ከፍተኛ ሊግ ሀ | ሰበታ መሪነቱን ሲያጠናክር ተከታዮቹ ነጥብ ጥለዋል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ 16ኛ ሳምንት ጨዋታዎች እሁድ ሲከናወኑ ሰበታ መሪነቱን ያጠናከረበት ድል አስመዝግቧል። ተከታዮቹ ነጥብ ሲጥሉ አንድ ጨዋታ ደግሞ ተቋርጧል።

ወደ ባህር ዳር ያመራው ሰበታ ከተማ አውስኮድን 3-2 በማሸነፍ ወደ ፕሪምየር ሊግ የሚያደርገውን ጉዞ አሳምሯል። አውስኮዶች በ5ኛው ደቂቃ ላይ በሰዒድ ሰጠኝ ግብ መሪ መሆን የቻሉት ቢሆንም ዐቢይ ቡልቲ በ35ኛው ደቂቃ ሰበታን አቻ አድርጎ ለረጅም ደቂቃዎች ጎል ሳይቆጠር ዘልቋል። በግማሽ ዓመት ላይ ክለቡን በድጋሚ የተቀላቀለው ዐቢይ ቡልቲ በ75ኛው ደቂቃ ላይ ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ ወደ መሪነት ሲያሸጋግር በ82ኛው ደቂቃ ላይ ናትናኤል ጋንቹላ መሪነታቸውን አስተማማኝ ያደረገ ሦስተኛ ጎል አስቆጥሯል። ጨዋታው የተጠናቀቀው በ90ኛው ደቂቃ ኤርሚያስ ዳንኤል የአውስኮድን ሁለተኛ ግብ አስቆጥሮ በሰበታ 3-2 አሸናፊነት ነበር። ድሉ ተከታዮቹ ነጥብ በመጣላቸው ምክንያት ሰበታ ከተማ በ3 ነጥብ ልዩነት ምድቡን እንዲመራ አስችሎታል።

ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ለገጣፎ ሼህ መሐመድ አላሙዲ ስታዲየም ላይ በወልዲያ 3-0 ተሸንፏል። ተስፋዬ ነጋሽ በ6ኛው ደቂቃ ላይ በ76ኛው ደቂቃ ላይ ሁለት ጎሎችን ሲያስቆጥር ተስሎች ሳይመን በ85ኛው ደቂቃ ተጨማሪውን አክሏል።

ጎፋ ሜዳ ላይ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከአቃቂ ቃሊቲ ነጥብ ተጋርቶ ወደ ፕሪምየር ሊግ የሚያደርገው ጉዞ ረጅም አድርጓል። ለትግራይ ዋልታ ፖሊሱ አማኑኤል ብርሀነ የህሊና ፀሎት ተደርጎ በተጀመረው ጨዋታ የመጀመርያው አጋማሽ ባለሜዳው ኤሌክትሪክ ተሽሎ የታየበት ነበር። በ6ኛው ደቂቃ ላይ ታፈሰ ተስፋዬ ከርቀት አክርሮ የሞከራትም ተጠቃሽ የግብ ሙከራ ነበረች። በአቃቂ ቃሊቲዎች በኩል ደግሞ በ10ኛው ደቂቃ ሮቤል ጥላሁን ከርቀት የተሻገረለትን ኳስ በአግባቡ በመቆጣጠር በመታት ኳስ የመጀመሪያ የግብ ሙከራ አድርገዋል። ኤሌክትሪክ የጨዋታ የበላይነት ያሳዩ እንጂ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን በግብ ሙከራ ማጀብ አልቻሉም።

በሁለተኛው የጨዋታ ምዕራፍም ባለሜዳዎቹ ጫና ፈጥረው ወደ አቃቂዎች የግብ ክልል ቶሎ ቶሎ በመድረስ ሲችሉ በ62ኛው ደቂቃ ታፈሰ ተስፋዬ ወደ ግብ አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ያዳነበት፤ በ65ኛው እና 75ኛው ደቂቃ ወንድምአገኝ አብሬ የመታቸው ኳሶች በግቡ አናት ላይ የወጡበትን ሙከራዎች አድርጓል።

በጨዋታው እንቅስቃሴ ጥንቃቄ የመረጡት አቃቂዎች በመልሶ ማጥቃት የጎል እድል መፍጠር ተሳክቶላቸው ጎል ማስቆጠር ችለዋል። በ87ኛው ደቂቃ ላይ ጉልላት ተሾመ ከርቀት የተሻገረለትን ኳስ በአግባቡ በመቆጣጠር ወደ ግብነት ለውጦም መሪ አድርጓል። ሆኖም የአቃቂ መሪነት ብዙ ደቂቃ አልቆየም። በተጨማሪ ደቂቃ ላይ ኳስ በሳጥን ውስጥ ኳስ በእጅ በመነካቱ የተሰጠው ፍፁም ቅጣት ምትን ተፈሰ ተስፋዬ አስቆጥሮ ኤሌክትሪኮች አቻ በመሆን ጨዋታውም 1-1 ተጠናቋል።

አራተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ፌዴራል ፖሊስ ገላን ከተማን ኦሜድላ ሜዳ ላይ አስተናግዶ 3-0 አሸንፏል። ቻላቸው ቤዛ በ37ኛው እና 75 ኛው ደቂቃ ላይ ሁለት ጎሎችን ሲያስቆጥር እንዳለማው አበራ በ55ኛው ደቂቃ ቀሪዋን ጎል አስቆጥሯል።

አክሱም ላይ አክሱም ከቡራዩ ያደረጉት ጨዋታ በባለሜዳው 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ለአክሱም በ13ኛው ደቂቃ ላይ ብቸኛዋን የድል ጎል ያስቆጠረው ሙሉጌታ ረጋሳ ነው።

ወሎ ላይ ወሎ ኮምበልቻ ከ ደሴ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ በተነሳ ረብሻ ምክንያት ገና በ31ኛው ደቂቃ ላይ ተቋርጧል። ጨዋታው ዛሬ 4:00 ላይ በዝግ ስታድየም ካቆመበት ይቀጥላልም ተብሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡