“የስፖርት ጨዋነት ምንጮች” የውይይት መድረክ የመጀመርያ ቀን ውሎ

በቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር አዘጋጅነት ለሁለት ቀናት ” የስፖርት ጨዋነት ምንጮች ” በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው የምክክር ጉባዔ ሰኞ በሼራተን ሆቴል ተጀመረ።
በዚህ የውይይት መድረክ ላይ የወጣቶች እና ሚኒስቴር ሂሩት ካሳ ፣ የሠላም ሚኒስቴር ዴኤታ አልማዝ መኮንን፣ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ጂራ፣ የጉባዔው አዘጋጅ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ሰብሳቢ አብነት ገብረመስቀል እና የውይይቱ መሪ ዕውቁ ጋዜጠኛ ፍቅሩ ኪዳኔ እንዲሁም የተለያዩ የስፖርት አካላት ኃላፊዎች ታድመውበታል።

የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት አቶ አብነት ገብረመስቀል ” በስፖርታዊ ጨዋነት ምንጮች ባተኮረው የውይይት መድረክ ላይ የተገኘነው የራሳችንን አሻራ አስቀምጠን ለማለፍ ነው። ሥርዓት አልበኝነት እግርኳሱን እየጎዳው በመሆኑ በርካታ የስፖርት ቤተሰቦችን ከስፖርት ማዘውተርያ እያራቀ ይገኛል። በጊዜ መሰራት የሚገውን የቤት ስራ ባለመስራታችን ችግሩ እየተባባሰ መጥቶ በዘር ፣ በጎሳ፣ በኃይማኖት እና በፖለቲካ አመለካከት ያተከሩ ልዩነቶች እዚም እዛም እየታዩ ይገኛሉ። ስለሆነም ይህ እየተባባሰ የመጣውን ችግር ለመቅረፍ ይህ የውይይት መድረክ ተዘጋጅቷል። ” ብለዋል።

በማስከተል አቶ ኢሳይያስ ጂራ በንግግራቸው ” እግርኳሱ የሌላ ነገር አጀንዳ መነኸርያ ከማድረጋችን ባሻገር ቂም እያወረስን እንገኛለን። እከሌ ሲያሸንፍ ከስፖርት መርህ ውጭ እከሌ ዘር ተሸነፈ፣ አሸነፈ በሚል ጤናማ ያልሆነ አስተሳሰብ ላይ ደርሰናል። ከስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል የተነሳ ሙሉ ጤና ይዞ መጥቶ ጤናውን አጉድሎ የሚመለስበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። ችግሮችን ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም ይህ በቂ አይደለም። እግርኳሱን ከዚህ እግርኳሳዊ ካልሆነ ተግባር ለመታደግ በዚህ የሁለት ቀን ውይይት ያለፉትን ደካማ ጎኖች እንደ ግብዓት ወስደን ወደፊት ምን ማድረግ አለብን በሚል ትኩረት ሰተን ልንሰራ ፣ ልንነጋገር ይገባል። ” ብለዋል።

“መለያየት ሞት ነው” በሚል ርዕስ የቀረበ የአራት ደቂቃ ዘጋቢ ፊልም ለጉባዔው ታዳሚዎች ከቀረበ በኋላ ወደ ጥያቄ እና መልስ ፕሮግራም ሲያመራ መሠረታዊ የሆኑ የአካሄድ ክፍተቶች የነበሩበት መሆኑን ጉባዔተኞች በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም የጉባዔው መሪ ጋዜጠኛ ፍቅሩ ኪዳኔ ሀሳቡን ባለመቀበላቸው የጉባዔው መንፈስ ሲረበሽ ተስተውሏል። ይሁን እንጂ በርከት ያሉ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ከተሳታፊዎች ቀርቧል። ለአብነት ያህል፡-

– ለስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ዳኝነት አንድ መንስዔ ሆኗል

– የውድድሩ ፎርማት መቀየር አለበት

– እግርኳሱ እና ፖለቲካው ተቀላቅለዋል፤ መለያየት አለባቸው።

– በአንድ ቦታ ስህተት ሲፈፀም ፌዴሬሽኑ በህጉ መሠረት ቅጣት አለመጣሉ ተመሳሳይ ችግሮች በሌሎች ሜዳዎች እንዲፈጠሩ እያደረገ ነው።

– ጎሳን፣ ዘርን፣ ፖለቲካን መሠረት ያደረጉ የክለብ አደረጃጀቶች፣ አርማዎች እና መጠሪያዎች መስተካከል አለባቸው።

– ስለ ሥነ-ምግባር ትምህርት ክለቦች እና ደጋፊዎች መማር አለባቸው። የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን በተወሰኑት ጥያቄዎች ላይ ምላሽ ተሰቶበታል።

አቶ አብነት ገ/መስቀል – እኛ ደጋፊዎቻችንን መምከር እንጂ ማስተማር አንችልም። ትምህርት ለወጣቶች መስጠት ለተጫዋቾች መሰረታዊ ትምህርት ያስፈልጋቸዋል። በራሳቸው መኖር እንዲችሉ ትምህርት ያስፈልጋቸዋል።

አቶ ኢሳይያስ ጅራ – ስፖርታዊ ጨዋነት ጉዳይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ብቻ ሳይሆን የሁሉም ነው። እናስተምርላችሁ ብለን ክለቦችን ስንጠይቅ መልስ የሰጠው ሁለት ክለብ ብቻ ነው። እኛ እናስተምር ባልን አዕምሮውን ክፍት አድርጎ መቅረብ ላይ ችግር አለ።

ከምሳ መልስ ቀላል የማይባል ታዳሚ ሳይገኝ በቀጠለው የምዕራፍ ሁለት የምክክር ጉባዔ በክለቦችን አደረጃጀት ሁኔታ አስመልክቶ አቶ አብነት ገ/መስቀል (የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ አደረጃጀትን አስመልክቶ) ፣ አቶ ሰዒድ (የጅማ አባጅፋር እግርኳስ ክለብ አደረጃጀትን) ፣ ኃይለየሱስ ፍስሀ (አጠቃላይ የክለብ አደረጃጀቶችን አስመልክቶ) እንዲሁም አቶ አኀቲ ለገሰ (የመቐለ 70 እንደርታ የደጋፊዎች ማኅበር አደረጃጀት አስመልክቶ) አጫጭር ጥናታዊ ሀሳቦችን አቅርበዋል። በቀረበው ጥናታዊ ሀሳብ መሰረት ከታዳሚው ጥያቄዎች ቀርበዋል። ጥያቄዎቹም በትክክል ጉባዔው ሊያሳካው የፈለገውን ዓላማ መነሻ ያላደረገ እና እያንዳንዱ ተሳታፊ ከግል ፍላጎቱ ተነስቶ የሚጠይቀው በመሆኑ ምላሹም ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ሲሰጥ ተስተውሏል።

ከተወሰኑ የሻይ እረፍት በኋላ በመቀጠል የተሰብሳቢውን ቀልብ የገዙ እና ትኩረት የሳቡ በተለያዩ ዕርሶች ዙርያ ባለሙያዎች አጫጭር የሆኑ የጥናት ሀሳቦችን ለቤቱ አቅርበዋል።

አቶ ንዋይ በየነ – የሥነምግባር መነሻ እና መድረሻን በክለብ አመራሮች ዙርያ፣ አሰልጣኝ መሠረት ማኒ – የሴቶች እግርኳስ ከትናንት እስከ ዛሬ ያለው ጥንካሬ እና ተግዳሮቶች ከሥነ ምግባር አንፃር፣ ኢንስትራክተር ሺፈራው እሸቱ – ውድድሩን የሚመሩት አካላት (ዳኞች ፣ የጨዋታ ህግ መምህራን ፣ የፌዴሬሽን አመራሮች የውድድር አመራሮች) ማን ናቸው? ስፖርቱን ያውቁታል? ለሥነ-ምግባርስ ተገዢ ናቸው? በሚል፣ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ – በስፖርታዊ ጨዋነት ምንጭ ዙርያ የአሰልጣኞችን ድርሻ በተመለከተ አሁን ያሉትን ተግዳሮቶች እና አሰልጣኞች በስራዎቻቸው የሚገጥሟቸው የተለያዩ ጫናዎች እንዲሁም ከሥነ ምግባር ጋር ያለው ተዛማች ጉዳይ ላይ ሀሳባቸውን ሲገልፁ በመጨረሻም ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ ከዳኝነት ጋር ተያይዞ ያሉትን ችግሮች ገልፃ ፖለቲካ እና እግርኳሱ መለያየት እንዳለበት አፅኖት በመስጠት “ዘረኞችን ፣ ጎሰኞችን ፣ ፖለቲከኞች መዳኘት አቅቶናል” ብላለች።

ወደ ማጠቃለያ ላይ ተመሳሳይ የሆኑ እና ችግሩ ላይ ከማተኮር ይልቅ እያንዳንዱ ተሳታፊ በሚፈልገው መልኩ የተለያዩ ጥያቄዎችን በማንሳት እና በተወሰኑት ላይ ምላሽ በመስጠት የመጀመርያ ቀን የጉባዔው ውሎ ተጠናቋል።

* ከፍተኛ ጊዜ እና ገንዘብ በወጣበት በዚህ መድረክ የቀረቡት ጥናቶች አብዛኛዎቹ ጥናት የተደረገባቸው ሳይሆኑ የግል ስሜት እና ፍላጎትን መሠረት ያደረጉ መሆናቸውና የመድረክ መሪዎቹ ጉባዔውን የተቆጣጠሩበት መንገድ መስተካከል ባለመቻሉ ተሰብሳቢ አስቦት የመጣውን ነገር አግኝቶ እንዳይሄድ ማድረጉን መታዘብ ችለናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡