የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዝዮን 19ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ሲካሄዱ መሪው ንግድ ባንክ ግማሽ ደርዘን አስቆጥሮ፣ ተከታዩ አዳማ ወደ አርባምንጭ ተጉዞ ድል አስመዝግበዋል።
ባንክ ሜዳ ላይ ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ያስተናገዱት ንግድ ባንኮች ከጨዋታ ብልጫ ጋር ረሂማ ዘርጋው እና ሽታዬ ሲሳይ ባስቆጠሩት ስድስት ጎሎች ታግዘው ወደ ዋንጫ የሚያደርጉትን ጉዞ አጠናክሮ ቀጥለውበታል። 09:00 በጀመረውና ንግድ ባንኮች በሁሉም ረገድ ብልጫ በወሰዱበት የመጀመርያው አጋማሽ በ8ኛው ደቂቃ ሽታዬ ሲሳይ በጥሩ ሁኔታ ነፃ አቋቋም ላይ ለምትገኘው ረሂማ ዘርጋው አሻግራላት ረሂማ በግንባሯ በመግጨት ጎል አስቆጥራ መምራት ችለዋል። ጥሩነሽ አካዳሚ የንግድ ባንክን እንቅስቃሴ መቆጣጠር በተሳናቸው በዚህ ጨዋታ 17ኛው ደቂቃ በአንድ ሁለት ቅብብል ትግስት ዘውዴ ያቀበለቻትን ሰንጣቂ ኳስ ረሂማ ዘርጋው የአጨራረስ ብቃቷን ተጠቅማ ሁለተኛ ጎሏን በማስቆጠር የንግድ ባንክን መሪነት አስፍታለች።
የግብ ዕድልም በመፍጠርም ሆነ በኳስ ቁጥጥሩም ብልጫ የተወሰደባቸው ጥሩነሽ አካዳሚዎች በራሳቸው የሜዳ ክፍል ከሚያደርጉት የተቆራረጠ ቀብብል በቀር ወደ ፊት በመሄድ የተሳካ የጎል ሙከራ ሊያስመለክቱን አልቻሉም። ጨዋታው የቀለላቸው ንግድ ባንኮች በአንፃሩ ብርቱካን ገ/ክርስቶስ የሜዳውን የመሐል ክፍል በሚገባ ተቆጣጥራ ኳሱን በማደራጀት በነበራት የጎላ ሚና ታግዘው ወደ ጎል በመድረስ ተጨማሪ ጎሎች ማስቆጠር ችለዋል። 35ኛው ደቂቃ ላይም ብርቱካን ገ/ክርስቶስ ያቀበለቻት ኳስ ረሂማ ዘርጋው ሐት – ትሪክ የሰራችበት ጎል አክላለች። ረሂማ በውድድር ዓመቱ 16ኛ ጎሏን ስታስቆጥር ከአዳማ ሴናፍ ዋቁማ በአንድ ጎል አንሳ ለከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት እየተፎካከረች ትገኛለች።
ከረሂማ በኋላ የንግድ ባንክ ጎል አስቆጣሪነትን ሽታዬ ሲሳይ ስትረከብ 42ኛው ደቂቃ ከግብ ጠባቂዋ ንግስቲ ጀምሮ የተመሰረተው ኳስ ከብዙ ንክኪዎች በኃላ በመጨረሻም ትግስት ዘውዴ እግር ገብቶ ያሻገረችውን ኳስ ሽታዬ ሲሳይ የግብ መጠናቸውን ማስፋት የቻሉበትን እና የጨዋታ ብልጫ መውሰዳቸውን ያሳዮ.ዩበትን አራተኛ ጎል አስቆጥራለች። ብዙም ሳይቆይ ሽታዬ ሲሳይ የግል ብቃቷን በመጠቀም ከርቀት አክርራ በመምታት ግሩም አምስተኛ ጎል 45ኛው ደቂቃ ላይ በማስቆጠር ወደ እረፍት አምርተዋል።
በአንፃራዊነት በተሻለ ሁኔታ የጎል ዕድል አይፍጠሩ እንጂ ኳስ ይዘው በመጫወት መልካም እንቅስቃሴ በማድረግ ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚዎች በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የተሻሉ ነበሩ። ጨዋታውን በመጀመርያው አጋማሽ የጨረሱት ንግድ ባንኮች ደግሞ ቀላል ኳሶችን በመጫወት እና የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ ቀሪ ደቂቃውን ሲጠቀሙበት ተመልክተናል። 64ኛው ደቂቃ ሽታዬ ሲሳይ የማሳረጊያ ስድስተኛ ጎል ለራሷ ደግሞ ሐት-ትሪክ የሰራችበትን ጎል ማስቆጠር ችላለች። በቀረው ደቂቃ ብዙም የተለየ ነገር መመልከት ባንችልም ሌሎች ተጨማሪ ጎል መሆን የሚችሉ አጋጣሚዎችን ዓይናለም አሳምነው፣ ረሂማ ዘርጋው እና ሽታዬ ሲሳይ ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። አልፎ አልፎ ወደ ፊት የሚሄዱት ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚዎች ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ የአማካይ ስፍራ ተጫዋቾች ቢኖራቸውም ጎል ማስቆጠር ሳይችሉ በንግድ ባንክ የበላይነት 6 – 0 ለመሸነፍ ተገደዋል። (በዳንኤል መስፍን)
ወደ አርባምንጭ ተጉዞ አርባምንጭ ከተማን የገጠመው አዳማ ከተማ 3-1 በሆነ ውጤት መርታት ችሏል፡፡ ከሌላው ጊዜ አንፃር ቀዝቀዝ ባለ አየር የተካሄደው የሁለቱን ክለቦች ጨዋታ በርከት ያሉ ተመልካቾች ያስተናገደ ሲሆን እንግዶቹ አዳማዎች ገና በጊዜ ጫና ማሳደር በመጀመር በ3ኛው ደቂቃ በግራ መስመር ሎዛ አበራ ያሻገረችውን ኳስ ሴናፍ ግብ ጠባቂዋን ለማለፍ ስትሞክር በግብ ጠባቂዋ የተያዘባት መልካም አጋጣሚ የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ ነበር፡፡ ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር አዳማዎች ከአማካይ ክፍሉ ከሰናይት ቦጋለ መነሻ ያደረጉ ኳሶች በመጠቀም በግራ እና በቀኝ ሰብረው ገብተው በአጥቂዎቻቸው አማካኝነት ለማጥቃት ከፍተኛ ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን ሴናፍ ዋቁማ በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ያገኘችውን ኳስ በግልፅ ያመከነችበት አጋጣሚም ተጠቃሽ ሙከራዎች ናቸው፡፡ ባለሜዳዎቹ አርባምንጮች ደግሞ ፀጋነሽ ወራና በግል ጥረቷ አግኝታ ያልተጠቀመባቸው ሁለት ሙከራዎች የሚጠቀሰ ነበሩ።
በተደጋጋሚ በሁለቱ ልዩነት ፈጣሪ አጥቂዎቻቸው አስፈሪ መከራን ሲያደርጉ የነበሩት አዳማ ከተማዎች 26ኛው ደቂቃ የመጀመርያ ጎል አግኝተዋል። ልማደኛዋ አጥቂ ሎዛ አበራ የተከላካዮችን መዘናጋት ተጠቅማ ከግብ ክልል ውጪ አክርራ ወደ ግብ የመታችው ኳስ ከመረብ በማሳረፍ ነበር አዳማ ከተማን መሪ ማድረግ የቻለችው፡፡ ከዚህች ግብ መቆጠር በኃላ አዳማዎች የተቀዛቀዙ ቢሆንም አርባምንጮች ይህን ተጠቅመው ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ለእረፍት ወጥተዋል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ሂደት ሁለቱም ክለቦች የጎል እድሎችን ለመፍጠር በተደጋጋሚ ወደ ግብ ክልል ቢደርሱም ግብ በማስቆጠር የተሳካላቸው አዳማዎች ነበሩ። 49ኛው ደቂቃ ላይ ሰናይት ቦጋለ፣ ሎዛ አበራና በሁለተኛው አጋማሽ ድንቅ የነበረችው እፀገነት ብዙነህ ተቀባብለው የአርባምንጭ ከተማ ተከላካዮችን በማለፍ እፀገነት ያሳለፈችላትን ኳስ ሎዛ አበራ በድንቅ አጨራረስ የአዳማን ልዩነት አስፍታለች። ለስህተት ሲጋለጥ የነበረው የአርባምንጮች የተከላካይ መስመር እና በግብ ጠባቂዋ ስህተት 54ኛው ደቂቃ ላይ እፀገነት ያሻገረችውን ኳስ ሴናፍ ዋቁማ በቀላሉ ወደ ግብነት ቀይራ የአዳማን መሪነት ወደ 3-0 መሪነት አሸጋግራለች።
በሁለተኛው አጋማሽ ሙሉ በሙሉ በአዳማ ከተማ ብልጫ ተወስዶባቸው የታዩት አርባምንጮች 65ኛው ደቂቃ ከሽንፈት ያልታደጋቸውን ግብ አስቆጥረዋል። አማካዩዋ ትሁን አየለ ከመሀል ሜዳ ያሻገረችውን ኳስ ቱሪስት ለማ በደረቷ አብርዳ ከተቆጣጠረች የኋላ በግብ ጠባቂዋ አናት ላይ በማሳለፍ ግሩም ግብ ብታስቆጥርም የግብ ልዩነቱን ከማጥበብ የዘለለ ትርጉም ሳይኖረው ጨዋታው በአዳማ ከተማ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ (በቴዎድሮስ ታከለ)
አዲስ አበባ ስታድየም ላይ በ10:00 ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኙት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክን ያገናኘው ጨዋታ በጊዮርጊስ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል። የመጀመርያዎቹ እና የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ጎሎች የተስተናገዱበት ጨዋታ አመዛኙ ክፍለ ጊዜ አሰልቺ ገፅቴን የተላበሰ ነበር። በዚት ግጥሚያ ገና በ20 ደቂቃዎች አራት ጎሎች ሲቆጠሩ ኤሌክትሪክ በዓለምነሽ ገረመው ጎል ቀዳሚ መሆን ቢችልም ዳግማዊት ሰለሞን ጊዮርጊስን አቻ አድርጋለች። ብዙም ሳይቆይ ትበይን መስፍን በድጋሚ ኤሌክትሪክን መሪ ስታደርግ የጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ የነበረችው ዳግማዊት መኮንን እንስት ፈረሰኞቹን አቻ አድርጋለች።
ከአራቱ ጎሎች መቆጠር በኋላ ጨዋታው በሚቆራረጡ ቅብብሎች እናገየ ኢላማቸውን ባልጠበቁ የርቀት ሙከራዎች ታጅቦ ለረጅም ደቂቃዎች ዘልቋል። በ43ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት ወርቅነሽ መልመላ ከመስመር ያሻገረችውን ዓለምነሽ ገረመው ኃይል የሌለው ምት ምታ በቀላሉ ግብ ጠባቂዋ ከምባቴ ያወጣችው ሙከራም ብቸኛው ተጠቃሽ ሙከራ ነበር።
ተቀዛቅዞ በቀጠለው ሁለተኛ አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በኳስ ቁጥጥር የተሻሉ ቢሆኑም ወደ ማጥቃት ወረዳ የሚደርሱባቸው ጊዜያት በጣም ጥቂት ነበሩ። በተመሳሳይ ኤሌክትሪኮችም የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው የተዳከመ እና ያልተሳኩ ቅብብሎች የበዙበት ሲሆን ተስተውሏል። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ በተሻለ ሁኔታ ወደ ጎል መቅረብ የጀመሩት ጊዮርጊሰች ጫና በመፍጠር የጎል ሙከራ ሲያደርጉ ጎልም ማስቆጠር ችለዋል። በ87ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት የተሻመ ኳስ ሲመለስ ከጥሩ ቦታ ላይ ሆና ያገኘችውን ኳስ መልካም ተፈሪ ሞከራ ግብ ጠባቂዋ ገነት አንተነህ በጥሩ ሁኔታ ስትመልሰው ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ዳግማዊት ከግራ መስመር በመቀስ ምት ወደ ግብ ሲያመራ ግብ ጠባቂዋ ገነት እንደምንም ብታድነውም የተመለሰውን ኳስ ፅዮን ማንጁራ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከግርጌው የተላቀቀበትን ወሳኝ የድል ጎል አስቆጥራለች።
በሌሎች ጨዋታዎች ዲላ ላይ ጌዲኦ ዲላ በሜዳው አዲስ አበባ ከተማን ጋብዞ በፈጣኗ አጥቂ ረድዔት አስረሳኸኝ ሁለት እና በፀሎት መሐመድ ተጨማሪ ጎል 3-0 ሲያሸንፍ ድሬዳዋ ከተማ በሀዋሳ በሜዳው 2-0 ሽንፈት ገጥሞታል፡፡ አጥቂዋ ነፃነት መና በ17ኛው ደቂቃ ከርቀት ባስቆጠረችው ግብ ሀዋሳን መሪ ስታደርግ በድጋሚ በ43ኛው ደቂቃ ሁለተኛውኝን አክላለች። ባህር ዳር ላይ በቀጣይ ዓመት ቡድኑን እንደሚያፈርስ ያስታወቀው ጥረት ኮርፖሬት ከ መከላከያ ያደረጉት ጨዋታ ደግሞ 3-3 ተጠናቋል። ምስር ኢብራሂም (2) እና አዲስ ንጉሴ ለጥረት፣ መዲና ዐወል (2) እና ሔለን አሸቱ ለመከላከያ ጎሎቹን አስቆጥረዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡