በዮናታን ሙሉጌታ
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ትላንት እና ከትላንት በስተያ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ቀጥለው ተካሂደዋል፡፡ ከነዚህ ጨዋታዎች መካከል በትላንትናው ዕለት ኢትዮጵያ ቡና ኤሌክትሪክን 2 ለ 1 በሆነ ውጤት የረታበት ጨዋታ የሚጠቀስ ነው፡፡ ከምሽቱ 11፡30 ላይ የተደረገውና ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ ተመልካቹን እስከመጨረሻው ሰዓት ድረስ ዘና ያደረገውን ይህን ጨዋታ ከታክቲካዊ ዝርዝሮች ጋር ሶከር ኢትዮጵያ እንደሚከተለው ታስቃኛችኋለች፡፡
በምስል 1 ላይ እንደተመለከተው ሁለቱም ቡድኖች በሦስተኛው ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች ማለትም ኤሌክትሪክ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ባደረገው እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና አዳማ ከነማን ካስተናገደበት ጨዋታዎች በተለየ የአሰላለፍ እና የተጨዋቾች ምርጫ ለውጦችን አርገው ቀርበዋል፡፡
ኤሌክትሪኮች ቅዱስ ጊዮርጊስን ከገጠሙበት የ5-3-2 formation ወደ 4-2-3-1 ሲመጡ ሦስት የተጨዋቾች ለውጥም በማድረግ ነበር፡፡ ከሦስቱ የመሀል ተከላካዮች አንዱ የነበረውን ተስፋዬ መላኩን በተከላካይ አማካዩ ደረጀ ኃይሉ እንዲሁም የአጥቂ አማካይ ሚና የተጠቀሙበትን ማናዬ ፋንቱን በኃይሉ ተሻገር ለውጠዋል፡፡ እንዲሁም በቀኝ መስመር ተከላካይ ሚና ላይ ዐወት ገ/ሚካኤልን በመሐመድ ሰይድ ተክተው ተጠቅመውበታል፡፡ በአጠቃላይ ቡድኑ ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር ካደረገው ጨዋታ ይልቅ ለማጥቃትና ወደፊት ገፍቶ ለመጫወት የተሻለ ተነሳሽነት የነበረው ሆኖ ታይቷል፡፡
በኢትዮጵያ ቡና በኩል እሁድ አዳማን በገጠመበት ወቅት በሁለቱ መስመሮች ላይ ያሰለፋቸውን ጥላሁን ወልዴንና ሳዲቅ ሼቶን ከመጀመሪያ አሰላለፍ ውጪ በማድረግ በምትካቸው ያቡን ዊልያምን እና ዮሴፍ ደሙዬን ተጠቅሟል፡፡ በዚህም መሠረት ቡና ያለ አጥቂ ከተጫወተበት የእሁዱ ጨዋታ በተለየ ያቡን ዊሊያምን በመጨረሻ አጥቂነት ተጠቅሟል፡፡ መሀል ሜዳውን በጋቶች ኤሌያስና መስዑድ አማካይነት ያዋቀረውን ኢትዮጵያ ቡና ሁለቱን መስመሮች በቀኝ ዮሴፍ ደሙዬንና ግራውን በእያሱ ታምሩ በማሰለፍ ቀርቧል፡፡
ጨዋታው እንደተጀመረ ነበር የኤሌክትሪኩ አጥቂ ፒተር ከቀኝ መስመር ወደ መሀል ያሻማት ኳስ ሳይታሰብ ጐል ሆና የተመዘገበችው፡፡ ለጐሏ መገኘት የኢትዮጵያ ቡናው ግብ ጠባቂ ወንድወሰን የጊዜ አጠባበቅ ስህተት ዋና ምክንያት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ከጐሏ መገኘት በኋላ በአብዛኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ እንደታየው ኢትዮጵያ ቡና የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን ወስዶ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ቡና አራቱ አማካዮች (ከጋቶች በቀር) ቡድናቸው ኳስ በሚነጠቅበት ጊዜና እንዲሁም ኳስን ከኋላ መስርቶ በሚጀምርበት ጊዜ ከተከላካይ አማካዩ ጋቶች ፓኖም ፊት እንዲሁም ከፊት አጥቂያቸው ያቡን ጀርባ ባለው ቦታ ላይ አራቱም በአግድሞሽ መስመር ሰርተው ይንቀሳቀሱ ነበር፡፡ በተጨማሪም ቡድኑ በመከላከል ወደ ማጥቃት ሲሸጋገር እንዲሁም ከኋላ ተመስርቶ የመጣው ኳስ መሀል ሜዳውን እንዳለፈ ሁለቱ የመስመር አማካዮች ፈጥነው ወደፊት በመሄድ ከያቡን ግራና ቀኝ በመግባት ራሳቸውን መሀል ለመሀል በተለይም በመስዑድና ኤልያስ አማካይነት ለማስነጠቁ ኳሶች ዝግጁ ያረጉ ነበር፡፡ ይኸም እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ ቡና የሜዳው የጐን ስፋት እንዲጠቀምና በኤሌክትሪክ ተከላካዮች መካከል የሚኖረው ክፍተት እንዲሰፋ ለማድረግ እጅጉን ጠቅሞት ነበር፡፡
(ምስል 2ን ይመልከቱ)
በጨዋታው አብዛኛው ክፍለ ጊዜም በዚህ እንቅስቃሴ አማካይነት በሚገኘው ክፍተት ነበር አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ቡና የጐል እድሎች የተፈጠሩት እንዲሁም ሁለቱ ጐሎች የተቆጠሩት፡፡ በተጨማሪም ጋቶች ያመከናት የፍጹም ቅጣት ምት አጋጣሚም የተፈጠረችው በተመሳሳይ እንቅስቃሴ በተገኘ ክፍተት ነበር፡፡ በዘመናዊ እግር ኳስ ከላይ በተጠቀሰው መላኩ በየተከላካዮቹ መሀል የሚኖረው ክፍተት መስፋት ለጐሎች መቆጠር ምክንያት ሲሆን ይታያል፡፡ እዚህ ላይ ግን የተከላካይ አማካዮች ሚና ወሳኝ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ከ አራቱ ተከላካዮች ፊት የነበሩት የኤሌክትሪክ የመሀል ሜዳ ተጫዋቾች ድክመት ታይቶባቸዋል፡፡ ይልቁኑም በመስመር ተከላካዮቹ እና በመሀል ተከላካዮቹ መካከል እየተፈጠረ የነበረውን ክፍተት ለማጥበብ ተከላካዮቹ በተጠጋጉ ቁጥር በሁለቱ መስመሮች ላይ ይተዋቸው የነበሩ ሰፋፊ ቀዳዳዎች ቡድኑን ለጥቃት ሲዳርጉት ተስተውሏል፡፡ ሁለቱ የኤሌክትሪክ የተከላካይ አማካዮች ትኩረትም የነበረው ተጋጣሚያቸው በሜዳው መሀል ለመሀል የሚፈጥራቸውን አጋጣሚዎች ለማስቆም መሞከር ነበር እንጂ በሁለቱ መስመሮች ይጋረጥባቸው የነበረውን አደጋ ወደኋላ ተመልሰው የመሸፈን ሚና ሲወጡ የነበሩት የመስመር አማካዮቻቸው ነበሩ፡፡ እነዚህ አማካዮች ደግሞ በተፈጥሮ ወደ ማጥቃቱ ያዘነበሉ በመሆናቸው አንዳንዴም ቡድኑ በመከላከል ስራ ላይ በሚጠመድበት ጊዜ ወደ ኋላ ተመልሰው በቦታቸው ላይ ሳይገኙ በመቅረት በሌሎች አጋጣሚዋች ደግሞ ቦታቸው ላይ ተገኝተውም የኢትዮጵያ ቡና ተጨዋቾች ተጠጋግተው በሚያደርጓቸው ቅብብሎች በቀለሉ እየታለፉ ነበር፡፡
በ4-1-4-1 አጨዋወት ወቅት የቡድኑ ብቸኛ የፊት አጥቂ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት እሙን ነው፡፡ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ቡናው ያቡን ዊልያም የትላንትናው እንቅስቃሴ እጅጉን የሚደነቅ ነበር፡፡ ተጨዋቹ ካስቆጠራቸው ጎሎች በተጨማሪም ከላይ ለተጠቀሰው በኤሌክትሪክ ተከላካዮች መካከል ይፈጠር ለነበረው ክፍተት ወደ ክንፍ በመውጣት እና እንዲሁም ሁለቱን የመሀል ተከላካዮች በእንቅስቃሴ በመረበሽ የራሱን ሚና ተወቷል፡፡
በኤሌክትሪክ በኩል በአብዛኛው የቡድኑ የማጥቃት አካሄድ ፒተርን የተከተለ ነበር፡፡ በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች ተጨዋቹ በቀኝ አማካይነት ሚና ላይ ሳለ የቡድኑ የማጥቃት አቅጣጫ ወደቀኝ ያመዘነ ነበር፡፡ ጐሏም የተገኘችው በዚሁ አኳኋን ነበር፡፡ ከ15ኛው ደቂቃ በኋላ ፒተር ወደፊት አጥቂነት ሲመጣ በምትኩ ፍፁም ወደ መስመር ወቷል፡፡ ከዚህም በኋላ በተለይ በመጀመሪያው አጋማቭ አደገኛ የነበሩት የኤሌክትሪክ ኳሶች በቀጥታ ወደፒተር የሚላኩ ወይም በመልሶ ማጥቃት በፍፁም በኩል ማለትም በቀኝ በኩል የሚነሱ ነበሩ፡፡ በተጨማሪም ፒተር ወደ ግራ ክንፍ ወጣ በማለት ኳሶችን ከበኃይሉና ብሩክ ጋር በመቀበል ወደ መህል ይዞ ለመግባት እንዲሁም የተሻለ ፍጥነት ለነበረው ፍፁም ለማሳለፍም ሙከራ አድርጓል፡፡ ቡድኑ እንደተጋጣሚው የበዛ ባይሆንም የጐል እድሎችን ግን መፍጠር ችሎ ነበር፡፡ እዚህ ላይ ግን የኢትዮጵያ ቡና አማካዮች በፍጥነት ወደኋላ ተመልሶ ክፍተቶችን በመዝጋት ተገቢውን የመከላከል ቅርፅ ለመያዝ ያደርጉ የነበሩት ጥረትና እንዲሁም የተጋጣሚያቸው ፈጣሪ ተጨዋቾች ኳስን በተረጋጋ ሁኔታ ይዘው በተመቻቸ መንገድ ለአጥቂዎች እንዳያደርሱ በዙሪያቸው ጫና ለማሳደር ያሳዩት እንቅስቃሴ የሚደነቅ ነው፡፡
የኤሌክትሪክ ቡድን የማጥቃት እንቅስቃሴ በመጨረሻዎቹ 30 ደቂቃዎች በርትቶ ታይቷል፡፡ በተለይም ያቡን ዉሊየም በ53ኛው ደቂቃ ካስቆጠራት ጐል በኋላ ኤሌክትሪኮች ተጭነው ተጫውተዋል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ መጀመሪያ ላይ በሀይሉ ተሻገርን በዘላለም አሰግድ (ቁ.11) ከቀየሩ በኋላ የነበራቸውን ሁለት የቅያሬ ዕድል የተጠቀሙበት ግቡ ከተቆጠረባቸው በኋላ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ብሩክ አያሌውን በአብዱልከሪም ሱልጣን (ቁ.17) እንዲሁም አጥቂውን ፍፁም ገ/ማሪያምን በማናዬ ፋንቱ (ቁ.23) በመቀየር አስገብተዋል፡፡ ከነዚህ ቅያሬዎች በኋላም የቡድኑ አጨዋወት ወደ 4-3-3 የቀረበ ነበር፡፡
(ምስል 3ን ይመልከቱ)
በነዚህ ኤሌክትሪክ በተሻለ መልኩ ጫና በፈጠረባቸው ደቂቃዎች ከቡድኑ ተከላካዮች ወደ አጥቂዎቹ በቀጥታ ይላኩ የነበሩ ኳሶች ቡድኑ የግብ አጋጣሚ መፍጠሪያ ዋነኛ መንገዶች ነበሩ፡፡ በነዚህ አጋጣሚዎች በቁመቱ ዘለግ ያለው አዲስ ነጋሽ ወደፊት በመጠጋትና ከፒተር ጋር በመሆን የአየር ላይ ኳሶቹ የማውረዱን ኃላፊነት ሲጋራው ተስተውሏል፡፡ ኢትዮጵያ ቡናዎች በበኩላቸው ባገኙት አጋጣሚዎች ወደተጋጣሚያቸው ጐል ክልል በመድረስ የግብ እድሎችን በብዛት ለመፍጠር ሙከራ አድርገው ነበር፡፡ በዚህም ሂደት ጥላሁን ወልዴን (ቁ.11) በዮሴፍ ደሙዬ፣ አማኑኤል ዮሐንስን (ቁ.24) በኤልያስ ማሞ ቀይረው በመግባት በተለይም በግራ በኩል የነበረውን የቡድኑን እንቅስቃሴ አጠናክረዋል፡፡ እነዚህ ቅያሪዎች ከኤሌክትሪኮች ቀኝ መስመር ይነሱ የነበሩ ረጃጅም ኳሶችን ለማቆረጥና በዛው መስመር ላይ የሚገኙ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ለመጠቀም የታሰቡ ይመስሉ ነበር፡፡ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ቡና አማካዮች የኤሌክትሪክ ተጨዋቾች ይፈጥሩ የነበሩትን የማጥቃት ጫና በሚያቋርጡበት ቅፅበት በፍጥነት ወደማጥቃት በመግባት እና የተሻለ ከመከላከል ወደ ማጥቃት የሚደረግ ሽግግርን በማሳየት ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ደርሰው ሙከራዎችን ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ በተጨማሪም በመከላከል ጊዜ ወደኋላ በመሳብ ለተጋጣሚያቸው ክፍተት ላለመስጠት ያረጉት ሙከራ ተሳክቶላቸው ኤሌክትሪኮች ኳስን ከኋላ መስርተው ከመምጣት ይልቅ በቀጥታ ከተከላካይ መስመራቸው ረጃጅም ኳሶችን ወደፊት በመጣል ላይ እንዲገደቡ አድርገዋቸዋል፡፡ በዚህም መሰረት ምንም እንኳን ያገኟቸውን የጎል እድሎች መጠቀም ባይችሉም ውጤታቸውን አስጠብቀው ለመውጣት ግን ችለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በቀጣይ ሲካሄድ ኤሌክትሪክ ሰኞ 11፡30 ላይ ደደቢትን ሲገጥም፣ ኢትዮጵያ ቡና በመጪው ሰኞ በጉጉት በሚጠበቀው የሸገር ደርቢ ቅ/ጊዮርጊስን ያስተናግዳል፡፡