀሪዋን ጎል አስቆጥሯል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡