U-20 ምድብ ለ | አዳማ ከተማ በጎል ተንበሽብሾ መሪነቱን አጠናክሯል

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዙር ዛሬ ሲጀመር በምድብ ለ አዳማ ከተማ፣ ፋሲል ከነማ፣ ኤሌክትሪክ እና ሀላባ ከተማ አሸናፊዎች ሆነዋል።

አዳማ ከተማን ከአሰላ ኅብረት ያገናኘውን ጨዋታ አዳማዎች ከድንቅ ጨዋታ ጋር ፍፁም የበላይነት ጋር 7-0 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፈዋል። በመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ የተንቀሳቀሱት አዳማ ከተማዎች 11ኛው ደቂቃ ላይ ዱሬሳ ሹቢሳ ከሳጥን ውጪ መትቶ ግብ ጠባቂው በተከላካዮች በመሸፈኑ ምክንያት በእጆቹ መሀል ሾልካ በተቆጠረች ጎል ቀዳሚ መሆን ሲችሉ ጨዋታው በአዳማ ከተማዎች የበላይነት ቀጥሎ 44ኛው ደቂቃ ላይ የአሰላ ኅብረት ግብ ጠባቂ እግሩ ላይ የያዘውን ኳስ ተጫዋች ለማለፍ ሲሞክር ተጨናግፎበት አቤኔዘር ሲሳይ ኳሷ ላይ በፍጥነት ደርሶ በባዶ መረብ ላይ በማሳረፍ ልዩነቱን ወደ ሁለት አስፍቷል።

በሁለት ግብ ልዩነት እየመሩ ወደ እረፍት ያመሩት አዳማ ከነማዎች ከእረፍት መልስ በ50ኛው ደቂቃ የቡድኑ የመሀል ሞተር አላሚን ከድር 2 ተጨዋቾችን አልፎ ያለቀለት ኳስ ለቢንያም አይተን አቀብሎት ቢንያም ወደ ግብነት በመቀየር ልዩነቱን ሦስት ሲያደርሰው ብዙም ሳይቆይ በ52ኛው ደቂቃ ዮናስ አብነት ከቀኝ መስመር ወደ ፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውስጥ 2 ተጨዋቾችን በማለፍ ያቀበለውን ኳስ ቢንያም አይተን በድጋሚ ተረጋግቶ በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮ 4-0 እንዲመሩ አስችሏል።

ጎል ባስቆጠሩ ቁጥር ይበልጥ ኃይል እየጨመሩ የመጡት አዳማዎች ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር አልተቸገሩም። በ58ኛው ደቂቃ ዱሬሳ ሹቢሳ ከመሀል ለመሬት የሾለከለትን ኳስ ከተከላካዮች አምልጦ በመውጣት በሚገባ ተቆጣጥሮ በመግፋት ግሩም ግብ አስቆጥሯል። በ72ኛው ደቂቃ በጥሩ አንድ ሁለት ቅብብል ጥሩ አቋቋም ላይ ለነበረው ዮሐንስ ፋንታ የደረሰውን ኳስ ዮሐንስ አክርሮ ወደ ግብ በመምታት በግብ ጠባቂው ቀኝ በኩል ድንቅ ግብ በማስቆጠር የግብ መጠኑን ወደ ስድስት አድርሷል።

አዳማዎችን መቆጣጠር የከበዳቸው አሰላ ኅብረት ተጫዋቾች የኳስ ቁጥጥርን ለማምከን አልፎ አልፎ የኃይል ጨዋታ የመረጡ ቢሆንም በመጨረሻ ደቂቃ የፍፁም ቅጣት ምት እንዲሰጥባቸው አድርጓል። 89ኛው ደቂቃ ላይ አቤኔዘር ሲሳይ ተከላካዮችን አልፎ ሲገባ ከኋላ በመጠለፉ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት አላሚን ከድር መትቶ ግብ ጠባቂው ቢያድነውም በቅርበት የነበረው ዮሐንስ ፋንታ ወደ ማሳረጊያ ጎልነት ቀይሮት ጨዋታው በአዳማ ከተማ 7-0 አሸናፊነት አጠናቋል።

በዘንድሮው የውድድር አመት በሜዳቸው በሰፊ የግብ ልዩነት እያሸነፉ የሚገኙት አዳማዎች የደረጃ ሰንጠረዡን በ3 ነጥቦች ልዩነት መምራታቸውን ቀጥለዋል።

በተመሳሳይ ሰዓት ጎንደር አፄ ፋሲለደስ ስታድየም ላይ አፍሮ ፅዮንን ያስተናገደው ፋሲል ከነማ 3-1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ሀለለተኛ ደረጃውን ይዞ መቀጠል ችሏል። የቡድኑ አምበል ዳንኤል ዘመዴ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ናትናኤል ማስረሻ ቀሪዋን ጎል አስቆጥሯል።

በሌሎች ጨዋታዎች ኢትዮ ኤሌክትሪክ ግርጌ ላይ የሚገኘው ወልቂጤ ከተማን 3-1 ሲያሸንፍ ሀላባ ከተማ ኢትዮጵያ መድንን 4-0 አሸንፏል። አዲስ አበባ ከተማ የሳምንቱ አራፊ ቡድን ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡