“የታጠቁት መሳርያ ዘመናዊ ነበር፤ ቀጥታ ተኩስ ነበር የከፈቱብን” አሌክሳንደር ገብረህይወት የዋልታ ፖሊስ ትግራይ ተጫዋች
ባሳለፍው ዓርብ መላው የእግርኳስ አፍቃሪን እጅግ ያሳዘነ ድርጊት በዋልታ ፖሊስ ትግራይ ክለብ አባላት ላይ መፈፀሙ ይታወሳል። ከጥቃቱ በኃላ በስድስት የቡድኑ ተጫዋቾች ከባድ እና ቀለል ያለ ጉዳት ደርሶባቸው በህክምና እርዳታ ላይ የሚገኙ ሲሆን አማኑኤል ብርሃነ የተባለው ተጫዋች በሞት ተለይቷል። የተጫዋቹ የቀብር ሥነ-ስርዓትም ቅዳሜ ዕለት በመቐለ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስትያን ተፈፅሟል።
ጥቃቱ በተፈፀመበት ዕለት ከነበሩት ተጫዋቾች መካከል እንዱ የሆነው አሌክሳንደር ገብረህይወት ስለ ሁኔታው ሃሳቡን ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግሯል። “ምንም ሳናስበው የመጣ እጅግ ዘግናኝ ጥቃት ነው። እንደ እግዝአብሄር ቸርነት፤ እንደ ሹፌራችን እና አሰልጣኛችን ጥረት ባይሆን ኖሮ ጉዳቱ ከዚህ በበለጠ እጅግ አስከፊ ይሆን ነበር” ያለው ተጫዋቹ በተለይም በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች የነበረው የተኩስ እሩምታ እጅግ አስፈሪ መልክ እንደነበረው ያስረዳል።
” ልክ አንድ መንገድ ላይ ስንደርስ በሁሉም በኩል በታጣቂዎቹ ተከበብን። እጅግ በሚገርም ፍጥነት ሙሉ የመኪናችን አካል በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ነው የወደመው። የታጠቁት መሳርያ ዘመናዊ ነበር። እንዳዩንም ቀጥታ ተኩስ ነበር የከፈቱብን” ሲል ስለ ሁኔታው ያክላል።
የቡድኑ አባላት ከጥቃቱ በኋላ ቶሎ የህክምና ድጋፍ አለማግኘታቸው ሁኔታው እንዳባባሰው የገለፀው አሌክሳንደር የሹፌሩ ብቃት ባይታከልበት ኖሮ ሁኔታው እጅግ አስከፊ እንደነበር ተናግሯል። “ሹፌራችን ከእግዚአብሔር ቀጥሎ እሱ ነው ያተረፈን። የደረሰበትን በጣም ትልቅ ጉዳት እና የታጣቂዎቹን ጥቃት ተቋቁሞ በርካታ መንገድ ባይጓዝ ኖሮ እኛ አንተርፍም ነበር። የታጠቁት መሳርያ በጣም ዘመናዊ ነው ፤ ከጥቃቱ በኃላም ህክምናው ቶሎ ስላላገኘን ሁኔታው ከባድ አድርጎብን ነበር “ብሏል።
አሌክሳንደር በመጨረሻም ” ሜዳ ውስጥ የሚሰነዘሩብንን እግር ኳሳዊ ያልሆኑት ስድቦች እና ዛቻዎች ተቋቁመን ወደ ጥሩ ብቃት መጥተን፤ ደረጃችንም አሻሽለን ነበር። ከዛ በኋላ ይህ ጥቃት መከሰቱ አሳዝኖኛል።” ሲል አስተያየቱን አጠቃሏል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡