እግር ኳስ በመላው ዓለም ካለው ተወዳጅነት ባለፈ ከሜዳ ውጪ ባሉ ማኅበራዊ ትስስር ላይም የራሱን የሆነ በጎ አስተዋፅኦ ሲያበረክት ይታያል። በቅርብ ዓመታት ደግሞ ከስፖርትነት ባለፈ ሀገራትን በኢኮኖሚውም ዘርፍ የመደገፍ አቅም እንዳለው በሚገባ እያሳየ የሚገኘው ተወዳጁ ስፖርት ለብዙዎች የደስታ ምንጭ ሆኖ እስካሁን ዘልቋል።
ከ1920ዎቹ ጀምሮ ወደ ሀገራችን ከገባ ጊዜ አንስቶም ዘመናዊዎቹን ትሩፋቶቹን ሳያሳየን በተለያዩ ችግሮች ታንቆ የንፉቅቅ ለመሄድ ቢገደድም እስካሁንም ድረስ ስሜትን መግዛቱ እና የትኩረት ምንጭ መሆኑን ቀጥሏል። ነገር ግን በሚፈለገው መጠን ውጤታማ አለመሆኑ ካለበት ጥልቅ የአስተዳደራዊ ችግር ባለፈም በተለያዩ ዘመናት በሀገራችን የነበሩ ፖለቲካዊ ጉዳዮች እንደየጊዜው የየራሳቸውን ፈተና ሲሰጡት ኖረዋል። አሁንም እየሆነ ያለው ይህ ነው። በአጠቃላይ በእግር ኳሳችን በተለይም ደግሞ በሊጎቻችን የየሳምንቱ መርሀ ግብሮች ላይ የወቅቱ ፖለቲካዊ ንዝረት ውጤት የሆኑ አሳዛኝ ድርጊቶችን መመልከት እየለመድነው ብሎም ተቀብለነው ያለነው ጉዳይ ሆኗል።
መቼም አሁን ያለንበት ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ ተከትሎ እንደህዝብ በመካከላችን የፈተጠረውን ልዩነት መካድ አይቻልም። ከዚህ ባለፈም በየሳምንቱ ቁጥሩ ከፍ ያለ ተመልካችን በአንድ ቦታ ላይ የመሰብሰብ ምክንያት የሆነው እግር ኳሳችንም የእነዚህ ልዩነታችን ማሳያ መሆኑ የአደባባይ ሀቅ ነው። አለፍ ሲል ደግሞ ለሁከት እና ግርግር እየዳረገን ስፖርትነቱን እስክንዘነጋ ድረስ ብዙ አስከፊ ጉዳቶችን ሲያስመለክተን ቆይቷል። እነዚህን ጉዳዮችን ሙሉ ለሙሉ ማስቀረት እና በጨዋታዎች ወቅት የሚታየውን ብሔር ዘመም ድባብ ማስቆም ባይቻል እንኳን የሚያስከትለውን ጥፋት ለመቆጣጠር መሞከር ደግሞ ከአስተዳዳሪው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የሚጠበቅ ነው። የችግሩ አሳሳቢነት እና ቀጣይነት ያለው መሆን ደግሞ ፌዴሬሽኑ በዘመቻ መልክ አንድ ጊዜ ትኩረት ሰጥቶት ከዛ በቸልተኝነት የሚዘነጋው ሳይሆን ከሳምንት ሳምንት በልዩ ንቃት ሊከታታለው የሚገባ ነው።
በዓመቱ መጀመሪያ አዲሱ የፌዴሬሽን አመራር ካለፈው ዓመት ሁነቶች በመነሳት የትግራይ እና የአማራ ክልል ክለቦች መካከል የነበረውን ችግር በማርገብ ጨዋታዎችን በሜዳቸው እንዲያከናውኑ ሲዋትት ነበር። በመጨረሻም ነገሮች ተስተካክለው ተስተካካይ ጨዋታዎችም ተደርገው በታሰበው መንገድ ክለቦቹ በየሜዳቸው መጫወታቸውን ማድረግ ቀጥለዋል። በመጀመሪያው ዙር ይህንን ማድረግ ሳይቻል ቀርቶ አዲስ አበባ ላይ የተከናወነው ብቸኛ ጨዋታ የሲዳማ ቡና እና የወላይታ ድቻ ጨዋታ ነበር። ውሳኔው ጨዋታውን ተከትሎ ሊመጣ ይችል የነበረውን ጥፋት ማስቀረቱ በሁለተኛውም ዙር ጨዋታውን አዲስ አበባ ስታድየም ላይ መደርጉ ቅሬታን የሚያስነሳ አይደለም። ነገር ግን ይህ የሆነበት ምክንያት እውነታ ግን መረሳት አልነበረበትም። በሲዳማ እና ወላይታ ህዝቦች መካከል አሁን ላይ ያለው መቃቃር ጨዋታው በመዲናዋ እንዲደረግ ማስገደዱ በፍፁም ሊረሳ እና ሊዘነጋ ባልተገባው ነበር።
ይህን ጉዳይ በተመለከተ የችግሩን ምንጭ መለየት ከባድ አልነበረም ፤ መፍትሄ የሆነውን የገለልተኛ ሜዳ ጨዋታ ፍቃድ መስጠትም ቀላል ነበር። ነገር ግን ልክ በዚሁ መጠን ሁለቱን ብሔሮች በአንድ ቦታ ሊያገናኙ የሚችሉ ሌሎች ጨዋታውዎች ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባ ነበር። ባሳለፍነው ሳምንት ወላይታ ድቻ ወደ ሀዋሳ ከተማ በመምጣት ከደቡብ ፖሊስ ያደርግ የነበረው ጨዋታም ከቀሪ መርሐ ግብሮች ብቸኛው ይህ ችግር ሊያጠቃው የሚችለው ጨዋታ መሆኑ ብዙ መመራመርን አይጠይቅም። ታድያ ለዓመታት በፌዴሬሽን አመራሮቻችን ሲታይ የነበረው ቸልተኝነት እና የጀመሩትን ስራ በሁሉም ረገድ ያለመጨረስ ችግር አሁንም በመደገሙ ቡድናቸውን ተከትሎው በመጡ የወላይታ ድቻ ደጋፊዎች ላይ ከዕለቱ ጨዋታም ሆነ ከእግር ኳስ ጋር ተዛማችነት የሌለው ጥቃት ተፈፅሞባቸው እንድንመለከት አድርጎናል። ይህ እጅግ የሚያሳዝን እና መጪውን ጊዜም በስጋት እንድንመለከት የሚያደርገን ክስተት ነው።
በጣም የሚያሳዝነው ጉዳይ ደግሞ የሊግ አመራሩ ጉዳዩን ዘንግቶት ለጨዋታው ልዩ ትኩረት ሳይሰጥ እንዳያልፍ የወላይታ ድቻ እግር ኳስ ክለብ 07/08/2011 ጨዋታው በገለልተኛ ሜዳ ይደረግልኝ ሲል በደብዳቤ መጠየቁ ሊያነቃው ይገባ የነበረ መሆኑ ነው። የክለቡን ሀሳብ ያልተቀበለው ኮሚቴው ግን ሐሙስ ዕለት ጨዋታው በወጣለት መርሀ ግብር በዕለተ ቅዳሜ በሀዋሳ እንደሚካሄድ በደብዳቤ ምላሽ ሰጥቷል። በእርግጥ ይህን ማለቱ ኮሚቴውን አያስወቅሰውም። ነገር ግን ጨዋታው በቦታው እንዲካሄድ ሲወስን ከወትሮው እና ከሌሎች ጨዋታዎች የተለየ ትኩረት ማድረግ አለመቻሉ ትልቅ ጥፋት ነው። ለሁኔታው ልዩ ትኩረት በመስጠት የተጋጣሚ ቡድኖች እና ደጋፊዎችን ደህንነት ከአካባቢው የፀጥታ አካል ጋር በልዩ ሁኔታ መነጋገር እና ተግባራዊነቱን በጥብቅ በመከታተል ሠላማዊ የእግር ኳስ ጨዋታ እንድንመለከት ለማድረግ በቂ ጊዜም ነበረው። ይህ ሳይሆን በመቅረቱ ግን እየለመድነው የመጣነውን የደጋፊዎች አስቃቂ አካላዊ ጉዳት በድጋሚ እንድናይ ሆነናል። ቀጥሎም በማግስቱ ይደረግ የነበረው የሀዋሳ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታም ተላልፎ ከአካላዊው ጉዳት ባለፈ እንግዶቹ ቡድኖች ለኪሳራ ተዳርገው ሳምንቱ አልፏል።
ነገ በፌዴሬሽን አመራሮቹ የስኬት ዝርዝር ውስጥ ከላይ የሚቀመጠው የአማራ እና ትግራይ ክለቦችን ጉዳይን ፈር ለማስያዝ ሲደረግ የነበረው ሩጫ የዘመቻ መልክ ኖሮት ሌሎች ተመሳሳይ ችግሮችን በተመሳሳይ ዓይን ለማየት እንዳይቻል አድርጓል። በመሆኑም 21ኛው ሳምንት ላይ ስንደርስ የዚህን ቸልተኝነት ውጤት አሁንም በደም እና በአካል ጉዳት እንድንመለከት ምክንያት ሆኗል። በደጋፊዎች ላይ ለደረሰው አሳዛኝ ጉዳት እና ክለቦቹን ለፋይናንስ ክስረት በዳረገው ጉዳይ ተጠያቂው ማነው ? ጥቃቱን ያደረሱት አካላት በሕግ አግባብ ይጠየቁ ይሆናል። ጥፋቱ ሳይደርስ የእግር ኳሳዊ አስተዳድር ውሳኔዎችን ወስነው ከነጭራሹንም መጥፎውን አጋጣሚ ሊያስቀሩ ይችሉ የነበሩ አካላት ቸልተኝነትስ በምንድን ነው የሚዳኛው ? ከዚህ በኋላስ ትኩረት በማይሰጣቸው በየሳምንቱ አስፈሪ ድባቦች በሚያስተናግዱት የከፍተኛ እና የአንደኛ ሊግ ጨዋታዎች ላይስ ይህ ቸልተኝነት እስከምን የሚያደርስ ጥፋት ሊያስከትልብን ይችላል? እነዚህ ጥያቄዎች ችግሩ አስደንግጦት ስራዬ ብሎ የሚያጤነቸው አመራር ይፈልጋሉ።
ፕሪምየር ሊጉንም ሆነ ሌሎቹን ውድድሮች እያስተዳደረ የሚገኘው ፌዴሬሽኑ እስከሆነ ድረስ ሊጎችን በተመለከተ ከሚሰራቸው የዕለት ተዕለት ስራዎች በተጨማሪ ወቅቶች የሚያመጧቸውን ተጨማሪ የሰው ሀይል እና ትኩረት የሚያሻቸው ጉዳዮች ላይ ይበልጥ መትጋት ይኖርበታል። መሰል አካባቢያዊ ግጭቶች የሚያንዣብቡባቸው ጨዋታዎችን በሁሉም ሊጎች ለይቶ ከወትሮው በተለየ መልኩ ጥንቃቄን በተላበሰ ሁኔታ እንዲከናወኑ ማድረግ የግድ ይላል። ይህን ማድረግ ካልተቻለም በዝግ ስታድየም ወይንም በገለልተኛ ሜዳ እንዲከናወኑ ቀደም ብሎ በመወሰን የስፖርት ቤተሰቡን ከሁሉም ዓይነት ኪሳራዎች መከላከል ከአመራሮች ይጠበቃል። ክለቦች ጨዋታዎች እንዲተላለፉላቸው ወይንም የቦታ ለውጥ እንዲደረግላቸው ሲጠይቁም ጉዳያቸውን በተቃርኖ ከመመልከት ይልቅ በበሳል አመራር ግራ ቀኙን ተመልክቶ ውሳኔዎችን የማስተላለፍ ኃላፊነት አሁንም የሚወድቀው በእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ባለስልጣናት ላይ ነው። ይህ ሳይሆን ቀርቶ የመርሐ ግብር መቆራረጥን ለማስቀረት ብቻ ብለን በጭፍን ውድድሮችን በጊዜ ለመጨረስ በቂ ከለላ በሌለበት ሁኔታ ጨዋታዎች እንዲከናውወኑ በማድረጉ ከቀጠልን ግን በውቡ ስፖርት እግር ኳስ ሰበብ የሰዎች ህይወት እንደቀልድ የሚረግፍበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።
ከዛ ይሰውረን…