ሪፖርት | ሸገር ደርቢ ያለ ጎል ተጠናቋል

በ23ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተጠባቂ የነበረው የሸገር ደርቢ ያለ ጎል ተጠናቋል፡፡

ዩጋንዳዊው ግብጠባቂያቸው ኢስማኤል ዋቴንጋን በሁለተኛው ዙር ለመጀመሪያ ጊዜ በቡድን ስብስባቸው ውስጥ ያካተቱት ባለሜዳዎቹ ኢትዮጵያ ቡናዎች ባሳለፍነው ሳምንት በአዳማ ከተማ ከሜዳው ውጭ 1ለ0 ከተረታው የመጀመርያ ተሰላፊ ውስጥ አጥቂውን ፍፁም ጥላሁን በቃልኪዳን ዘላለም እንዲሁም አህመድ ረሺድን በኃይሌ ገ/ተንሳይ ተክተው ወደ ጨዋታው ገብተዋል፡፡ በአንጻሩ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሳምንቱ መጀመሪያ የሊጉን መሪ መቀለ 70 እንደርታን 1ለ0 ከረታው ስብስብ ውስጥ ናትናኤል ዘለቀን በታደለ መንገሻ በመተካት ጨዋታውን ጀምረዋል፡፡

እንደወትሮው የሁለቱ ግንኙነት ሁሉ ብዙም ሳቢ ባልነበረው የመጀመሪያው አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡና ምንም እንኳን በጠሩ የግብ እድሎች ባይታጀብም ከተጋጣሚያቸው በተሻለ የመሀል ሜዳ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ነበራቸው። በአንጻሩ ጊዮርጊሶች በአመዛኙ ከተከላካዮች በቀጥታ ፊት መስመር ላይ ወደ ግራ መስመር አድልቶ ይንቀሳቀስ ወደነበረው አቤል ያለው በሚሻገሩ ረጃጅም ኳሶች ተወስነው ሲንቀሳቀሱ ተስተውሏል፡፡

በኢትዮጵያ ቡናዎች በመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ኃይሌ ገ/ተንሳይ ከቅጣት ምት ከሞከራት ኳስ በተጨማሪ ቃልኪዳን ዘላለም ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ ተቆጣጥሮ አስቆጠረ ተብሎ ሲጠበቅ ያመከናት ኳስ ተጠቃሽ ሙከራ ነበረች፤ በቅዱስ ጊዮርጊሶች በኩል ደግሞ በተመሳሳይ ከፍሪምፓንግ ሚንሱ የቅጣት ምት ሙከራ በተጨማሪ ሪቻርድ አርተር ከሳጥን ውጪ በቀጥታ ሞክሮ ወደ ውጪ የወጣበት ኳስ ተጠቃሽ ነበሩ፡፡

በመጀመሪያው አጋማሽ በተለይ ኢትዮጵያ ቡናዎች ከወትሮው በተለይ ኃይልን የቀላቀለ የጨዋታ አቀራረብ መርጠው በመምጣታቸው በርከት ያሉ ጥፋቶችን ሲፈፅሙ ተስተውሏል። በተለይም ፈጣኑን አቤል ያለውን ለማቆም ሆነኛ አማራጭ ሆኗቸው ታይቷል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊሶች ሪቻርድ አርተር ላይ በተፈፀመበት ጥፋት የፍፁም ቅጣት ምት ይገባኛል ጥያቄ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ሁለተኛ አጋማሽ በንጽጽር ከመጀመሪያው የተሻለ የመሸናነፍ ተነሳሽነት ተስተውሎበታል፡፡ በ59ኛው ደቂቃ በጨዋታው በተገኘችው ብቸኛ የጠራ የግብ አጋጣሚ አስራት ቶንጆ በግሩም ሁኔታ ያሳለፈለትን ኳስ ሁሴን ሻባኒ ከቅዱስ ጊዮርጊሱ ግብጠባቂ ማታሲ ጋር 1ለ1 ተገናኝቶ ያመከናት የጨዋታው የተሻለችው ሙከራ ነበረች፡፡

ኢትዮጵያ ቡናዎች በተሻለ የኳስ ቁጥጥርና በፍጥነት ወደ ተጋጣሚያቸው ሳጥን በተደጋጋሚ መድረስ ቢችሉም በተጫዋቾች ደካማ ውሳኔ አሰጣጥ የተነሳ ፍሬያማ አልነበሩም። በአንጻሩ አሜ መሐመድ እና በኃይሉ አሰፋን በሁለተኛው አጋማሽ ቀይረው ካስገቡ በኋላ በተሻለ ከመስመር በሚጣሉ ኳሶች ለመጠቀም የሞከሩት ጊዮርጊሶች በርካታ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚ ቢያገኙም መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ በሁለተኛው አጋማሽ ሰዓት በማባከን የቢጫ ካርድ የተመለከተው የኢትዮጵያ ቡናው ግብጠባቂ ወንድወሰን አሸናፊ ከሳጥን ውጭ ኳስ በእጅ በመንካቱ በሁለት ቢጫ ከሜዳ ሊወጣ ችሏል፡፡

ጨዋታው 0-0 በሆነ የአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለዋንጫ የሚያደርገው ጉዞ እንቅፋት ሲገጥመው ደረጃውም ወደ አራተኛ ዝቅ ብሏል። ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ወደ 6ኛ ደረጃ በአንድ ከፍ ማለት ችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡