” በውድድር ዓመቱ ቡድናችን ጥሩ ባይሆንም በግሌ ብዙ ትምህርት ወስጄበታለው፤ ጥሩ ጊዜም እያሳለፍኩ ነው” መድሃኔ ብርሃኔ

በዘንድሮ የውድድር ዓመት በደደቢት ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ ተስፋ ከተጣለባቸው ተጫዋቾች አንዱ ነው። በአዲስ አበባ ቄራ አከባቢ የተወለደው ታታሪው መድሃኔ ብርሃኔ በዚህ ዓመት በመስመር ተከላካይነት ፣ በፊት አጥቂነት እና መስመር ተጫዋችነት ተሰልፎ በግሉ ምርጥ ዓመት እያሳለፈ ይገኛል።

በበርካታ የሜዳ ክፍሎች መጫወት የሚችለው እና ከቅርብ ጨዋታዎች ወዲህ ቦታውን ቀይሮ ምርጥ ብቃቱን በማሳየት ጎሎችም በማስቆጠር ላይ የሚገኘው መድሃኔ ብርሃኔ ስለ ታዳጊ ቡድን ቆይታው ፣ ስለ እግር ኳስ ህይቱ እና ስለ ወቅታዊ አቋሙ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል።

የታዳጊ ቡድን ቆይታ…

የእግር ኳስ ህይቴ የሚጀምረው ሰፈር ውስጥ በነበረው ፕሮጀክት ነው ከዛ ቀጥሎ ራዕይ ወደሚባል ቡድን ነው ያመራሁት። ከዛ በኋላ ደግሞ ብዙ ነገር ወደተማርኩበት ደደቢት ታዳጊ ቡድን በአሰልጣኝ ኤልያስ ኢብራሂም አማካኝነት መጣሁ። የራዕይ ቆይታዬ በጣም ጥሩ ነበር፤ በተመሳሳይ የደደቢት ቡድናችንም በጣም ጥሩ ቡድን ነበር። ለዋንጫ የደረስንባቸው ግዜያቶች ነበሩ።
በሁሉም የታዳጊ ቡድን ቆይታዎቼ ብዙ ነገር ተምሬበታለው። በተለይ የደደቢት ታዳጊ ቡድን ቆይታዬ በዋንጫ ባይታጀብም በጣም አሪፍ ጊዜ ስለነበረኝ ብዙ ሳልቆይ ነበር ወደ ዋናው ቡድን ያደግኩት።

ዓምና በጥቂት ጨዋታዎች ላይ ተቀይሮ የመግባት እድል ብታገኝም በፕሪምየር ሊጉ ብዙ እድል ያገኘኸው ዘንንሮ ነው። ቆይታህን እንዴት ትገልፀዋለህ?

ዓምና በጥቂት ጨዋታዎች ተሳታፊ ነበርኩ።
ግን እንዲህ በተከታታይ መሰለፍ የጀመርኩት በዚህ ዓመት ነው። በመጀመርያ ዓመት ቆይታዬም ቡድናችን ጥሩ ባይሆንም በግሌ ብዙ ትምህርት ወስጄበታለው፤ ጥሩ ግዜም እያሳለፍኩ ነው። ከሁሉም ግን በርካታ ልምድ እየቀሰምኩበት ነው። በመጀመርያው ዙር በቡድናችን ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ባይኖሩም በሁለተኛው ዙር እንደ መድሃኔ ታደሰ እና ኃይሉ ገብረየሱስ የመሰሉ ተጫዋቾች በመምጣታቸው ከነሱም ልምድ እንድንወስድ ዕድል ከፍቶልናል። ባጠቃላይ ቆይታዬ በሁለት ጎኑ ነው የማየው። በአንድ በኩል ቡድናችን በወራጅ ቀጠና መገኘቱ በጣም ያስከፋኛል፤ በሌላው በኩል ደግሞ በቋሚነት ቡድኔን እያገለገልኩ በመሆኔ በጣም ደስተኛ ነኝ።

በአዲስ ቦታ ላይ በመሰለፍ ግቦች ማስቆጠር መጀመርህ ምን ስሜት ፈጠረብህ ?

ወሳኝ ጎሎች በማስቆጠሬ በጣም ደስ ነው ያለኝ። በርግጠኝነትም ጎሎች ማስቆጠሬን እቀጥልበታለው። መስመር ላይ መሰለፉ ተመችቶኛል።

በዚህ ዓመት በተከላካይነት ፣ በመስመር እና በአጥቂ ቦታ ላይ ተሰልፈሃል የቱ ቦታ ተመቸህ?

ሁሉም ቦታዎች ምርጫዎቼ ናቸው የኔ ምርጫ ይሄ ነው ማለት ይከብደኛል። ሁሉም ቦታዎች ላይ የመጫወቱ ብቃቱ አለህ ብሎ አሰልጣኜ ካሰለፈኝ የኔ ስራ አሰልጣኜ ባለኝ መሰረት መጫወት ነው።

ከዚ በፊት የተለየ ሚና ተሰጥቶህ ተጫውተህ ታውቃለህ?

አዎ። በራዕይ እና ታዳጊ ቡድን ቆይታዬ የፊት አጥቂ ሆኜ ተጫውቻለው፤ ጎሎችም አስቆጥር ነበር።
በተለይ በራዕይ ቆይታዬ በርካታ ግቦች አስቆጥር ነበር። በአንድ የውድድር ዘመን በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ፉክክር ውስጥ ገብቼ በአንድ ግብ ነበር የተበለጥኩት እና በዛን ሰዓት አጥቂ ሆኜ መጫወቴ በብዙ ረገድ ጠቅሞኛል።

የደደቢት የመጀመርያ ዙር ደካማ ውጤት ምክንያት ምን ነበር ትላለህ?

በመጀመርያ ደረጃ ቡድናችን በወጣቶች የተገነባ ስለሆነ የልምድ እጥረት ነበረን። ልምድ ያለው ተጫዋች በቡድናችን ውስጥ አለመኖሩ በጣም ጎድቶናል። ከዛ ውጭ በጣም ዘግይተን ወደ ቅድመ ውድድር መግባታችንም በጣም ጎድቶናል። ቡድናችን ጥሩ ሆኖ ሳለ ብዙ የዝግጅት ጊዜ ስላልነበረን ቶሎ መቀናጀት አልቻልንም እሱም ችግር ፈጥሮብናል።

ቡድናችሁ በአንፃራዊነት ከመጀመርያው ዙር በተሻለ መነቃቃት ላይ ነው ያለው እና ይህን በምን የመጣ ነው ትላለህ?

አሁን የተለየው ነገር ጥሩ የማሸነፍ ስነ-ልቦና ገንብተናል። ከዚህ በተጨማሪ የነበረን የልምድ ችግር የሚያቃልሉልን ልምድ ያላቸው መጥተዋል። ከዛ ባለፈ አሰልጣኛችን የሚከተለው አጨዋወት በጣም ውጤታማ በመሆኑ ብዙ እንድንለወጥ ረድቶናል። ብዙ ነገር እንድንለውጥ ያደረገን አሰልጣችን ዳንኤል ፀሃዬ ነው። ብትኩረት ነው የሚያሰራን የቡድኑ ስሜት ለመቀየር ብዙ ጥሩ ስራዎች ሰርቷል። በዚህ አጋጣሚ የመቐለ ከተማ ነዋሪዎች መጥተው እንዲያበረታቱን እጠይቃለው። አሁንም ስታድየም ድረስ በመምጣት እያበረታቱን ነው። በዚ መልካም ስራቸው እንዲቀጥሉ እና ከቡድናችን ጎን እንዲቆሙ እማፀናለው። ላለመውረድ የሚታገለው ቡድናችን ተባብረን እናትርፈው እላለው። እንደ ቡድንም ለኔ በግልም እየደወሉ ያበረታቱናል። ለዚህም በደደቢት ተጫዋቾች ስም በጣም ማመስገን እፈልጋለው

ከቤተሰብ ተለይተህ መጫወት የጀመርከው ዘንድሮ ነው። ተፅዕኖ አልፈጠረብህም?

ከቤተሰብ ርቆ መኖር በጣም ይከብዳል። ከዚህ በፊት ከእናቴ ተለይቼ አላውቅም። መጀመርያ ላይ ከሷ መለየት ከብዶኝ ነበር፤ በተለይ መጀመሪያ አከባቢ እናቴን ከአጠገቤ ማጣት በጣም ከብዶኝ ነበር። ግን ደግሞ ወደ መቐለ በመምጣት የግድ ስራዬ መስራት ስላለብኝ እና የምፈልገው ቦታ ላይ መድረስ ከፈለግኩኝ እንዲ አይነት መስዋዕትነት መክፈል እንዳለብኝ ከእናቴ ጋር ተናጋግሬ ነው የመጣሁት ለመልመድም ብዙ ግዜ አልፈጀብኝም።
መቐለ ለመልመድም ብዙ አልከበደኝም በጣም ደስ የሚል ከተማ እና ህዝብ ነው።

ቀጣይ እቅድህ ?

በጣም ጥሩ ተጫዋች ሆኜ ሀገራችን ላይ ባሉት ትላልቅ ቡድኖች መጫወት እና የሀገሬን ብሔራዊ ቡድን ላይ መጫወት ነው። ከዛ ባለፈው ውጪ ሀገር ሄጄ መጫወትም ፍላጎት አለኝ።

አርአያህ ማን ነው ማንን እያየህ ነው ያደግከው ? 

እንደ ዕድልም አርዓያዬ የምለው ተጫዋች በአጠገቤ ነበር የሚጫወተው ፤ አስራት መገርሳን እያደነቅኩ ነው ያደግኩት። እሱን በቅርበት ማየቴ በብዙ ነገር ጠቅሞኛል ፤ ብዙ ነገርም ተምሬበታለው። እሱም ብቻ ሳይሆን ከነጌታነህ ከበደ ፣ ሥዩም ተስፋዬ ፣ ብርሃኑ ቦጋለ እና ሽመክት ጉግሳ ብዙ ነገር ተምርያለው ብዙ ልምድም ቀስሚያለው።

ከሀገር ውስጥ የማን አድናቂ ነህ ?

ከሀገር ውስጥ የጌታነህ ከበደ አድናቂ ነኝ። ወሳኝ ጎሎች አስቆጥሮ ቡድን ይዞ መውጣት የሚችል ትልቅ አጥቂ ነው የሱ አድናቂ ነኝ።

ከጎኑ መጫወት የምትፈልገው ተጫዋች ማነው?

ከአጠገባቸው ሆኜ ብጫወት ብዬ የምመኛቸው ተጫዋቾች የኢትዮጵያ ቡናው ሄኖክ ካሳሁን እና የመቐለ 70 እንደርታው ሀይደር ሸረፋ ናቸው። እነሱ ሲጫወቱ ማየት ደስ ይለኛል ኳስ አቅልለው ነው የሚጫወቱት። በተጨማሪም ሄኖክ ካሳሁን የሰፈሬ ልጅ ነው እና ሲጫወት በቅርበት እያየሁት ስላደኩ ከሱ ጎን ብጫወት ደስ ይለኛል።

ማመስገን የምትፈልጋቸው…

መጀመርያ እዚህ ያደረሰኝ ፈጣሪን አመሰግናለሁ። በመቀጠል እናቴ አልጋነሽ ሀጎስ እና ወንድሞቼ ጎይትም ብርሃኔ እና ኤፍሬም ክፍሌን በጣም ማመስገን እፈልጋለው። ከዚህ በተጨማሪ የታዳጊ ቡድን አሰልጣኞቼ አክረም ዓብዱልቃድር ፣ ኤልያስ ኢብራሂም እና ብዙ ነገር ያስተማረኝ አሰልጣኝ አስራት ኃይሌን ማመስገን እፈልጋለው። ከታዳጊ በድን ወደ ዋናው ቡድን በአስራት ሃይሌ አማካይነት ነው ያደግኩት ከሱ በርካታ ነገር ተምርያለው። በሱ ስር ጥቂት ወራትን ብቻ መሰልጠኔ ዕድለኛ አደለሁም ፤ ብዙ ጊዜ ብቆይ ከዚህ የበለጥ ብዙ ትምህርት እቀስም ነበር።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡