ቀጣዩ የዳሰሳችን ትኩረት የባህር ዳር እና ደበብ ፖሊስ ጨዋታ ይሆናል።
በግዙፉ የባህር ዳር ስታድየም ነገ 09፡00 ላይ ባህርዳር ከተማ ደቡብ ፖሊስን ያስተናግዳል። ከሁለት ግብ በላይ ተቆጥሮበት የማያውቀው ባህር ዳር ከተማ ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና ከደረሰበት ከባድ ሽንፈት በኋላ ዳግም ወደ ሰንጠረዡ አጋማሽ ተንሸራቷል። በሜዳቸው የሚያደርጉትን የነገ ጨዋታ በማሸነፍም ከከባዱ ሽንፈት ለማገገም እና እስከ አራተኛ ደረጃ ከፍ ለማለት እንደሚጥሩ ይጠበቃል። ከመከላከያ በአንድ ነጥብ ብቻ ከፍ ብለው የተቀመጡት ደቡብ ፖሊሶች ደግሞ በገለልተኛ ሜዳ ከወላይታ ድቻ ነጥብ ከተጋሩበት ያሳለፍነው ሐሙስ ጨዋታ በኋላ ከአደጋው ክልል ርቀታቸውን ለማስፋት ከባህር ዳር ሦስት ነጥብ ይዘው መመለስ ይጠበቅባቸዋል። ባለሜዳው የአሸናፊነት መንፈሱን መልሶ ለማግኘት ዕንግዳው በድን ደግሞ በሊጉ የመቆየት ተስፋውን ለማለምለም የሚያደርጉት ጨዋታ መልካም ፉክክር እንደሚደረግበት ይጠበቃል።
በመጀመሪያ አሰላለፋቸው ውስጥ በርካታ ለውጦችን ሊያደርጉ የሙችሉት ባህር ዳር ከተማዎች የቡድናቸው አምበል ፍቅረሚካኤል ዓለሙ አሁንም ከጉዳቱ ባለማገገሙ በነገው ጨዋታ አይሰለፍም። ከፍቅረሚካኤል ውጪ ምንም የጉዳት እና የቅጣት ዜና የሌለበት ቡድኑ ለተከታታይ ቀናት ልምምድ ሲያከናውን ያለአሰልጣኙ ጳውሎስ ጌታቸው መሆኑ ተሰምቷል። ጳውሎስ ጌታቸው ወላጅ አባታቸው በመታመማቸው ከቡድኑ ጋር ያልቆዩ ሲሆን ምናልባት ዛሬ ምሽት ከአዲስ አበባ ባህር ዳር በመግባት ቡድኑን ይቀላቀላሉ ተብሎ ተገምቷል። በደቡብ ፖሊስ በኩል በድቻው ጨዋታ ተጎድቶ የወጣው ዮናስ በርታን ማገገም ጨምሮ ያለምንን ጉዳት እና ቅጣት ዜና ነው ወደ ባህር ዳር ያቀናው።
በኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ ከተከላካይ መስመራቸው ጀርባ በሚተውት ክፍተት ከአምስቱ ግቦች በተጨማሪ ተደጋጋሚ ጥቃት ሲሰነዘርባቸው የነበሩት ባህር ዳሮች ነገም ተመሳሳይ ችግር ሊገጥማቸው ይችላል። ለመልሶ ማጥቃት የተመቸ አደረጃጀት ያላቸው ደቡብ ፖሊሶች ኳስ ይዘው ለመጫወት ቢሞክሩም ይበልጥ በሁለቱ መስመሮች በቶሎ ወደተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ ለመግባት ምቹ መሆናቸው ለባለሜዳዎቹ ስጋት ይሆናል። የባህር ዳር የመስመር አጥቂዎችም ቡድኑ ሊይዝ ከሚችለው የተሻለ የኳስ ቁጥጥር መነሻነት ከፖሊስ የመስመር ተካላካዮች ጋር የሚያደርጉት ፍልሚያም በጨዋታው ተጠባቂ ነው።
የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች
– በፕሪምየር ሊጉ ያገናኛቸው የመጀመሪያ ዙር የሀዋሳው ጨዋታ በወሰኑ ዓሊ ብቸኛ ግብ በጣና ሞገዶቹ አሸናፊነት ተጠናቋል።
– በሜዳቸው በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ያለሽንፈት የቀጠሉት ባህር ዳሮች የሊጉን መሪዎች የገጠሙበትን የመጨረሻ ጨዋታ ጨምሮ ስድስት የድል እና አራት የአቻ ውጤቶችን አስመዝግበዋል።
– ከአስር የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች በአምስቱ ሽንፈት የገጠመው ደቡብ ፖሊስ ሁለቴ አሸንፎ ሦስቴ ደግሞ ነጥብ በመጋራት ተመልሷል።
ዳኛ
– ጨዋታውን ተፈሪ አለባቸው በመሀል ዳኝነት ይመራዋል። እስካሁን በስድስት ጨዋታዎች በመሀል ዳኝነት የተመደበው ተፈሪ 36 የማስጠንቀቂያ ካርዶችን ሲመዝ አንድ የሁለተኛ ቢጫ ፣ ሁለት የቀጥታ የቀይ ካርዶች እና ሦስት የፍፁም ቅጣት ምት ውሳኔዎችንም አሳልፏል። አርቢትሩ ከዚህ ቀደም በህር ዳር ሲዳማ ደቡብ ፖሊስ ደግሞ ከሽረ ያደረጓቸውን ጨዋታዎች ዳኝቷል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ባህር ዳር ከተማ (4-3-3)
ምንተስኖት አሎ
ሣለአምላክ ተገኝ – ወንድሜነህ ደረጄ – አቤል ውዱ – አስናቀ ሞገስ
ዳግማዊ ሙሉጌታ – ዳንኤል ኃይሉ – ኤልያስ አህመድ
ግርማ ዲሳሳ – ጃኮ አራፋት – ወሰኑ ዓሊ
ደቡብ ፖሊስ (4-3-3)
ሀብቴ ከድር
አናጋው ባደግ – ደስታ ጊቻሞ – አዳሙ መሀመድ – አበባው ቡታቆ
ዘላለም ኢሳያስ – ዮናስ በርታ – ብሩክ አየለ
የተሻ ግዛው – ኄኖክ አየለ – በረከት ይስሀቅ
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡