በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 23ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሐ ግብር የሆነው የወልዋሎ እና የጅማ አባጅፋር ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።
ወልዋሎዎች ባለፈው ሳምንት ደደቢትን ካሸነፈው ስብስባቸው ክሪስቶፈር ችዞባን አስወጥተው በአብዱራሕማን ፉሴይኒ ተክተው ሲገቡ ጅማዎች በበኩላቸው ሲዳማን ካሸነፈው ስብስብ ማማዱ ሲዲቤ እና መስዑድ መሐመድ ምትክ በአክሊሉ ዋለልኝ እና ብሩክ ገብርአብ በመጠቀም ወደ ሜዳ ገብተዋል።
ባለፈው ሳምንት ህይወቱን ላጣው የዋልታ ፖሊሱ ተጫዋች አማኑኤል ብርሃነ በተደረገው የህሊና ፅሎት የጀመረው ጨዋታው የወልዋሎዎች የጨዋታ ብልጫ እና ጥቂት የግብ ሙከራዎች የታየበት ነበር። በጨዋታው በሁለቱም መስመር ለማጥቃት ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት እና ከተጋጣሚያቸው አንፃር ሲታይ በኳስ ቁጥጥር የተሻለ ብልጫ የነበራቸው ወልዋሎዎች እንደወሰዱት ብልጫ በርካታ ዕድሎች ባይፈጥሩም የሚጠቀሱ የጎል ሙከራዎች ግን አድርገዋል።
በቅርብ ጨዋታዎች ላይ በጥሩ ብቃት የሚገኘው ሪችሞንድ አዶንጎ ከኤፍሬም አሻሞ የተላከለትን ኳስ መትቶ መላኩ ወልዴ ተደርቦ ያወጣው እና ደስታ ደሙ ከቅጣት ምት ብርሃኑ ቦጋለ ያሻማውን ኳስ በግንባር ገጭቶ ያደረገው ሙከራ እንዲሁም ፕሪንስ ሰቨሪንሆ ከቅጣት ምት ያደረገው ጥሩ ሙከራ ወልዋሎን መሪ ለማድረግ የተቃረበ ነበር። በሃያ ሰባተኛው ደቂቃም ጋናዊው አብዱራህማን ፉሴይኒ ከአፈወርቅ ኃይሉ የተላከለትን ግሩም ኳስ በጥሩ አጨራረስ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።
በመጀመርያው አጋማሽ በመከላከል ክፍል ላይ ካሳዩት ጥሩ ጥንካሬ ውጭ ይህ የሚባል የተጠና የማጥቃት አጨዋወት ያላሳዩት እንግዶቹ ጅማዎች በዛ አጋማሽ ብሩክ ገብርአብ እና አስቻለው ግርማ በግል ካደረጉት ጥረት ውጭ ይህ ነው የሚባል ንፁህ የግብ ዕድል አልፈጠሩም። በዚህም አስቻለው ግርማ በጥሩ ሁኔታ ወደ ሳጥን ይዞት የገባው ኳስ ከግብ ጠባቂው በላይ መትቶ አብዱላዚዝ ኬታ በጥሩ ሁኔታ ያወጣው ኳስ እና ዲድየ ለብሪ ከሳጥኑ ጠርዝ ያገኘውን ኳስ አክርሮ መቶ ኬይታ ተፍቶ ወደ ውጭ ያወጣውን ሙከራ በጅማዎች በኩል ከታዩት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ይጠቀሳሉ።
ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ ተመጣጣኝ ፉክክር የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ በጅማዎች በኩል የተሻለ መነቃቃት የታየበት ወልዋሎዎች ደሞ ወደ መከላከል ያመዘኑበት ክፍለ ግዜ ነበር። የተጫዋች አደራደር ለውጥ አድርገው የተመለሱት ጅማዎች ብልጫ ባሳዩባቸው የመጀመርያዎቹ አስር ደቂቃዎች በሶስት አጋጣሚዎች አቻ ለመሆን ተቃርበው ነበር። በተለይም ኦኪኪ ኦፎላቢ ዓወት ገብረሚካኤል ያሻማውን ኳስ ተጠቅሞ በግንባር ገጭቶ ሞክሯት ኬታ እንደምንም ያዳናት ኳስ እና ዲድየ ሌብሬ ከመአዝን አሻምቷት መስዑድ መሐመድ በጥሩ ምት ያደረጋት ሙከራ ለግብ የቀረቡ ነበሩ።
እንደ መጀመርያው አጋማሽ በርካታ ዕድሎች ያልፈጠሩት ወልዋሎዎች በበኩላቸው ምንም እንኳ ሁለተኛው ግብ ለማስቆጠር ባይታደሉም ጥቂት የማይባሉ ዕድሎች ፈጥረዋል። ብርሃኑ እሻሞ ከርቀት ያደረጋት ሙከራ እና ሬችሞንድ አዶንጎ ተጫዋቾች አልፎ በመምታት ያመከናት ወርቃማ ዕድል የቢጫ ለባሾቹን መሪነት ከፍ ለማድረግ ከተቃረቡት ሙከራዎች ይጠቀሳሉ።
በሁለተኛው አጋማሽ በተለይም መስዑድ መሐመድ እና ዋለልኝ ገብሬ ተቀይረው ከገቡበት ደቂቃ የተሻለ በመንቀሳቀስ በቀጥተኛ ኳሶች በሶስተኛው የሜዳ ክፍል የተሻለ ውጤታማ የነበሩት ጅማዎች ሁለት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ካደረጉ በኃላ የአቻነቷን ግብ አስቆጥረዋል ፤ ከታዩት ሙከራዎችም ማማዱ ሲዲቤ ዋለልኝ ገብሬ ያሻማለትን ኳስ ተጠቅሞ በግንባር ያደረጋት ሙከራ ጎል ለመሆን ተቃርባ ነበር። በ72ኛው ደቂቃም ኳስ በወልዋሎ ሳጥን ውስጥ በእጅ ተነክታለች በሚል የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ኦኪኪ አፎላቢ አስቆጥሮ ቡድኑ ነጥብ ተጋርቶ እንዲወጣ አስችሏል።
ጨዋታው ግብ ከተቆጠረበት ደቂቃ በኃላ ይህ ነው የሚባል የረባ ሙከራ ሳይታይበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ ሁለቱም ቡድኖች ደረጃቸው ለማሻሻል የነበራቸውን ዕድል ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡