ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ባህር ዳር ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ

በሰንጠረዡ አጋማሽ ላይ የሚገኙት የባህር ዳር እና ድሬዳዋን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

በመካከላቸው የሁለት ነጥቦች ልዩነት ብቻ ያለው ባህርዳር ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ 8 እና 9ኛ ደረጃ ላይ ሆነው ነገ 09፡00 ላይ በባህር ዳር ኢንተርናሽናል ስታድየም ይገናኛሉ። በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎቻቸው ድል ያልቀናቸው ባህር ዳሮች ወደ ዋንጫ ፉክክሩ የመመለስ ሁኔታቸው የጠበበ ቢሆንም ወደ አሸናፊነት ከተመለሱ እስከ ስድስተኛነት ከፍ የማለት ዕድሉ ይኖራቸዋል። ከተጋጣሚያቸው በተሻለ ጥሩ ጊዜን እያሳለፉ የሚገኘት ድሬዳዋ ከተማዎች በበኩላቸው በስተመጨረሻ ካደረጓቸው አምስት ጨዋታዎች አራቱን በድል በመወጣት ከወራጅ ቀጠናው ርቀው መቀመጥ ሲችሉ መሀል ላይ ለመርጋት የሚያግዛቸውን ነጥብ ከባህር ዳር ለማግኘት ወደ ሜዳ ይገባሉ። 

ባህር ዳር ከተማ በነገው ጨዋታ አምስት ተጨዋቾችን በጉዳት እና በቅጣት አያሰልፋም። በዚህም ሣላምላክ ተገኝ በኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ በቀይ ካርድ በመውጣቱ እና ወንድሜነህ ደረጄ በአምስተኛ  ቢጫ ካርድ በቅጣት እንዲሁም ተስፋሁን ሸጋው፣ ፍቅረሚካኤል አለሙ እና ዳንኤል ኃይሉን በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ ሆነዋል። ከዚህ በተጨማሪ የቡድኑ የተከላካይ መስመር ተጫዋች አቤል ውዱ ሰሞኑን መጠነኛ ጉዳት አስተናግዶ እንደነበረ ቢሰማም ለነገው ጨዋታ ዝግጁ እንደሆነ ተረጋግጧል። በመከላከያው ጨዋታ የኳስ ቁጥጥሩን ለተጋጣሚያቸው መተውን ምርጫቸው ያደረጉ ይመስሉ የነበሩት የጣና ሞገዶቹ ነገ በተሻለ ኳስ ይዘው ለመጫወት እንደሚሞክሩ ይጠበቃል። ሆኖም ተጋጣሚያቸው ከሚኖረው ቅርፅ አንፃር መሀል ለመሀል ከማጥቃት ይልቅ የመስመር አጥቂዎቻቸውን መጠቀም ምርጫቸው ሊያደርጉ ይችላሉ። በዚህ ሂደት ውስጥም ቡድኑ ጥሩ ባይሆንም በግሉ መልካም እንቅስቃሴ ሲያደርግ የሚታየው ወሰኑ ዓሊ አስተዋፅዖ ተጠባቂ ነው። 

ከውጤት ባለፈ በመጀመሪያ አሰላለፍ ምርጫም መረጋጋት እየታየበት የሚገኘው ድሬዳዋ ከተማ ከሜዳው እንደመውጣቱ ከባድ ፈተና እንደሚገጥመው ቢታመንም ያስመዘገባቸውን ድሎች ተክከትሎ የሚገኝበት በራስ የመተማመን ደረጃ እንደሚረዳው ይገመታል። ወላይታ ድቻን ከኋላ በመነሳት የረቱት ብርቱካናማዎቹ የኢታሙና ኬይሙኒ እና ከአራቱ ጨዋታዎች በሦስቱ ግብ የቀናው ረመዳን ናስር ብቃት መልካም መሆንም ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል። በነገው ጨዋታም ወደ ኋላ ቀረት ብለው በመከላከል በቀጥተኛ ኳሶች በመታገዝ ጥቃቶችን እንደሚሰነዝሩ ይገመታል። ድሬዎች ፍቃዱ ደነቀ እና ራምኬል ሎክ ከጉዳት ያልተመለሱላቸው ሲሆን ኤልያስ ማሞንም ሳይዙ ነው ወደ ሰሜን ያቀኑት። በአንፃሩ የመስመር ተከላካዩ ያሬድ ዘውድነህ  ከጉዳት መልስ ለጨዋታው ብቁ መሆኑ ተሰምቷል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– በሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙበት የዘጠነኛው ሳምንት ጨዋታ በድሬዳዋ ከተማ 2-1 አሸናፊነት የተጠናቀቀ ነበር። 

– በሜዳቸው በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ያለሽንፈት እየተጓዙ የሚገኙት ባህር ዳሮች ስድስት የድል እና አምስት የአቻ ውጤቶችን አስመዝግበዋል።   

– ከ11 የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች ሁለቴ ድል የቀናቸው ድሬዳዋ ከተማዎች አምስት ጊዜ አንድ ነጥብ ይዘው ሲመለሱ አራቴ ደግሞ ሽንፈት ገጥሟቸዋል።

ዳኛ

– ጨዋታውን ለመምራት የተመደበው ብርሀኑ መኩሪያ እስካሁን በዳኘባቸው ስድስት ጨዋታዎች 21 የማስጠንቀቂያ ካርዶችን ሲመዝ ሁለት የፍፁም ቅጣት ምት እና አንድ የሁለተኛ ቢጫ ካርድ ውሳኔዎችን አሳልፏል። አርቢትሩ ለመጨረሻ ጊዜ ድሬዳዋ እና ደደቢትን ያገናኘው ጨዋታ ላይ የዳኘ ሲሆን ባህር ዳር ከአዳማ እንዲሁም ድሬዳዋ ከፋሲል ያደረጓቸው ጨዋታዎችንም መርቷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ባህርዳር ከተማ (4-3-3)

ሀሪሰን ሔሱ

ግርማ ዲሳሳ – አሌክስ አሙዙ – አቤል ውዱ – አስናቀ ሞገስ

ዳግማዊ አባይ – ደረጄ መንግስቱ – ኤልያስ አህመድ

ፍቃዱ ወርቁ – ጃኮ አራፋት – ወሰኑ ዓሊ

ድሬዳዋ (4-2-3-1)

ሳምሶን አሰፋ

ገናናው ረጋሳ – አንተነህ ተስፋዬ – በረከት ሳሙኤል – ዘነበ ከበደ

ፍሬድ ሙሸንዲ – ሚኪያስ ግርማ 

ኤርሚያስ ኃይሉ – ምንያህል ተሾመ – ረመዳን ናስር 

ኢታሙና ኬይሙኒ