የአሰልጣኞች አስተያየት| ሀዋሳ ከተማ 0-1 ሲዳማ ቡና

የ23ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በሀዋሳ ደርቢ ሀዋሳ ከተማ እና ሲዳማ ቡናን አገናኝቶ በሲዳማ ቡና 1-0 አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

“ወደ ዋንጫው ፉክክር የሚወስደን ስለሆነ አስፈላጊ ጨዋታ ነበር” ዘርዓይ ሙሉ (ሲዳማ ቡና)

ስለጨዋታው

ሁለታችንም ከሽንፈት ስለተመለስን ጨዋታው እጅግ ከባድ ነበር። በተለይ ለኛ ወደ ዋንጫው ፉክክር የሚወስደን ስለሆነ አስፈላጊ ጨዋታ ነበር። ከእረፍት በፊት በዙ አጋጣሚዎችን አግንተን አልተጠቀምንባቸውም። ከእረፍት በኋላ የያዝነውን ውጤት አስጠብቀን ለመውጣት ነው ያሰብነው። ከእረፍት በኋላ እነሱ የተሻሉ ነበሩ።

በሁለተኛ አጋማሽ በመሐል ሜዳ መበለጣቸው

በብዛት ባለፈው ሳምንት የተጠቀምኩባቸው ተጫዋቾችን ናቸው ዛሬ የተጠቀምኩት። ከጅማ ጋር ስንጫወት ብዙ ጉልበት የሚፈልግ ጨዋታ ስለነበር ተጫዋቾቼ ላይ ድካም ፈጥሮባቸዋል።

“ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች መጠቀም አልቻልንም”
አዲሴ ካሳ (ሀዋሳ ከተማ)

ስለጨዋታው

መጀመሪያ አጋማሽ ላይ የተሻለ ተንቀሳቅሰው ያገኙትን አጋጣሚ ተጠቅመዋል። በሁለተኛው ግማሽ ግን በነሱ ሜዳ ላይ እየተጫወትን ነው የጨረስነው። ያገኘናቸውን አጋጣሚዎችን መጠቀም አልቻልንም። ስለዚህ ያው ኳስ ጨዋታ ነው፤ የሆነው ሆኗል።

የተከላካዮች ስህተት

ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ይህን ስህተት አርመናል። የነሱ አጨዋወት በአዲስ ግደይ እና ሐብታሙ ገዛኸኝ ያነጣጠረ ስለነበር ኳሶች በጣም ይወረወሩ ነበር። እኛ ደግሞ አላስፈላጊ ጉልበት እያባከን ነበር። ወደ አንድ አቅጣጫ ብቻ እየተጫወትን ሌላው ክፍላችን እየተውነው ነበር። ለዛም በጣም አደገኛ ኳሶች ሲወረወሩብን ነበር በተለይ በቀኝ የተከላካይ መስመር ክፍላችን።

ጎል የማግባት ችግር

ይህ ግልፅ ነው። በመጀመሪያ ዙርም ታፈሰ ሰለሞን ነበር ከመሀል እየተነሳ ጎል ሲያገባ የነበረው። አሁን ታፈሰ በግል ጉዳይ ምክንያት የለም፤ በተከታታይ ሁለት ጨዋታ አልተጠቀምንበትም። ጎል የማታገባ ከሆነ ደግሞ ወደ ሽንፈት ነው የምትመጣው፤ ይህን እናስተካክለዋለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡