ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ደቡብ ፖሊስ ከ ወላይታ ድቻ

በታችኛው የሰንጠረዡ ክፍል ለውጦችን እንደሚያመጣ በሚጠበቀውን የደቡብ ፖሊስ እና የድቻ  ጨዋታ እንዲህ ዳሰነዋል።

በ12ኛ እና 13ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ወላይታ ድቻ እና ደቡብ ፖሊስ ነገ በ11፡00 አዲስ አበባ ላይ የሚያከናውኑት ጨዋታ በተለይም ለፖሊሶች ወሳኝነቱ ከፍ ያለ ነው። በሳምንቱ መጨረሻ በደጋፊዎች ላይ በደረሰ ጥቃት ምክንያት ሳይከናወን ቀርቶ ወደ ነገ በተዘዋወረው ጨዋታ ቀድሞ የተጫወተው መከላከያ ሽንፈት የደቡብ ፖሊሶችን ትኩረት የሚጨምር ነው። ከሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ከጎንደር አንድ ነጥብ ይዘው የተመለሱት ደቡብ ፖሊሶች በድል ከጦሩ ጋር ያላቸውን ልየነት በማስፋት ከአደጋው ለመራቅ ከዚህ ጨዋታ የሚያገኙት ነጥብ በእጅጉ ያስፈልጋቸዋል። ሳምንት ኢትዮጵያ ቡናን ድል በማድረግ ከመቐለው ሽንፈት ያገገሙት ድቻዎች በበኩላቸው ከወራጅ ቀጠናው በአምስት ነጥቦች ከፍ በማለታቸው ከተጋጣሚያቸው አንፃር በአነስተኛ ጫና ነው ጨዋታውን የሚያከናውኑት። ውጤት ከቀናቸውም ከአዳማ ጋር በነጥብ በመስተካከል ለከርሞው በሊጉ የመቆየታቸውን ነገር ከወዲሁ ለማረጋገጥ ይበልጥ ዕድላቸውን ያሰፋሉ።

ከቡድኖቹ ወቅታዊ አጨዋወት መንገድ አንፃር ጨዋታው የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ለማግኘት ፉክክር የሚደረግበት እና ቡድኖቹ በማጥቃት ላይ አመዝነው የሚንቀሳቀሱበት እንደሚሆን ይታመናል። ከተጋጣሚያቸው በተሻለ መሀል ላይ የሚይዟቸውን ኳሶች በፍጥነት ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ለማድረስ እንደሚጥሩ የሚጠበቁት ደቡብ ፖሊሶች ከመስመር አጥቂዎቻቸው ወደ ውስጥ በሚላኩ ኳሶች አደጋ የመፍጠር ዕድል አላቸው። የቡድኑ ግብ አዳኝ ኄኖክ አየለ ብቃትም እንደወትሮው ሁሉ ለፖሊስ የበላይነት ወሳኝነቱ የጎላ ነው። በወላይታ ድቻ በኩል በአንፃሩ በፍጥነት ዝግ ያለ የኳስ ምስረታ የሚጠበቅ ሲሆን መሀል ላይ ሊያገኝ ከሚችለው የቁጥር ብልጫ በመነሳት ወደ መሀል በጠበበ መልኩ እንደሚያጠቃ ይጠበቃል። ነገር ግን የባዬ ገዛኸኝ በቀይ ካርድ ቅጣት ቡድኑ ከፊት የሚኖረውን ስልነት ሊቀንሰው የሚችል ቢሆንም ቀሪው ስብስቡ ግን በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛል። በአሰልጣኝ ገብረመስቀል ቢራራ ቡድን በኩል ደግሞ አበባው ቡታቆ ከቅጣት አዳሙ መሀመድ ደግሞ የፋስሉን ጨዋታ ካስመለጠው የግል ጉዳይ መልስ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይጠበቃል።

የእርስ በርስ ግንኘነት እና እውነታዎች

– ቡድኖቹ በሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙበትን የስድስተኛ ሳምንት ጨዋታ ወላይታ ድቻ በአንዷለም ንጉሴ ግብ  አማካይነት 1-0 ማሸነፍ ችሎ ነበር።

– ከሲዳማ ጋር ያደረጋቸውን የአዲስ አበባ ጨዋታዎች ጨምሮ ከሶዶ በወጣባቸው 11 ጨዋታዎች ምንም ድል ያላሳካው ወላይታ ድቻ ነጥብ ተጋርቶ የተመለሰውም አራት ጊዜ ብቻ ነበር።

ዳኛ

– ጨዋታው ለኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ ሰባተኛ ጨዋታው ይሆናል። እስካሁን 22 የማስተጠንቀቂያ ካርዶች እና አንድ የፍፁም ቅጣት ምት ውሳኔዎችን አሳልፏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ደቡብ ፖሊስ (4-3-3)

ሀብቴ ከድር

አናጋው ባደግ – ደስታ ጊቻሞ  – አዳሙ መሀመድ – አበባው ቡታቆ

 ዘላለም ኢሳያስ – ዮናስ በርታ – ብሩክ አየለ

የተሻ ግዛው – ኄኖክ አየለ – ብሩክ ኤልያስ

ወላይታ ድቻ (4-1-3-2)

ታሪክ ጌትነት

እሸቱ መና – ደጉ ደበበ – ዐወል አብደላ – አንተነህ ጉግሳ

በረከት ወልዴ

ፀጋዬ አበራ – አብዱልሰመድ ዓሊ – ቸርነት ጉግሳ

ኃይሌ እሸቱ – አላዛር ፋሲካ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡