ኤሌክትሪክ 0-1 ቅዱስ ጊዮርጊስ ፡ የጨዋታ ትንተና

 

በዮናታን ሙሉጌታ

በአነጋጋሪ ሁኔታ ለ40 ቀናት ተቋርጦ የነበረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ትላንት በሦስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቀጥሎ ሲውል የአምናው ሻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ ተመልካቹን ከመቀመጫው አስነስታ ባስጨበጨበችው የአሉላ ግርማ ድንቅ ጐል በመታገዝ ኤሌክትሪክን 1 ለ 0 በሆነ ውጤት ለማሸነፍ ችሏል፡፡  ሶከር ኢትዮጵያም እንደተለመደው በሜዳ ላይ የነበረውን ታክቲካዊ ዳሰሳ እንደሚከተለው አቅርባላችኋለች፡፡

በምስል አንድ ላይ እንደሚታየው ኤሌክትሪክ የተጠቀመበት ፎርሜሽን በመከላከል ላይ ያተኮረ ነበር፡፡  ይኸውም ከቀኝ እና ከግራ የሚነሱት ኳሶችን ለመከላከል ታስቦ የተደረገ ነው፡፡ በተጨማሪም ከተከላካዩ ፊት ያሉት ሁለቱ አማካዮች ቡድኑ በመሀል ሜዳ እንቅስቃሴ ከተጋጣሚው የአጥቂ አማካይ በኩል ሊፈጠሩ የሚችሉበትን የጎል አጋጣሚወች መግታትንና በማጥቃት ጊዜም የእንቅስቃሴው አስጀማሪ የመሆን ሚና ተስቷቸው ነበር፡፡

ከሁለቱ አማካዮች ፊት የነበረው ማናዬ ፋንቱ ከአጥቂዎቹ ጀርባ በመሆን የአጥቂ አማካይነቱን ሚና ወስዷል፡፡ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ቡድኑ ሙሉ ለሙሉ በማጥቃት ላይ የተመሰረተ አጨዋወትን ተከትሏል፡፡ ቡድኑ በ4፡3፡3 ፎርሜሽን ከአራቱ ተከላካዮች ፊት ተካፋዩ አለባቸውን ሲጠቅም ከሱ ጐን አሉላ ግርማን እንዲሁም ምንያህል ተሾመን ከሁለቱ አማካዮች ፊት በማድረግ ከአጥቂው ክፍል ጀርባ እንዲጫወት አደርጓል፡፡  ከፊት ከነበሩት ሦስት አጥቂዎችም በሁለቱ መስመሮች ላይ የተሰለፉት በኃይሉና ብሪያን የቡድኑ ቁልፍ የማጥቃት እንቅስቃሴ መነሻዎች ነበሩ፡፡

image 2

በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ በተለይም በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ ተመጣጣኝ የሆነ እንቅስቃሴ ከሁለቱ ቡድኖች ታይቷል፡፡  ሁለቱም ድድኖች በመልሶ ማጥቃትና በተሻጋሪ ኳሶች ጥቃት ለመሰንዘር ሙከራም ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡

የኤሌክትሪኮች የኋላ ክፍል በቁጥር በመብዛት የቅዱስ ጊዮርጊስን ወደጐን በሜዳው ስፋት የተለጠጠ አጨዋወትን እና ከሁለቱ መስመሮች የሚነሱ ተሻጋሪ ኳሶችን የማክሸፍ ሀሳብ የተሳካ ነበር ማለት ይቻላል፡፡

የኤሌክትሪክ የመስመር ተከላካዮች ከሁለቱ አማካዮች ጋር በመሆን የጊዮርጊስን ተሻጋሪ ኳሶች እንዳይነሱ በማድረጉ ረገድ እምብዘም ባይሳካላቸውም ነገርግን ለጊዮርጊስ የመስመር አጥቂዎች ክፍተት አልሰጡም ነበር፡፡ ለዚህም ይመስላል የቅዱስ ጊዮርጊስ ረጃጅም ኳሶች በአብዛኛው ያንሱ የነበረው ከሁለቱ የመስመር ተከላካዮች ነበር፡፡ እነዚህ አደገኛ ረጃጅም ኳሶች ወደ ኤሌክትሪክ ሳጥን ውስጥ ሲጣሉም ሦስቱ የመሀል ተከላካዮች በተጋጣሚያቸው አጥቂ ላይ በሚኖራቸው የቁጥር ብልጫ ምክንያት የታለመላቸውን አደጋ ከማድረሳቸው በፊት ይቋርጡ ነበር፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋግሞ በነዚህ ሁለት መስመሮች ክፍተቶችን ለመጠቀምም ሞክሯል፡፡ ለዚህም ይመስላል የኤሌክትሪክ የግራመስመር ተከላካይ የነበረው አሰልፈው መኮንን ለማጥቃት ወደፊት በሚሳብበት ጊዜ ይተወው የነበረው ክፍተት ለመጠቀም ጊዮርጊሶች ብሪያንን እና በኃይሉን ቦታ ለመቀየር የጐላ እድሎችን ለማግኘት ሞክረው የነበረው፡፡ ነገር ግን በአብዛኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የቅዱስ ጊዮርጊስ መስመር የተፈለገውን ያህል የማግባት አጋጣሚዎች መፍጠር አልቻለም፡፡

በአዲስ እና በብሩክ የበላይነት የተወሰደበት ምንያህል ተሾመ የፈጠራ ብቃቱን ተጠቅሞ ከአማካይ ክፍል የሚነሳ የጐል ዕድል ለመፍጠር ተቸግሮም ታይቷል፡፡ ለዚህም እንደምክንያት ሊወሰድ የሚችለው የቡድኑ የማጥቃት ስትራቴጂ መነሻዎች የነበሩት ሁለቱ መስመሮች መሆናቸው ነው፡፡ ይኸም ምንያህል በመሀል ላይ እንዲዋልል አድርጐታል፡፡  ጊዮርጊሶች በሁለተኛው አጋማሽ አበባው ቡታቆን ወደሜዳ ሲያስገቡም የተጨዋቹን የተመጠኑ ረጅም ኳሶች ለማግኘትና ዕድሎች ለመፍጠር በማሰብ ይመስላል ይኸም ቡድኑ በተሻጋሪ ኳሶች ላይ እምነት መጣሉን በሁለተኛው አጋማሽም መቀጠሉን ይጠቁማል፡፡

በመከላከሉ ላይ ተጠምዶ ያመሸው ኤሌክትሪክ በመልሶ ማጥቃት አልፎ አልፎ ወደ ተጋጣሚው ሳጥን ውስጥ ለመግባት ጥረት አድርጓል፡፡ ነገር ግን ቡድኑ በመሀል ሜዳ ላይ በተወሰደበት የቁጥር ብልጫ ምክንያት ስኬታማ አልሆነም፡፡  ሁለቱ የመስመር ተከላካዮች በመከላከል ላይ በማተኮራቸው ምክንያት እንዲሁም አዲስ እና ብሩክም ወደተከላካዩ ቀርበው ይጫወቱ የነበረ በመሆኑ ለኤክትሪክ የፊት አጥቂዎች ብቸኛው የመጨረሻ የኳስ ምንጫቸው የነበረው ከበስተኋላቸው ማናዬ ፋንቱ ነበር፡፡  ነገር ግን በእለቱ በጥሩ አቋም ላይ በነበረው ተስፋዬ አለባቸው እና አስገራሚዋን ጐል ከመረብ ባሳረፈው አሉላ ግርማ አማካይነት የኤክትሪክ የመሀል ክፍል የታሰበውን ጫና መፍጠር አልቻለም፡፡  ለዚህም ይመስላል የኤሌክትሪክ የፊት አጥቂዎች ፍፁምና ፒተር ኳስ ለማግኘት ወደጐን እና ወደኋላ ይሳቡ የነበረው፡፡

በዚህ መልኩ የኤሌክትሪክ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴና የቅዱስ ጊዮርጊስ ከተሻጋሪ ኳሶች የጐል ዕድል የመፍጠር ሙከራዎች በየቡድኖቹ የተሳኩ የመከላከል ሂደቶች እየከሸፉ እስከ አሉላ ግርማ የ59ኛ ደቂቃ ጐል ድረስ ጨዋታው ቀጥሏል፡፡

 

image 3

ከግቧ መቆጠር በኋላ ጨዋታው ለየት ያለ መልክና የተሻለ ፍሰት ተስተውሎበታል፡፡  የዚህም ምክንያት የኤሌክትሪክ የጨዋታ ቅርፅ ከ5፡3፡2 ወደ 4፡3፡3 መቀየሩ ነው፡፡ (ምስል 3ን ይመልከቱ)

ኤሌክትሪክ ሀብታሙ መንገሻን በሦስተኛ አጥቂነት ቀይረው ካስገቡ በኋላ የተሻለ ወደፊት ለመንቀሳቀስ ሞክረዋል፡፡  ከዚህም ጐን ለጐን በኃይሉ ተሻገርና ዋለልኝ ገብሬ ብሩክ እና ማናዬን በመተካት ወደሜዳ መግባታቸው ለቡድኑ የማጥቃት ፍላጐት ማሳያ ተደርጐ የሚወሰድ ነው፡፡ ይህ ቅያሪ ቡድኑ በመሀል ሜዳ በተጋጣሚው የተወሰደበትን ብልጫም ለማስተካከልም ይረዳው ነበረ፡፡

ኤሌክትሪኮች ወደ ቀኝ ባመዘነ የማጥቃት እንቅስቃሴ በጫወታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ጫና ፈጥረው ታይተዋል የቆሙ ኳሶች ዕድሎችንም አግኝተዋል ወደጎልነት መቀየር ግን አለቻሉም፡፡ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በጨዋታው ላይ ተፅዕኖ መፍጠር የተሳነውን ምንያህልን በምንተስኖት በመተካት ለውጥ የተደረገበትን እና ወደ ማጥቃት የተሳበውን የኤሌክትሪክን አማካይ ክፍል ንፁህ የማግባት ዕድል እንዳይፈጥር ለመቆጣጠር ሞክሯል፡፡

በተጨማሪም የኤሌክትሪክ የተከላካይ መስመር ቁጥር ወደ አራት ዝቅ ማለቱን ተከትሎ የጐል አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ቁጥር አቡበከር ሳኒን በስተቀኝ በኩል በበኃይሉ አሰፋ ምትክ አስገብቷል፡፡

የኤሌክትሪክ ተከላካዮች ቅርፅን መለወጥ ተከትሎ የአማካዮችም እንደመጀመሪየው ለተከላካዮቹ አብዝቶ ሽፋን ከመስጠት ይልቅ ወደፊት በመሳብ ወደተጋጣሚያቸው ሳጥን እየተጠጉ ዕድሎችን ለመፍጠር መሞከር ለቅዱስ ጊዮርጊስ የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ፈጥሮላቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ከሁለቱም ቡድኖች በኩል ሌላ ጐል ሳንመለከት ጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ 1 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በመጪው ሳምንት ቀጥሎ ሲካሄድ ዕሮብ ዘጠኝ ሰዐት ላይ ቅ/ጊዮርጊስ በሜዳው ድሬዳዋ ከነማን ሲያስተናግድ ሀሙስ 11፡30 ላይ ኤሌክትሪክ ኢትዮጵያ ቡናን ይገጥማል፡፡

ያጋሩ