የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ 11ኛ ሳምንት ውሎ

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ 11ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዳሜ እና እሁድ ተከናውነዋል።

ከሸገር ደርቢ ጨዋታ አስቀድሞ በ08:00 በበርካታ ተመልካቾች ፊት የተካሄደው የቅዱስ ጊዮርጊስ አና የወላይታ ድቻ ጨዋታ 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። በስቴዲየሙ እንደነበረው ቁጥሩ በርካታ ተመልካች ጥሩ ፉክክር ይስተናገዳል ተብሎ ቢጠበቅም ይህ ነው የሚባል ጥሩ የእግር ኳስ ፍሰት ሳይታይበት ተጠናቋል። ባለሜዳዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊሶች አልፎ አልፎ ካልሆነ በቀረ በሚቆራረጥ ኳሶቻቸው ምክንያት የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ተቸግረው ታይተዋል። በአንፃሩ እንግዶቹ ወላይታ ድቻዎች በጠንካራ መከላከላቸው ባሻገር በሚጠቀሙት የረጃጅም ኳስ እና መልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ከቅዱስ ጊዮርጊስ በተሻለ ወደ ግብ ክልል በመድረስ የጎል አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ሞክረዋል።

በቀኝ መስመር በተደጋጋሚ ሰብረው በመግባት ጥቃት ሲሰነዝሩ የታዩት ወላይታ ድቻዎች ከተሻጋሪ ኳስ የተላከውን አበባየሁ ሀጂሶ በግንባሩ በመግጨት ጎል አስቆጥሮ ቀዳሚ መሆን ችለዋል። ጎሉ ከተቆጠረባቸው በኋላ ተረጋግተው ወደ አቻነት ለመመለስ ጥረት ያደረጉት ፈረሰኞቹ አቻ መሆን የሚችሉበትን ዕድል በረከት ማህተሜ ለጎሉ ሁለት ሜትር ቅርበት ላይ ነፃ ኳስ አግኝቶ አገባው ሲባል ወደ ሰማይ የሰደዳት ኳስ የምታስቆጭ አጋጣሚ ነበረች። ከተወሰነ ደቂቃ በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊሶች አቻ የመሆናቸው ጥረት ተሳክቷል። አስቀድሞ የግብ ዕል አግኝቶ ሳይጠቀምበት የቀረው በረከት ማህተቤ ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ግብጠባቂው ሲመልሰው አግኝቶ ጎል በማስቆጠር ቅዱስ ጊዮርጊስን አቻ አድርጓል።

ብዙ ማራኪ ያነበረው ይህ ጨዋታ ከሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ይልቅ በቅዱስ ጊዮርጊስ እና በኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች መካከል የነበረው ብሽሽቅ ትኩረት ይስብ ነበር። ከእረፍት መልስ በተሻለ ኳሱን ይዘው በመጫወት ጥሩ መንቀሳቀስ የቻሉት ወላይታ ድቻዎች በዕለቱ ተስፋ ሰጪ የሆነ መልካም እንቅስቃሴ ያደረገው አንበሉ ታምራት ሰማኝ በግሩም ሁኔታ ከመስመር ያሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ አበባየሁ ሀይሶ በግንባሩ ገጭቶ ለራሱም ለቡድኑም ሁለተኛ ጎል ማስቆጠር ችሏል። በበርካታ ደጋፊዎቻቸው መሐል መጫወታቸው ጫና ውስጥ እንደገቡ የታዩት የቅዱስ ጊዮርጊስ ተስፈኞች የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ተቸግረዋል። ውጤቱን አስጠብቀው ለመውጣት ወደ ኃላ በማፈግፈግ በመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ወላይታ ድቻዎች በመጨረሻው ደቂቃ ላይ በግብ ክልላቸው ውስጥ ኳስ በእጅ በመንካታቸው ለቅዱስ ጊዮርጊስ ተሰጠውን ፍፁም ቅጣት በረከት ማህተቤ ወደ ጎልነት ቀይሮ ፈረሰኞቹን አቻ ከማድረጉ ባሻገር ለራሱም ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በሁለት አቻ ውጤት ተጠናቋል። (በዳንኤል መስፍን)

በምድብ ሀ እሁድ ሊደረግ የነበረው የድሬዳዋ ከተማ እና የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ  ጨዋታ አካዳሚ ወደ ስፍራው ባለመጓዙ ሳይካሄድ ቀርቷል። ረፋድ 04፡00 ላይ መጫወት የነበረባቸውን ጨዋታ በፎርፌ እንዲሸነፉ ሆኗል።

የአካዳሚው ታዳጊዎች ከዚህ ቀደም ይደረግላቸው የነበረው ድጋፍ እና ክትትል እየወረደ በመምጣቱ ያላቸውን ቅሬታም እያሰሙ ይገኛሉ። ከዚህ በኋላ አካዳሚው ላይ ያለ ችግር እስካልተቀረፈ ድረስ ልምምድም ሆነ ውድድር እንደማያደረጉም ውሳኔ ላይ ደርሰዋል።

እንደታዳጊዎቹ ገለፃ ከሆነ ከዚህ በፊት የነበረው በጀት እና የተጨዋቾች ቁጥር መቀነስ ፣ የትጥቅ ጥራት መጓደል ፣ እንዲሁም በቂ የላብ መተኪያ አለመሟላት አጠቃላይ የሚሰጣቸው ትኩረት አናሳ መሆን ተፅዕኖ አሳድሮባቸዋል። ከቤታቸው ወደ ማሰልጠኛው ሲገቡ የተሻለ ነገር ጠበቀው እንደነበር እና አመራር ያለው ችግር ሞራላቸው እንዲነካ ማድረጉንም ለሶከር ኢትዮጵያ ጨምረው ገልፀዋል።

አካዳሚው እንደ ሀገር በጀት ተይዞለት የሚንቀሳቀስ ትልቅ ተቋም ከመሆኑ አንፃር ለታዳጊዎቹ ተገቢውን ትኩረት መስጠት እና ችግሮች ሲኖሩ በቶሎ ለመፍታት መጣር ይኖርበታል። ከቤተሰቦቻቸው ተነጥለው የመጡት ስፖርተኞችም የተሻለ ነገር ተምረው ሀገርንም ሆነ የራሳቸውን ለመለወጥ የሚያስችል ትምህርት በአግባቡ ሊሰጣቸውም ይገባል።

ከኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ የሚሰጠውን ምላሽ በቀጣይ ይዘን እንቀርባለን ። (በኤልያስ ኢብራሂም)

አጠቃላይ የ20 ዓመት በታች ውድድር 11ኛ ሳምንት ውጤቶች እኛ ሰንጠረዥ



© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡