የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከስፖርት ኮሚሽን ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የክለቦች የፋይናስ አቅም ላይ ያተኮረ የምክክር ጉባዔ ጥሪ የተደረገላቸው ክለቦች በሙሉ መገኘት ባለመቻላቸው ምክንያት ሳይካሄድ ቀርቷል።
የክለቦችን አቅም እየተፈታተነ እስከ መፍረስ እያደረሳቸው የሚገኘውን ጥናትን መሠረት ያላደረገው የፋይናስ ወጪን ለማጤን የታሰበው የምክክር ጉባዔ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከስፖርት ኮሚሽን ጋር በመተባበር ነበር ያዘጋጀው። በስፖርት ኮሚሽን መሰብሰቢያ አዳራሽ ዛሬ ጠዋት ሊካሄድ በታሰበው በዚህ የውይይት መድረክ ጥሪ ከተደረገላቸው ከ33 ክለቦች መካከል ኢትዮጵያ ቡና፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና አዳማ ከተማ ከፕሪምየር ሊጉ ሲገኙ የከፍተኛ ሊግ ዘጠኝ ክለቦች በአጠቃላይ 13 ክለቦች ተገኝተውበታል።
ለሚዲያ ዝግ በነበረው በዚህ የውይይት መድረክ ከመበተኑ በፊት ከተሳታፊዎች መካከል የአንድ ክለብ ኃላፊ ” የክለቦችን የፋይናስ አቅም ችግር ብቻ ሳይሆን የውድድሩ ፎርማት ላይም በሚገባ ጥናት ተደርጎበት ለቀጣይ ቀጠሮ ይቅረብ” ሲሉ አፅንኦት ሰጥተው መናገራቸውን ሰምተናል።
በዚህም መሠረት ሁሉም ክለቦች መገኘት ባለመቻላቸው የታሰበው የምክክር ጉባዔ ሳይሳካ ለሌላ ቀን ቀጠሮ በመያዝ ተጠናቋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡