” ደንቡን በሚገባ አይተነዋል፤ አንድ ግለ ሰብ በፈፀመው ጥፋት ክለብ ይቀጣል የሚል ነገር የለም” አቶ ተስፋይ የስሑል ሽረ ስራ አስከያጅ
ላለመውረድ በሚደረገው ትግል ውስጥ የሚገኙት ስሑል ሽረዎች ባለፈው ሳምንት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ባደረጉት ጨዋታ የሥነ ምግባር ጥሰት ፈፅመዋል በሚል ሁለት ጨዋታዎች ከሜዳቸው 200 ኪ.ሜ ርቀት ላይ እንዲጫወቱ እና ሰላሳ አምስት ሺ ብር እንዲከፍሉ ተወስኖባቸዋል።
በጨዋታው የቀድሞው የክለቡ ቡድን መሪ ኤፍሬም ሐዱሽ ከመስመር ዳኛው ኢብራሂም አጋዥ በፈጠረው እሰጣ ገባ ዳኛው ላይ ጥቃት ፈፅሟል በሚል ቅጣት የተጣለበት የስሑል ሽረ ስራ አስከያጅ አቶ ተስፋይ ከሶከር ኢትዮጽያ ጋር ባደረጉት አጭር ቆይታ አንድ ግለሰብ በፈፀመው ተግባር እንዲህ ዓይነት ከባድ ቅጣት መተላለፉ ተገቢ እንዳልሆነ ገልፀው ይግባኝ እንደሚጠይቁም ተናግረዋል። “የሚታወቅ ግለሰብ ከሆነ በህግ ነው መጠየቅ ያለበት፤ ክለቡ በደጋፊው ምክንያት ሊቀጣ ይችላል። ጥፋት የፈፀመው ግለሰብ ማን እንደሆነ እየታወቀ እና እሱን በህግ መጠየቅ እየተቻለ ይህን ውሳኔ መወሰናቸው አግባብ አይደለም። ጥፋት የፈፀመው ግለሰብም በዚህ ሰዓት ከኛ ጋር አይደለም፤ የቡድናችን አባል አይደለም።
” የይግባኝ ግዜ አልተሰጠንም። ደብዳቤው የተሰጠን ትላንትና አስር ሰዓት ነው። ደብዳቤውን ከዚ ሰዓት ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል ነው የሚለው። ከማን ከማን ጋር የምናደርጋቸው ጨዋታዎች ነው የሚል በግልፅ አልተቀመጠም። በአጠቃላይ ውሳኔው ተገቢ አይደለም። ከዚህ በተጨማሪ ደምባችንን በደምብ አይተነዋል። አንድ ግለሰብ በፈፀመው ጥፋት ክለብ ይቀጣል የሚል በደምብ ውስጥም የለም፤ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ውሳኔም ህጉን የተከተለ አይደለም።” ብለዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡