የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዳሜ፣ ሰኞ እና ዛሬ ሲካሄዱ አቃቂ ቃሊቲ መሪነቱን ያስጠበቀበት ድል አስመዝግቧል። መቐለ እና ቦሌ ከሜዳቸው ውጪ ሲያሸንፉ ንፋስ ስልክም ድል ቀንቶታል።
ቅዳሜ ረፋድ ላይ ፋሲል ከነማን ያስተናገደው ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ 1-0 ማሸነፍ ችሏል። የንፋስ ስልክ ብቸኛ የድል ጎል ባለቤት ሜሮን ገነሞ ናት። በዚሁ ዕለት ወደ ሻሸመኔ አቅንቶ ሻሸመኔ ከተማን የገጠመው ቦሌ ክፍለ ከተማ 4-0 አሸንፎ ተመልሷል። እዳአት ካሱ ሁለት ጎሎች ስታስቆጥር ቤተልሄም መንተሎ እና መዓዛ ዓብደላ ቀሪዎቹን ጎሎች ማስቆጠር ችለዋል።
የሳምንቱ ጨዋታ ትላንት ቀጥሎ ሲውል 11:00 ላይ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ መቐለ 70 እንደርታ ልደታ ክፍለ ከተማን ገጥሞ 1-0 አሸንፏል። ጥሩ የውድድር ዓመት በማሳለፍ ላይ የምትገኘው ዮርዳኖስ ምዑዝ የመቐለን ብቸኛ ጎል አስቆጥራ ቡድኑን ለ20 ሰዓታትም ቢሆን የሊጉ መሪ እንዲሆን አስችላለች።
በዛሬው ዕለት በተደረገ የ12ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ንግድ ባንክ ሜዳ ላይ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ከ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ተገናኝተው አቃቂ 3-1 በማሸነፍ መሪነቱን በድጋሚ ከመቐለ ተረክቧል። ቤዛዊት ንጉሴ፣ ሠላማዊት ጎሳዬ እና ዓይናለም መኮንን የድል ጎሎቹ ባለቤት ሲሆኑ የቂርቆስ ብቸኛ ጎል በጋብርኤላ አበበ አማካኝነት ተቆጥሯል።
የሁለተኛ ዲቪዚዮን ውድድር ሊጠናቀቅ የሁለት ሳምንታት ዕድሜ ብቻ በመቀሩበት በዚህ ወቅት አቃቂ ቃሊቲ ወደ አንደኛ ዲቪዚዮን ማደጉን ከወዲሁ ሲያረጋግጥ 3ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ፋሲል ከነማ በ6 ነጥብ የራቀው መቐለ 70 እንደርታ ማደጉን ለማረጋገጥ በእጅጉ ቀርቧል። (ከዚህ ሊግ ሁለት ክለቦች ወደ አንደኛ ዲቪዚዮን ያድጋሉ)
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡