በዓምላክ ተሰማ የተለየ ሚና ተሰጥቶት ወደ ዓለም ከ20 ዓመት በታች ውድድር ያመራል

በፖላንድ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የ2019 የፊፋ ከ20 ዓመት በታች ውድድር ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ዳኛ በዓምላክ ተሰማ ተመርጧል።

በፖላንድ አስተናግጅነት ከግንቦት 15 እስከ ሰኔ 8 በሚካሄደው በዚህ ውድድር ላይ የዓለም አቀፉ እግር ኳስ የበላይ አስተዳዳሪ ፊፋ ከመላው ዓለም 27 ዋና ዳኞች፣ 42 ረዳት ዳኞች እንዲሁም 21 የቪድዮ ረዳት (VAR) ዳኞች መርጧል። ከነዚህም ውስጥ ኢትዮጵያዊ ኢንተርናሽናል ዳኛ በዓምላክ ተሰማ ወይሶ በVAR ዳኝነት ተመድቧል።

ኢንተርናሽናል ዳኛ በአምላክ ከቀናት በፊት በሞሮኮ ተካሂዶ በተጠናቀቀውና የአፍሪካ ዋንጫ ለመምራት ከታጩ ዳኞች ጋር ስሎጠና ሲወስድ መቆየቱ የሚታዘስ ሲሆን በፖላንዱ ውድድር ላይ በዓምላክን ጨምሮ ሌሎች የተመረጡ ልምድ ያላቸው ዳኞች በቫር ዳኝነት እንደሚሳተፉ ታውቋል። ከአፍሪካም ተመሳሳይ ታላላቅ ጨዋታዎችን በመሐል ዳኝነት የማጫወት ልምድ ያላቸው ግብፃዊው ገሂድ ጊርሻ እና ጋምቢያዊው ባካሪ ጋሳማ (ፎቶ) ከበዓምላክ ጋር ተመሳመይ ሚና ተሰጥቷቸዋል። አፍሪካ በዋና ዳኝነት 3፣ በረዳት ዳኝነት ደግሞ 7 ዳኞችን ለውድድሩ አስመርጣለች።

ይህ ውድድር ከተጠናቀቀ ከ6 ቀናት በኋላ የአፍሪካ ዋንጫ በግብፅ አስተናጋጅነት መካሄድ የሚጀምር ሲሆን በዓምላክ ተሰማም ጨዋታዎችን ከሚመሩ ዳኞች አንዱ እንደሚሆን ይጠበቃል። 


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡