ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደቡብ ፖሊስ ነጥብ ተጋርተዋል

የ24ኛው ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደቡብ ፖሊስ መካከል ተከናውኖ ያለግብ ተጠናቋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በሸገር ደርቢ ከተጠቀመበት የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ሄኖክ አዱኛ እና አቡበከር ሳኒን በማሳረፍ አብዱልከሪም መሀመድ እና አሜ መሀመድን በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ሲያካትት ደቡብ ፖሊስ አዳማን ከረታበት ጨዋታ ምንም የተጫዋች ለውጥ ሳያደርግ ጨዋታውን ጀምሯል።

የመጀመሪያው አጋማሽ እንቅስቃሴ በጣሙን የተቀዛቀዘ እና የሁለቱም ቡድኖች የማጥቃት ዕቅዶች ወርደው የታዩበት ነበር። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ተነቃቅተው የታዩት ጊዮርጊሶች 3ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ያለው ከዘሪሁን አንሼቦ ጋር ታግሎ በግራ መስመር ከሳጥን ውስጥ የመታው ጠንከር ያለ ኳስ መክብብ ደገፉ ከመመለሱ በቀር ሌላ አስፈሪ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። የደቡብ ፖሊስ የኋላ ክፍል ባልተረጋጋበት ሁኔታ ስህተት ለመስራት የተቃረበባቸው ጊዜያት ቢኖሩም ፈረሰኞቹ ፊት ላይ የነበራቸው ንቃት መውረድ ዕድሎችን ለመፍጠር አላስቻላቸው። ኳስ ይዘው በሚቆዩባቸው ደቂቃዎችም ሳጥን ውስጥ ሰብረው መግባት ከብዷቸው ይታይ ነበር።

ከፊት ተነጥለው የሚታዩት ሦስት አጥቂዎቻቸው አቋቋም ቡድኑ የመልሶ ማጥቃት ዕቅድ ያለው እንዲመስል ቢያደርግም ከራሳቸው ሜዳ ኳስ ይዘው ለመውጣት የሚሞክሩት እንግዶቹም አቀራረባቸው ግራ የሚያጋባ ነበር። ኪዳኔ አሰፋ እና ዮናስ በርታ ለተከላካይ ክፍሉ ቀርበው ሽፋን በመስጠት በመጠመዳቸውም ለአጥቂዎች ኳስ የመጣሉ ኃላፊነት ዘላለም ኢሳያስ ላይ ብቻ የወደቀ ይመስል ነበር። በአጋማሹም ቡድኑ 30ኛው ደቂቃ ላይ የተሻ ግዛው በቀኝ መስመር ይዞት በገባው ኳስ የተሻለ የሚባል የመልሶ ማጥቃት ቅፅበት ቢያገኝም ኳሱን የተቀበለው ሄኖክ አየለ ከቅርብ ርቀት ያደረገው ሙከራ ለጥቂት በግቡ ጎን ወጥቷል።

ከዚህ ውጪ ሙሉዓለም መስፍን በጨዋታ ከሪቻርድ አርተር ተሻግሮለት ደስታ ጊቻሞ ደግሞ ከማዕዘን ምት መነሻነት በግንባር ያደረጓቸው ሙከራዎች የተሻሉ ነበሩ ማለት ይቻላል። ሆኖም ጊዮርጊሶች የተጋጣሚያቸውን ተከላካዮች ከኳስ ውጪ ጫና ውስጥ አለመክተታቸው እና በመስመር አጥቂዎቻቸው እንቅስቃሴ ከሜዳው ስፋት ተጠቃሚ አለመሆናቸው ቅብብሎቻቸው ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ እንዲቆራረጡ ምክንያት ይሆን ነበር። በመልሶ ማጥቃት ዝግጅታቸው ወርደው የታዩት ፖሊሶችም በቁጥር አንሰው ራሳቸውን ለአንድ ለአንድ ግንኙነት ይጋብዙ የነበረ በመሆኑ ከጊዮርጊስ ተከላካዮች ጀርባ ለመግባት በሚወስድባቸው ጊዜ ኳሶችን በቀላሉ ይነጠቁ ነበር።

ከዕረፍት መልስ የጨዋታው ፍጥነት እምብዛም ሳይሻሻል በተቀዛቀዘ መልኩ የቀጠለ ነበር። በርግጥ ጊዮርጊሶች በቅብብል ከመጀመሪያው በተሻለ መልኩ ወደ ተጋጣሚያቸው ሳጥን ሲቀርቡ ሲታይ ደቡብ ፖሊሶችም በትክክል ለመልሶ ማጥቃት የተመቸ ባህሪን ማሳየት ጀምረዋል።

በፈለጉት መጠን ወደ ሳጥኑ ውስጥ ዘልቀው መግባት የቸገራቸው ጊዮርጊሶች በኃይሉ አሰፋ እና ጋዲሳ መብራቴን በማስገባት ከተሻጋሪ ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለማግኘት ሞክረዋል። 55ኛው ደቂቃ ላይ በኃይሉ አሰፋ በገባባት ቅፅበት ከመሀል ሜዳ ያሻገረለትን ኳስ አቤል ያለው በተከላካዮች መሀል ሆኖ ሳጥን ውስጥ ቢያገኘውም ሙከራው በሚያቆጭ መልኩ ወደ ውጪ ወጥቷል። የመስመር አጥቂዎቹን ጭምር ወደ ኋላ ስቦ የነበረው ተጋጣሚያቸውን ለማስከፈት በቀጣይ ደቂቃዎችም ከበኃይሉ በግራ መስመር በሚነሱ ረጃጅም ኳሶች እና ተደጋጋሚ የማዕዘን ምቶች ጥረት ቢያደርጉም 75ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም መሀመድ ከረጅም ከርቀት ያደረገው ሙከራ በመክብብ ጥረት ሲድን 82ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በኃይሉ ከግራ ያሻገረው ኳስ በሀምፍሬይ ሚዬኔ ተገጭቶ በመክብብ እና በግቡ ቋሚ ጥረት ድኗል።

በጥልቅ መከላከላቸው እንዳለ ሆኖ ከዘላለም ኢሳያስ መነሻቸውን ባደረጉ ረጅም ኳሶች በቁጥር የበረከቱ የመልሶ ማጥቃት ቅፅበቶችን ያገኙት ደቡብ ፖሊሶች በግብ ፊት የነበረው ደካማ ውሳኔ አሰጣጣቸው ግብ እንዳያገኙ አድርጓቸዋል። በተለይም ተቀይሮ የገባው የመስመር አጥቂ ብሩክ ኤልያስ ከኋላ ጥሩ ሽፋን ከመስጠቱ ባለፈ የመጨረሻ ዕድሌችንም አግኝቶ ነበር። 68ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ አየለ በቀኝ በኩል በድንገት ከተከላካዮች ጀርባ ተገኝቶ መሬት ለመሬት የመታው ኳስ እንዲሁም በጭማሪ ደቂቃ አናጋው ባደግ ከቀኝ መስመር መሬት ለመሬት ሳጥን ውስጥ በላከው ኳስ ብሩክ ኤልያስ ነፃ ሆኖ ከግብ ጠባቂው ፊት ዕድሎችን ቢያገኝም ሳይጠቀምባቸው ቀርቷል። ያም ቢሆን ደቡብ ፖሊሶች እስከ 97ኛው ደቂቃ በዘለቀው ጨዋታ የባለሜዳውን ተሻጋሪ ኳሶች ተቋቁመው ነጥብ መጋራት ችለዋል።

በውጤቱም ሁለቱም ቡድኖች የደረጃ ለውጥ ሳያሳዩ በነበሩበት ቦታ ረግተዋል ፤ የበላዮቹን መቅረብ ያልቻለው ቅዱስ ጊዬርጊስ 4ኛ ከመከላከያ ጋር ነጥቡን ያስተካከለው ደቡብ ፖሊስ 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡