ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | መቐለ 70 እንደርታ ከ ስሑል ሽረ

በዛሬው ዕለት ከሚደረጉት ጨዋታዎች የሊጉ መሪ ምዓም አናብስት ከስሑል ሽረ የሚያደርጉት ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ከሁለተኛው ዙር መጀመር አንስቶ በወጣ ገባ አቋም ጨዋታቸውን እያካሄዱ የሚገኙት ምዓም አናብስት ተከታያቸው ፋሲል ከነማን የማሸነፍ ውጤት አይተው ወደዚህ ጨዋታ ስለቀረቡ ይበልጥ ጫና ውስጥ ሆነው እና የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ ገብተው ነው ይህን ጨዋታ የሚያካሂዱት።

በቅርብ ጨዋታዎች ከቀደመው ቀጥተኛ እና የመስመር አጨዋወታቸው የተወሰነ ለውጥ በማድረግ በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ላይ ተመስርተው ለመጫወት እየሞከሩ የሚገኙት መቐለዎች በዛሬው ወሳኝ ጨዋታም ከባለፈው ጨዋታ መሰረታዊ የአጨዋወት ለውጦች አድርገው ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በነበነረው ጨዋታ አደራደራቸው ወደ 4-2-3-1 ቀይረው ጥሩ በመንቀሳቀስ በርካታ ንፁህ የግብ ዕድሎች ያልፈጠሩት መቐለዎች በዛሬው ጨዋታ በዚህ ዓመት በብዛት ወደ ተጠቀሙበት ጠባቡ 4-4-2 ይመለሳሉ ተብሎ ይገመታል። ባለፉት የሜዳቸው ጨዋታዎች የተለመደው የመስመር አጨዋወታቸው በብዛት ሲተገብሩ ባይታዩም ዛሬ ግን የተጋጣሚያቸውን የመከላከል አቀራረብ ተመልክተው ወደ ቀደመው እና ውጤታማው የመስመር አጨዋወታቸው ሊመለሱ የሚችሉበት ዕድል የሰፋ ነው። መቐለዎች ለረጅም ጊዜያት ጉዳት ላይ ካለው ተከላካያቸው አቼምፖንግ አሞስ ውጪ በጉዳትም ሆነ በቅጣትም የሚያጡት ተጫዋች አይኖርም።

በሁለተኛው ዙር በርካታ ለውጦች ያደረጉት እና ባለፈው ሳምንት ሃዋሳ ከተማን 4-0 ረምርመው ወደዚህ ጨዋታ የሚቀርቡት ስሑል ሽረዎች ለሉጉ መሪዎች ከባድ ፈተና ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል። አሰልጣኝ ሳምሶን አየለን ከቀጠሩ በኃላ በተለይም ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች  ጥሩ የማጥቃት ጥምረት በመስራት በሁለት ጨዋታዎች ላይ ስድስት ግቦች ያስቆጠሩት ሽረዎች ነገም እንደባለፉት ጨዋታዎች በሳሊፉ ፎፋና የሚመራውን የማጥቃት ክፍል ላይ መሰረት አድርገው ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከሌሎች የቡድኑ ክፍሎች በተለየ ጥንካሬ መላበስ ያልቻለው እና በሁለተኛው ዙር  አስር ግቦች ያስተናገደው የስሑል ሽረ የመከላከል አደረጃጀት ግን በተሻለ መልኩ ጠንክሮ መቅረብ ካልቻለ ጠንካራውን የመቐለ የማጥቃት ክፍልን ለመመከት መቸገሩ አይቀርም። ቡድኑ ከግብ ጠባቂው ሀፍቶም ቢሰጠኝ ውጪ የሚያጣው ተጫዋች አይኖርም።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– በፕሪምየር ሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙበት የስምንተኛው ሳምንት ጨዋታ ያለግብ የተጠናቀቀ ነበር። 

– ትግራይ ስታድየም ላይ 13 ጨዋታዎችን ያከናወነው መቐለ 70 እንደርታ 11 ጊዜ አሸንፎ ሁለቴ አቻ ተለያይቷል። ከጨዋታዎቹ በሰባቱ ግብ ሳያስተነግድ ከሜዳ መውጣት ችሏል።

– ስሑል ሽረ ከሜዳው ውጪ አስር ጨዋታዎችን ሲያደርግ በአንድ ድል እና በሁለት የአቻ ውጤቶች አምስት ነጥቦችን ሲያሳካ ሰባት ሽንፈቶች ገጥመውታል። 

ዳኛ

– ስድስተኛው ሳምንት ላይ ስሑል ሽረ ከ ሲዳማ ቡና ያደረገውን ጨዋታ የዳኘው እና መቐለን ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያገኘው ቢኒያም ወርቅአገኘው ይህን ጨዋታ ለመምራት ተመድቧል። ሳምንት ሶዶ ላይ ከዳኘው ጨዋታ መልስ ወደ መቐለ ለሚያመራው ቢኒያም ዘንድሮ በመሀል ዳኝነት የተሰየመበት ሰባተኛ ጨዋታውም ይሆናል። 

ግምታዊ አሰላለፍ

መቐለ 70 እንደርታ (4-4-2)

ፍሊፕ ኦቮኖ

ስዩም ተስፋዬ – አሌክስ ተሰማ – አሚን ነስሩ – አንተነህ ገ\ክርስቶስ    

ያሬድ ከበደ – ጋብርኤል አህመድ – ሚካኤል ደስታ – ሀይደር ሸረፋ

አማኑኤል ገ/ሚካኤል – ኦሴይ ማውሊ

ስሑል ሽረ (4-2-3-1)

ሰንደይ ሮቲሚ 

አብዱሰላም አማን – አሳሪ አልመሃዲ – ዲሜጥሮስ ወ\ስላሴ – ረመዳን የሱፍ

ሀብታሙ ሽዋለም – ደሳለኝ ደባሽ

ሳሊፉ ፎፋና – ያሳር ሙገርዋ – ቢስማርክ ኦፖንግ 

ቢስማርክ አፒያ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡