የሱዳን ፕሪምየር ሊግ በሃገሪቱ ላይ ባለው አለመረጋጋት ምክንያት ላልተወሰነ ግዜ ተራዘመ።
በምስራቅ አፍሪካ ውስጥ ካሉት ሊጎች የተሻለ የፉክክር መንፈስ እና የክለቦች የጥራት ደረጃ ያለው የሱዳን ፕሪምየር ሊግ በሃገሪቱ ላይ ባለው ወቅታዊ አለመረጋጋት ምክንያት ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሟል።
ባለፈው ሳምንት አልሜሪክ ሂላል አል ኦቢያድን ባስተናገደበት ጨዋታ ላይ የመሐል ዳኛው የሜሪኩን ባክሪ አልመዲናን በቀይ ካርድ ካሰነበቱት በኋላ በተከሰተው የሜዳ ውስጥ ስርዓት አልበኝነት የሀገሪቱን እግር ኳስ ፌደሬሽን ይህን ውሳኔ እንዲወስን ምክንያት እንደሆነ እየተገለፀ ይገኛል።
ፕሪምየርሊጉ መቼ እንደሚቀጥል እስካሁን ይፋዊ የሆነ መግለጫ ባይሰጥም ስለ ሱዳን እግር ኳስ በአልጀዚራ እና ቢቢሲ የሚፅፈው ዓብዱል ሙሳ የሃገሪቱን እግር ኳስ ፕሬዝደንት ከማል ሻዳድ በምንጭነት ጠቅሶ በሃገሪቱ ላይ ተስፋ ሰጪ ሰላም ከታየ ሊጉ ቀጣይ ሳምንት አል ሾርጣ ከአልሂላም በቃዳሪፍ በሚያደርጉት ጨዋታ ሊጀምር እንደሚችል ገልፀዋል።
ዑመር አልበሽርን ከ29 ዓመታት በኃላ በህዝብ ዓመፅ ከስልጣን ያወረደችው ሱዳን የሊብያ እና ግብፅ እግር ኳስ ዕጣ እንዳይደርሰው እየተፈራ ይገኛል። እንደሚታወቀው የሰሜን አፍሪካዎቹ ሀገራትተመሳሳይ የህዝብ ዓመፆች ካስተናገዱ በኋላ የእግር የኳሳቸው ደረጃ ወርዶ ክለቦቻቸው እና ብሄራዊ ቡድኖቻቸው ከትላልቅ ውድድሮች ርቀው እንደቆዩ የቅርብ ግዜ ትውስታ ነው።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡