ወልቂጤ ከተማ
በምድብ ለ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ወልቂጤ ከተማ ከሜዳው ውጪ በኦሜድላ ሜዳ ከየካ ክ/ከተማ ጋር ባደረገው ጨዋታ ለተነሳው ግርግር ምክንያት ሆኗል በሚች ሶስት የሜዳው ጨዋታዎችን በገለልተኛ ሜዳ እንዲያከናውን እና የ100 ሺ ብር ቅጣት እንደተጣለበት ይታወሳል። ክለቡ ቅጣቱን ይግባኝ በማለቱ ጉዳዩ እስኪታይ ድረስ ተፈፃሚ ሳይሆን የቆየ ሲሆን ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ በወሰነው መሰረት የጨዋታ ቅጣቱ ወደ አንድ ዝቅ እንዲል ሲደረግ የገንዘብ ቅጣቱም ወደ 10 ሺሀ ብር እንዲቀንስ መወሰኑ ታውቋል።
ካፋ ቡና
በምድብ ሐ 14ኛ ሳምንት ካፋ ቡና ከ ሻሸመኔ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ 1-1 ዘልቆ ወደ መጠናቀቂያው ሲቃረብ የተሰጠ ፍፁም ቅጣት ምት ሳይመታ የሻሸመኔ ቡድን ሜዳውን ለቆ በመውጣቱ ሳይጠናቀቅ መቅረቱ ይታወሳል። ይህን ተከትሎም የዲሲፕሊን ኮሚቴ ካፋ ቡና በፎርፌ አሸናፊ እንዲሆን ወስኗል።
በሌላ በከል ደግሞ በጨዋታው ላይ ለታየው የስፖርታዊ ጨዋነት ጥሰት ባለሜዳው ካፋ ቡና ቀጣይ ሁለት የሜዳው ጨዋታዎችን በገለልተኛ ሜዳ እንዲያደርግ ከውሳኔ ደርሷል። ካፋ በውሳኔው ቅሬታውን በመግለፅ ይግባኝ መጠየቁም ታውቋል።
የምድብ ሀ ተስተካካይ ጨዋታዎች
በተለያዩ ምክንያቶች ሳይደረጉ የቆዩ የምድብ ሀ ጨዋታዎች ነገ ይደረጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ለገጣፎ ከደሴ የሚደርገው ጨዋታ ባለው ነባራዊ የአየር ሁኔታ የሜዳ ወይም የሰዓት ለውጥ ሊደረግብት እንደሚችል የተሰማ ቢሆንም አሁን ባለው መረጀ ሁሉም ጨዋታዎች ነገ 9:00 እንደሚደረጉ ይጠበቃል።
አውስኮድከ ፌዴራል ፖሊስ
ለገጣፎ ለገዳዲ ከ ደሴ ከተማ
ወሎ ኮምቦልቻ ከ ገላን ከተማ
ወልዲያ ከ ቡራዩ ከተማ
የሳምንቱ መጨረሻ
በሊጉ በዚህ ሳምንት ቅዳሜ እና እሁድ ሊደረጉ የነበሩ ጨዋታዎች ወደ ቀጣዩ ሳምንት ተሸጋግረዋል። ነገ የተስተካካይ ጨዋታዎቹ የሚካሄዱ በመሆናቸውም ሚያዚያ 26 እና 27 ሁሉም ቡድኖች በተመሳሳይ የጨዋታ ቁጥር ላይ በመገኘት የ16ኛ ሳምንት መርሐ ግብራቸውን እንደሚያከናውኑ ይጠበቃል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡