ጳውሎስ ጌታቸው ራሳቸውን ከባህር ዳር ከተማ አሰልጣኝነት አነሱ

ዛሬ ከተደረጉ የ22ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች መካከል አንዱ የሆነው የባህር ዳር ከተማ እና የደቡብ ፓሊስ ጨዋታ ስድስት ጎሎች ተቆጥረውበት 3-3 ተጠናቋል።
በጨዋታው ሁለት ጎሎችን አስቆጥረው ሲመሩ የነበሩት የጣናው ሞገዶቹ በተከታታይ ሶስት ጎሎች ተቆጥረውባቸው እስከ 81ኛው ደቂቃ ድረስ 3-2 ሲመሩ ቆይተዋል። በዚህ ወቅት በስታዲየሙ የነበሩት ደጋፊዎች የአሰልጣኙን እና የአንድ አንድ ተጨዋቾችን ስም በማንሳት ተቃውሞ ሲያሰሙ ተደምጧል። ተቀይሮ ወደ ሜዳ በገባው እንዳለ ደባልቄ የግምባር ኳስ አቻ በመሆን ጨዋታቸውን ያጠናቀቁት ባህር ዳሮች ከደጋፊዎች እየተሰነዘረ የነበረው ተቃውሞ ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላም ቀጥሎ ተደምጣል። በተለይ አሰልጣኙ ላይ ያነጣጠረው የተቃውሞ ድምፅ አሰልጣኙ ራሳቸውን እንዲያገሉ እንዳደረገ ተገምቷል።

ጨዋታው ከተጠናቀቀ ከ30 ደቂቃዎች በኋላ ለብዙሃን መገናኛዎች ቃላቸውን የሰጡት ጳውሎስ ጌታቸው “እስካሁን አብሮኝ ለነበረ ሁሉ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። ከዚህ በኋላ ግን በቃኝ።” በማለት ራሳቸውን ከኃላፊነታቸውን ማንሳታቸውን አረጋግጠዋል።

አሰልጣኙ ነገ ለስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የልቀቁኝ ደብዳቤ በማስገባት ከክለቡ እንደሚለያዩም አስረድተዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡