የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከ17 ዓመት በታች ውድድር 9ኛ ሳምንት ሐሙስ በተለያዩ ሜዳዎች ተደርገው ኢትዮጵያ መድን፣ አዳማ ከተማ፣ ኤሌክትሪክ፣ መከላከያ እና አፍሮ ፅዮን አሸንፈዋል።
3:00 ላይ በአካዳሚ ሜዳ ለረጅም ጊዜ የሰንጠረዡ አናት ላይ የነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስን የገጠመው አዳማ ከተማ 2-0 አሸንፏል። ጥሩ ፉክክር በታየበት ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጥሩ የሚባል እንቅሰቃሴ ቢያደርጉም ጎል ማስቆጠር ሳይችሉ ወደ እረፍት አምርተዋል። ከእረፍት መልስ በርካታ የግብ እድሎችን መፍጠር የቻሉት አዳማ ከተማዎች ፍራኦል ጫል ከግራ ሳጥን ጠርዝ ወደ ግብ አክርሮ በመምታት ባስቆጠረው ድንቅ ግብ ቀዳሚ መሆን ችለዋል።
ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የተሻለ ለመንቀሳቀስ የሞከሩት ጊዮርጊሶች በተደጋጋሚ ወደግብ መድረስ ቢችሉም በአዳማ ከተማ ተከላካዮች ሲጨናገፍባቸው ተስተውሏል። በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃ ላይም ፍራኦል ጫላ ከነቢል ኑሬ የተሻገረለትን ኳስ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ በማለፍ አስቆጥሮ መሪነቱን ወደ ሁለት አስፍቷል። በዛሬው ጨዋታ ልዩነት ፈጣሪ የነበረው ፍራኦል ትልቅ ተስፋ የሚጣልበት ታዳጊ መሆኑን ከማሳየቱ በተጨማሪ በ14 ጎሎች የውድድሩ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነትን በመምራት የውድድር ዓመቱን አጋምሷል።
5:00 ላይ አፍሮ ፅዮን ከኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ የተደረገውን ጨዋታ አፍሮ ፅዮን 4 – 3 አሸንፏል። ግብ በማግባት ደረጃ ቀዳሚ የነበሩት አፍሮ ፅዮኖች ነበሩ፤ ጨዋታው በመጀመሪያዎች ደቂቃዎች ላይ አሸናፊ አክመል መሀል ለመሀል የተሻገረለትን ኳስ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ አፍሮ ፅዮኖችን ቀዳሚ ማድረግ ቢችልም ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ተጭነው የተጫወቱት አካዳሚዎች ከድር ዓሊ ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ አብድራህማን አብዲሰላም በጭንቅላት በመግጨት አቻ መሆን ችለዋል።
ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላ ከቀኝ መስመር የተሻማውን ኳስ ያሬድ ተፈራ በጭንቅላት በመግጨት ግብ አስቆጥሮ አፍሮ ፅዮኖች በድጋሚ መምራት ችለዋል። ሌላኛው ተስፋ የተጣለበት የአካዳሚ ታዳጊ ከድር ዓሊ የመጀመሪያው አጋማሽ ሊገባደድ ጥቂቅ ደቂቃዎች ሲቀሩ ከቀኝ መስመር አንዋር አቡደላ ያሻገረለትን ኳስ ከግብ ጠባቂ ጋር በመገናኘት ድንቅ ግብ አስቆጥሮ አካዳሚን አቻ በማድረግ ነበር የመጀመርያው አጋማሽ የተጠናቀቀው።
ሁለተኛው አጋማሽ ላይ የመሐል ሜዳ ላይ ብልጫ የወሰዱት አፍሮ ፅዮኖች ያሬድ ተፈራ ከግብጠባቂ ጋር በመገናኝት ድንቅ ግብ አስቆጥሮ ለሦስተኛ ጊዜ መሪ መሆን ሲችሉ በጨዋታው ድንቅ እንቅስቃሴ ያደረገው አሸናፊ አክመል በተከላካዮች ስህተት ያገኝውን ኳስ ወደ ጎልነት ለውጦ ሐት-ትሪክ በመስራት የአፍሮን የጎል መጠን አራት አድርሷል። በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር ሳጥን ጠርዝ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኝውን የቅጣት ምት አንዋር አብደላ ለአካዳሚ በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮ የግብ ልዩነቱን ማጥበብ ቢችልም ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠር ጨዋታው በአፍሮ ፅዮን 4-3 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ጃን ሜዳ ላይ ኢትዮጵያ ቡናን የገጠመው ኢትዮጵያ መድን 6-0 አሸንፎ መሪነቱን አጠናክሯል። ጌታነህ ካሳዬ 3 ጎሎች በማስቆጠር ሐት-ትሪክ ሲሰራ የጎል መጠኑንም 11 ማድረስ ችሏል። አሸብር ደረጄ (ሁለት) እና ኪሩቤል ከበደ ሌሎቹ ጎል አስቆጣሪዎች ናቸው።
ጎፋ ካምፕ ላይ መከላከያ ሠላምን 6-0 አሸንፏል። ምስግናው መላኩ ሐት-ትሪክ ሲሰራ፣ ያሬድ ማትዮስ ፣ ቅዱስ ዮሐንስ እና ሳሙኤል ገረመው (በራሱለ ላይ) አንድ አንድ ጎሎችን አስቆጥረዋል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሌላው በሳምንቱ ስድስት ጎሎች ያስቆጠረ ቡድን ሆኗል። ሀሌታን 6-1 ሲያሸንፍ አንዋር ሙራድ እና በረከት ብርሃኑ እያንዳንዳቸው ሦስት ጎሎች በማስቆጠር ሐት-ትሪክ መስራት ችለዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡