ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ደቡብ ፖሊስ ከ አዳማ ከተማ

 ከዛሬ የ23ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ውስጥ በደቡብ ፖሊስ እና አዳማ ከተማ ጨዋታ ዙሪያ የሚነሱ ነጥቦችን እንዲህ ተመልክተናቸዋል።

በሀዋሳው ሰው ሰራሽ ስታድየም ዛሬ 09፡00 ላይ ደቡብ ፖሊስ እና አዳማ ከተማ ይገናኛሉ። ባህር ዳር ላይ በስምንት ደቂቃዎች ልዩነት ሦስት ግቦችን ማስቆጠር ችለው የነበሩት ደቡብ ፖሊሶች ሙሉ ነጥብ ማሳካት ሳይችሉ የመከላከያን ቦታ ወስደው ወደ ወራጅ ቀጠናው በመግባታቸው ከዚህ ጨዋታ ወሳኝ የሆነ ውጤትን ይፈልጋሉ። ወደ አደጋው ዞን እንዳይቀርብ ያሰጋ የነበረው አዳማ ከተማ ሳምንት ኢትዮጵያ ቡናን በመርታት ከሦስት ተከታታይ ሽንፈቶች አገግሟል። መሀል ላይ የሚረጋ የሚመስለው ቡድኑ በአነስተኛ ጫናም ነው ወደ ሀዋሳ ያመራው።

ምንም እንኳን በድል ባይመለስም የባህር ዳሩን ጨዋታ የተወጣበት መንገድ ለደቡብ ፖሊስ በውድድሩ አጋማሽ አግኝቶት የነበረውን መነቃቃት መልሶ ሊያጎናፅፈው ይችላል። ከአበባው ቡታቆ መሰለፍ አጠራጣሪ መሆን በቀር ቀሪ ስብስቡ ከጉዳት እና ቅጣት ነፃ የሆነለት ቡድኑ በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ ይበልጥ ጫና ፈጥሮ በሚጫወትበት አቀራረቡ አዳማን እንደሚያስተናግድ ይጠበቃል። በርግጥ ግቦችን ካገኘ ውጤት ወደማስጠበቁ ሊያደላ ቢችልም እንደወትሮው ለመስመር አጥቂዎቹ የማጥቃት ነፃነትን በመስጠት በፈጣን ሽግግር ወደ አዳማ ግብ ክልል ደጋግሞ ለመድረስ መሞከሩ አይቀርም። ሆኖም አዳማ ከተማ በራሱ ሜዳ ላይ መቆየትን ከመረጠ በቅብብሎች ሰብሮ መግባት ለደቡብ ፖሊሶች ቀላል ላይሆን ይችላል።

አዳማ ከተማ ምንም እንኳን በተሻለ ነፃነት ጨዋታውን ቢያደርግም የቁልፍ ተጫዋቾቹ አለመኖር በሚፈልገው መጠን ክፍት ሆኖ ጫና በመፍጠር እንዳይጫወት ሊያደርገው ይችላል። ከሁሉም በላይ የከነዓን ማርክነህ ወደ ሀዋሳ አለመጓዝ በዚህ ረገድ ትልቁን ድርሻ ሲይዝ ዳዋ ሆቴሳ ፣ አንዳርጋቸው ይላቅ እና ብዙአየሁ እንዳሻውም በጉዳት ሳቢያ ከኑድኑ ጋር እንደሌሉ ይታወቃል። የኳስ ቁጥጥርን መሰረት ያደረገ አቀራረብ ሊኖራቸው እንደሚችል የሚጠበቁት አዳማዎች ጥሩ የማጥቃት ተሳትፎ በማድረግ የሚታወቀው የመስመር ተከላካያቸው  ሱለይማን ሰሚድ ከቅጣት መመለስ ግን ጥሩ ዜና ይሆናል። በተለይም አበባው ቡታቆ ከጨዋታው ውጪ ከሆነ ሱለይማን በተሻለ ሁኔታ ወደ ተጋጣሚው ሳጥን ገፍቶ በመጫወት የአዳማን የቀኝ መስመር ጥቃት ውጤታማ ሊያደርገው ይችላል። በጥቅሉ ግን ቡድኑ አማካይ ክፍል ላይ ከነዓንን በሌለበት ከፖሊስ በተሻለ ኳስ የመያዙ ነገር አጠራጣሪ ይመስላል። 

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ስድስት ጊዜ ተገናኝተዋል። በውጤቱም አዳማ ከተማ ሦስት ደቡብ ፖሊስ ደግሞ  ሁለት ጊዜ ሲያሸንፉ አንድ ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። በስድስቱ ጨዋታዎች ከተቆጠሩት 11 ግቦች ውስጥም ስድስቱ የአዳማ አምስቱ ደግሞ የደቡብ ፖሊስ ናቸው።

– በአዲስ አበባ ስታድየም ከድቻ ጋር የተገናኘበትን ጨዋታ ሳይጨምር ሀዋሳ ላይ 11 ጨዋታዎችን ያደረገው ደቡብ ፖሊስ ሦስቴ ድል ሲቀናው በቀሪዎቹ ስምንት ጨዋታዎች ግን ምንም ነጥብ ማሳካት አልቻለም።

– አዳማ ከተማ እስካሁን ከሜዳው ውጪ ካደረጋቸው 11 ጨዋታዎች መከላከያን በገጠመበት ጨዋታ ብቻ ነው ድል የቀናው። ከዛ ውጪ አምስት ጊዜ ሲሸነፍ አምስቴ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

                

                          
ዳኛ

– ጨዋታው ዘንድሮ ወደ ሊጉ ለመጣው ዮናስ ካሳሁን ስድስተኛው ይሆናል። በመሀል ዳኝነት በተሰየመባቸው አምስት ጨዋታዎች 20 የማስጠንቀቂያ ካርዶችን መዟል። 

ግምታዊ አሰላለፍ

ደቡብ ፖሊስ (4-3-3)

ሀብቴ ከድር

አናጋው ባደግ – ደስታ ጊቻሞ  – አዳሙ መሀመድ – አበባው ቡታቆ

 ዘላለም ኢሳያስ – ዮናስ በርታ – ኪዳኔ አሰፋ

የተሻ ግዛው – ኄኖክ አየለ – ላኪ ሳኒ

አዳማ ከተማ ( 4-2-3-1) 

ሮበርት ኦዶንካራ 

ሱለይማን ሰሚድ – ምኞት ደበበ – ቴዎድሮስ በቀለ – ሱለይማን መሀመድ

ብሩክ ቃልቦሬ – ኢስማኤል ሳንጋሪ

ኤፍሬም ዘካርያስ – አዲስ ህንፃ – ሙሉቀን ታሪኩ

ቡልቻ ሹራ