የሀዋሳ ከተማ ፖሊስ በጨዋታው ምክንያት ለሚፈጠር ችግር ኃላፊነት አልወስድም በማለቱ እሁድ ሳይደረግ የቀረው የ21ኛው ሳምንት የሀዋሳ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ በገለልተኛ ሜዳ አሰላ ላይ ተካሂዶ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
ሀዋሳ ወደ አዳማ ተጉዞ ከሜዳ ውጭ በማሸነፍ ወሳኝ ሦስት ይዞ ከተመለሰው ስብስቡ የአንድ ተጫዋች ለውጥ ብቻ በማድረግ ብሩክ በየነን በዳንኤል ደርቤ ተክቶ ወደ ሜዳ ሲገባ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲዳማ ቡናን በሜዳው ካሸነፈው ስብስቡ መካከል የሦስት ተጫዋች ለውጥ ያደረገ ሲሆን አስቻለው ታመነ ፣ ሙሉዓለም መስፍን እና አቤል ያለውን አሳርፎ አብዱልከሪም መሐመድ ፣ ታደለ መንገሻ እና አሜ መሐመድን ተክቷል።
በ2007 ወርኃ ሰኔ ሙገር ሲሚንቶ ከወላይታ ድቻ አንድ አቻ ከተለያየበት የ25ኛ ሳምንት ጨዋታ በኃላ ሙገር ሲሚንቶ ወደ ከፍተኛ ሊግ መውረዱን ተከትሎ ምንም አይነት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ሳያስተናግድ የቆየው የአሰላ አረንጓዴው ስታዲየም ዛሬ ለመጀመርያ ጊዜ ማስተናገድ ችሏል።
የመጠናናት እና የመጠባበቅ እንቅስቃሴ በማድረግ የጀመረው ጨዋታው ደቂቃ እየገፋ ሲሄድ ለጎል የቀረቡ ሙከራዎችን በሁለቱም ቡድኖች በኩል ያስመለክታል ተብሎ ቢጠበቅም ረጃጅም ኳሶች በርክቶበት ውሏል። የነበረው ከባድ ንፋስ እና የሜዳው ኳስ ይዞ ለመጫወት አለመመቸት ለአየር ላይ ኳሶች መብዛት ምክንያት ሊሆን እንደሚችልም ታይቷል። በሀዋሳዎች በኩል የተሳካ ሦስት ቅብብል እንኳ ያላደረጉት አብዛኛው ቁጥር በራሳቸው ሜዳ በዝተው በመገኘት ብቸኛ አጥቂያቸው እስራኤል እሸቱን ትኩረት ያደረገ የማጠቃት መንገዳቸው በመጀመርያ አጋማሽ ምንም የግብ ዕድል ሳይፈጥሩ እንዲወጡ አድርጓቸዋል።
በአንፃሩ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ኳሱን ተቆጣጥረው በመጫወት የተሻሉ የነበሩ ቢሆንም ሀዋሳዎች ሜዳቸውን ሳይለቁ በመጫወታቸው ጎል የማስቆጠር ዕድል ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል። በቀኝ መስመር ያደላው የፈረሰኞቹ የማጥቃት እንቅስቃሴ አቡበከር ሳኒ እና አቡዱልከሪም መሐመድ የሚያሻግሯቸው ኳሶች መድረሻቸው ሳይታወቅ ይባክኑ ነበር። ከማዕዘን ምት የተመታውን ተደርቦ ሲመለስ አሜ መሐመድ በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት በግቡ አናት ላይ የወጣውም በ36ኛው ደቂቃ ላይ በፈረሰኞቹ በኩል የመጀመርያ ለጎል ሙከራ ሆኖ ወደ እረፍት አምርተዋል።
ከእረፍት መልስ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከመጀመርያው አጋማሽ በተሻለ በርከት ያሉ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለዋል። 48ኛው ደቂቃ ላይ ከተሻጋሪ ኳስ አሜ መሐመድ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ውጭ የወጣበት፤ 55ኛው ደቂቃ አቡበከር ሳኒ ጣጣውን ጨርሶ ሰንጥቆ ቢያቀብለውም ሪቻርድ አርተር በማይታመን ሁኔታ ወደ ውጭ የሰደዳት የሚያስቆጩ አጋጣሚዎች ነበሩ። በእነዚህ ሁለት ሙከራዎች የተነቃቁት ቅዱስ ጊዮርጊዮርጊሶች ባላሰቡት ሁኔታ ተቀይሮ በገባው ታዳጊው አጥቂ መስፍን ታፈሰ አማካኝነት ከርቀት አጥብቆ የመታት ኳስ ግብ ጠባቂው ፓትሪክ ማታሲ እንደምንም አድኖበታል። የፈረሰኞቹ የማጥቃት ኃይላቸው ጨምሮ 61ኛው ደቂቃ አሜ መሐመድ ሳይጠቀምበት የቀረው ፣ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ናትናኤል ዘለቀ በ67ኛው ደቂቃ በግንባሩ ገጭቶ ግብጠባቂው ተክለማርያም ሻንቆ ወደ ውጭ ያወጣበት ሌላ ለጎል የቀረቡ ሙከራዎች ነበሩ።
ከደቂቃዎች በኃላ 71ኛው ደቂቃ አቡበከር ሳኒ አክርሮ ሲመጣ በሀዋሳ ተከላካዮች ተደርቦ የተመለሰውን ሪቻርድ አርተር አግኝቶ የመታውን የግቡ ቋሚ አግዳሚ የመለሰበት ቅዱስ ጊዮርጊሶችን መሪ ማድረግ የምትችል የምታስቆጭ አጋጣሚ ስትሆን በሀዋሳዎች በኩል የጊዮርጊስን ተከላካዮች ሲፈትን የታየው መስፍን ታፈሰ ሲሆን 77ኛው ደቂቃ ከእስራኤል እሸቱ የተቀበለውን ከሳጥን ውጭ አክርሮ ቢመታውም የውጭ መረቡን ነክቶ ወጥቶበታል።
የጨዋታው መጠናቀቂያ እየገፋ በሄደ ቁጥር ጊዮርጊሶች ጎል ለማስቆጠር ጫና በመፍጠር አማካዩ ሀምፍሬይ ሚዬኖ ሳጥን ውስጥ ነፃ ኳስ አግኝቶ ኳሱን አጠንክሮ ባለመምታቱ ሳይጠቀምበት የቀረው ሌላው ለጎል የቀረበ ሙከራ ነበር። ጨዋታውም በከባድ ንፋስ ታግዞ 0 – 0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡