በ23ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ትግራይ ስታድየም ላይ ደደቢትን የገጠመው ፋሲል ከነማ 5-1 በማሸነፍ ነገ ጨዋታውን ከሚያደርገው መሪው መቐለ ያለውን ልዩነት ማጥበብ ችሏል።
ደደቢቶች ባለፈው ሳምንት በወልዋሎ ሽንፈት ከገጠመው ቡድናቸው ዳዊት ወርቁ ፣ መድሃኔ ታደሰ ፣ አሸናፊ እንዳለን በኃይሉ ገብረ የሱስ ፣ ፋሴይኒ ኑሁ እና ኤፍሬም ጌታቸው ተክተው ሲገቡ በተመሳሳይ ዐፄዎቹ ድሬዳዋ ኣሸነፈው ስብስባቸው ሰለሞን ሐብቴ እና ኢዙ አዙካን በአብዱራህማን ሙባረክ እና ሽመክት ጉግሳ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።
ባለፈው ሳምንት ህይወቱን ላጣው የዋልታ ፖሊስ ትግራይ ተጫዋች በተደረገ የገንዘብ ማሰባሰብ የተጀመረው ጨዋታው በጥሩ ፍጥነት ሲጀምር ግብ ለማስተናገድም ብዙ ደቂቃ አልፈጀበትም። በአራተኛው ደቂቃ በሳጥኑ ቀኝ በኩል የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ቅጣት ምት አምሳሉ ጥላሁን በግሩም ሁኔታ በማስቆጠር ዐፄዎቹን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። የግቡ መቆጠርን ተከትሎ በፋሲል ተቀያሪ ተጫዋቾች ላይ በተወረወሩ ቁሳቁስ ምክንያት ጨዋታው ለጥቂት ደቂቃዎች ተቋርጦ ነበር።
ከግቡ መቆጠር በኋላ ተረጋግቶ መጫወት ያቃታቸው ባለሜዳዎቹ ለበርካታ ስህተቶች ሲዳረጉ በአንፃሩ ፋሲሎች ከሁለቱ የአጥቂ አማካዮች በሚነሱ ኳሶች በርካታ ዕድል ፈጥረዋል። በተለይም ኤፍሬም ዓለሙ በራሱ ጥረት ገብቶ ያደረጋት ሙከራ እና ሙጂብ ቃሲም ከሱራፌል ዳኛቸው የተላከለትን ኳስ መትቶ አቡዋላ ከግቡ መስመር የመለሳት ኳስ በፋሲል በኩል የሚጠቀሱ ሙከራዎች ናቸው።
በሃያ አራተኛው ደቂቃ ላይ አብዱልራህማን ሙባረክ ከመሃል ሜዳ የተሻገረችለትን ኳስ ከተከላካዮች ሾልኮ በመሄድ ከግብ ጠባቂው በላይ በመምታት አስቆጥሮ የዐፄዎቹን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረፍ ችሏል። በጨዋታው ቶሎ ቶሎ ወደ ደደቢት ግብ ክልል ሲደርሱ የታዩት እንግዶቹ በመጀመርያው አጋማሽ መጨረሻ ደቂቃዎች ተጭነው በመጫወት በሙጂብ ቃሲም አማካኝነት ሁለት እጅግ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች አድርገዋል። በተለይ አጥቂው የደደቢት ተከላካዮች ስህተት ተጠቅሞ ገብቶ በውሳኔ አሰጣጥ ችግር ያመከናት አስቆጪ ኳስ እጅግ ለግብ የቀረበች ነበረች።
በመጀመርያው አጋማሽ የተወሰኑ ተጫዋቾች በግል ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ ውጭ እንደ ቡድን ጥሩ መንቀሳቀስ ያልቻሉት ደደቢቶች ጥቂት ዕድሎች መፍጠር ችለው ነበር። ፉሴይኒ ኑሁ ከቅጣት ምት ያደረጋት ሙከራ እና ዓብዱልዓዚዝ ዳውድ አቡዋላ ያሻማውን ኳስ ተጠቅሞ በግንባር ያደረጋት ሙከራ ሰማያዊዎቹ ካደረጓቸው ሙከራዎች ይጠቀሳሉ።
ሳቢ ያነበረው እና በብዙ የሜዳ ውስጥ እሰጣ ገባዎች እና ስርዓት አልበኝነት እጅጉን ዘግይቶ ለመጠናቀቅ የተገደደው ሁለተኛው አጋማሽ ይህ ነው የሚባል ጥሩ የእግር ኳስ ፍሰት የታየበት አልነበረም። በ50ኛው ደቂቃ ላይ ሽመክት ጉግሳ ሰይድ ሐሰን በግሩም ሁኔታ ከመስመር ያሻማለትን ኳስ ተጠቅሞ ግብ ማስቆጠር ሲችል ከግቡ መቆጠር በኃላም አማካዩ ለቀድሞ ክለቡ ክብር ደስታው ከመግለፅ ተቆጥቧል።
በጨዋታው የደደቢትን የመከላከል አደረጃጀት አልፈው ለመሄድ ያልተቸገሩት እንግዶቹ ፋሲሎች ከግቡ መቆጠር በኃላ ብዙም ሳይቆዩ አራተኛ ግብ ለማከል ተቃርበው ነበር፤ አብዱራህማን ሙባረክ ከመስመር በጥሩ ሁኔታ ይዞ ገብቶ ያደረጋትን ሙከራ ሙሴ ዮሃንስ አድኗታል። እንግዶቹ ፋሲሎም ምንም እንኳ እንደ መጀመርያው አጋማሽ በርካታ ዕድሎች ባይፈጥሩም በኳስ ቁጥጥር ድርሻ ግን ከባለሜዳዎቹ የተሻሉ ነበሩ በዚህም በስልሳ አራተኛው ደቂቃ ላይ የሙጂብ ቃሲም የግል ጥረት የታከለባት አራተኛውን ግብ ማስቆጠር ችለዋል። አጥቂው ከተከላካዮች መሃል ሆኖ የተቀበላትን ኳስ በጥሩ ፍጥነት ከተከላካዮቹ አምልጦ በመሄድ ለኤፍሬም ዓለሙ አቀብሎት አማካዩ በጥሩ አጨራረስ ማስቆጠር ችሏል።
ከግቡ መቆጠር በኃላ በፋሲል የተቀያሪ ወንበር ተጫዋቾች ላይ መወርወር የጀመረው ቁስ እና ድንጋይ በመባባሱ ምክንያት ጨዋታው ለአንድ አንድ ሰዓት እንዲቋረጥ ያስገደደ ሲሆን በዚህም በተወሰኑ የሁለቱ ቡድን ተጫዋቾች ላይ የመፈንከት ጉዳት ደርሷል። ሁኔታዎች ተረጋግተው፤ ተመልካቾች ከስታድየም ለቀው በዝግ የቀጠለው ጨዋታም የተቀዛቀዘ ስሜት እና እጅግ ዘገምተኛ የጨዋታ ፍጥነት የታየበት ነበር።
በሰባ ዘጠነኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው አጥቂው ሙጂብ ቃሲም የደደቢት ተከላካዮች ስህተት እና ትኩረተ ማጣት ተጠቅሞ ያገኛትን ኳስ በማስቆጠር የቡድኑን መሪነት ወደ አምስት ከፍ ማድረግ ችሏል።
በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች አጨዋወታቸው ላይ ለውጥ በማድረግ በአጥቂ ክፍል ላይ ፉሴይኒ ኑሁ እና መድሃኔ ታደሰ ካጣመሩ በኋላ የተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉት ሰማያዊዎቹ በ85ኛው ደቂቃ ላይ ከባዶ ያዳነቻቸው ግብ አስቆጥረዋል። ፉሴይኒ ኑሁ ከአቡዋላ የተላከችለትን ኳስ በግል ጥረቱ ገብቶ ለመድሃኔ ታደሰ አቀብሎት አጥቂው ማስቆጠር ችሏል።
ውጤቱን ተከትሎ ፋሲል ከነማዎች ከሊጉ መሪ መቐለ 70 እንደርታ ያላቸው የነጥብ ልዩነት ወደ ሁለት ማውረድ ሲችሉ ደደቢቶች በሊጉ የመቆየታቸው ነገር እጅግ ተመናምኗል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡