ከ23ኛው ሳምንት መርሀ ግብር ውስጥ በብቸኝነት በነገው ዕለት በትግራይ ስታድየም የሚካሄደውን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።
ሁለት በሁለተኛው ዙር በተመሳሳይ መነቃቃት ላይ የሚገኙት ቡድኖችን የሚያገናኘው ይህ ጨዋታ አዝናኝ እና ተመጣጣኝ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል። ባለፈው ሳምንት ከደደቢት ጋር በነበረው ጨዋታ ከረጅም ጊዜ በኋላ ወደ 4-4-2 ተመልሰው ጥሩ በመጫወት በርካታ የግብ ዕድሎች የፈጠሩት ቢጫ ለባሾቹ በነገው ጨዋታው ያንን ውጤታማ ቡድን እና ጠንካራ የማጥቃት ጥምረት ይቀይራሉ ተብሎ አይጠበቅም።
በጨዋታው በሁለተኛው ዙር በጥሩ ብቃት ይገኝ የነበረው አማኑኤል ጎበናን በጉዳት በማጣቸው ምክንያት አደራደራቸው ላይ ለውጥ በማድረግ ከሚታወቁበት የመስመር አጨዋወት ይልቅ ሁለቱ አጥቂዎች ላይ መሰረት ባደረጉ ቀጥተኛ ኳሶች ሊጠቀሙ ይችላሉ። በዚህ መልኩ ከሌሎች ጨዋታዎች የተሻለ አስፈሪ የማጥቃት ክፍል የገነቡት ወልዋሎዎች በተለይም የቡድኑን የማጥቃት እና የአማካይ ክፍል ጥምረት ካላቸው የተጫዋቾች አማራጭ አንፃር ብዙ ለውጥ ሳያደርጉ ጅማን እንደሚያስተናግዱ ይገመታል። ወልዋሎዎች በጉዳት ምክንያት ከማይኖረው አማኑኤል ጎበና በቀር ቀሪው ስብስባቸው ለጨዋታው ብቁ ነው።
በሁለተኛው ዙር ጥሩ መሻሻል ካሳዩት የፕሪምየር ክለቦች በግንባር በቀደምትነት የሚነሱት ጅማ አባጅፋሮች በነገው የሜዳ ውጪ ጨዋታቸው ቀላል ግምት አይሰጣቸውም። ከሁለተኛውን ዙር መጀመር በኃላ ካደረጓቸው ሰባት ጨዋታዎች አምስቱን በማሸነፍ በአንድ ጨዋታ አቻ ወጥተው በድሬዳዋ ከተማ የተሸነፉት ጅማዎች በማጥቃቱ ላይ ወሳኝ ሚና ያለው ተጫዋቻቸው ማማዱ ሲዲቤ መጠነኛ ጉዳት ምክንያት አጨዋወታቸው ካልቀየሩ በስተቀር ላለፉት ጨዋታዎች ቡድኑን ውጤታማ ካደረገው አደራደር ላይ ለውጥ ያደርጋሉ ተብሎ አይገመትም። ባለፉት ጨዋታዎች በተከተሉት ቀጥተኛ አጨዋወት ምክንያት የመስመር ተጫዋቾቻቸው የማጥቃት ተሳትፎ የቀነሱት ጅማዎች የነገው ተጋጣምያቸው ወልዋሎ በርካታ ተጫዋቾች የሚያሳትፍ የጠንካራ መከላከል አደረጃጀት ባለቤት እንደመሆኑ የማጥቃት ክፍላቸው የተሻለ ውጤታማ ለማድረግ ከቀጥተኛ አጨዋወት ይልቅ ከሁለቱ መስመሮች የሚነሱ ጥቃቶችን ምርጫቸው ሊያደርጉ የሚችሉበት ዕድል የሰፋ ነው።
ጅማዎች ግብ ጠባቂያቸው ዳንኤል አጄይ በቤተሰብ ምክንያት ወደ ሆላንድ በማቅናቱ ከጨዋታው ውጪ ቢሆንባቸውም በአንፃሩ በቅርብ ጊዜ ከጉዳት የተመለሰው አምበላቸው ኤልያስ አታሮ ወደ ቋሚ አሰላለፍ ይመልሳል ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህ ውጪ ማማዱ ሲዲቤ በገጠመው መጠነኛ ጉዳት በቋሚነት የሚጀምርበት ዕድል ጠባብ ነው።
የእርሰ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች
– ወልዋሎ ሊጉን በተቀላቀለበት የ2010 የውድድር ዓመት ጅማ ላይ ጅማ አባ ጅፋር 3-0 ሲያሸንፍ የዓዲግራቱ ጨዋታ ደግሞ 1-1 የተጠናቀቀ ነበር። ዘንድሮ በመጀመሪያው ዙር የተገናኙበት ጨዋታ ደግሞ ያለግብ ተጠናቋል።
– ትግራይ ስታድየም ላይ 11 ጨዋታዎችን ያደረገው ወልዋሎ አምስቴ ድል ሲቀናው ሁለት ሽንፈት እና አራት የአቻ ውጤቶች ገጥመውታል።
– ጅማ አባ ጅፋር ከሜዳ ውጪ ካደረጋቸው 11 ጨዋታዎች አራቴ በድል ሁለት ጊዜ ደግሞ በአቻ ውጤት ሲመለስ በአምስት ጨዋታዎች ተሸንፏል።
ዳኛ
– ጨዋታውን ማኑሄ ወልደፃዲቅ በመሀል ዳኝነት ይመራዋል። አርቢትሩ እስካሁን በመራቸው ስድስት ጨዋታዎች 17 የማስጠንቀቂያ ካርዶችን ሲመዝ አምስት የፍፁም ቅጣት ምቶችን ሰጥቷል።
ወልዋሎ ዓ/ዩ (4-4-2)
አብዱልአዚዝ ኬይታ
እንየው ካሳሁን – በረከት ተሰማ – ደስታ ደሙ – ብርሃኑ ቦጋለ
ፕሪንስ ሰቨሪንሆ – ብርሃኑ አሻሞ- አፈወርቅ ኃይሉ – ኤፍሬም አሻሞ
ሪችሞንድ አዶንጎ – ክሪስቶፈር ችዞባ
ጅማ አባጅፋር (4-4-2)
ዘሪሁን ታደለ
ዐወት ገ/ሚካኤል – መላኩ ወልዴ – አዳማ ሲሶኮ – ኤልያስ ዓታሮ
ዲዲዬ ለብሪ – መስዑድ መሀመድ –ይሁን እንዳሻው – አስቻለው ግርማ
ኦኪኪ አፎላቢ – ቴዎድሮስ ታደሰ
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡