ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ፋሲል ከነማ ከ ወልዋሎ ዓ/ዩ

ከሊጉ መሪ በአምስት ነጥብ ርቀው በሁለተኛነት የሚገኙት ፋሲል ከነማዎች ወልዋሎን የሚያስተናግዱበት ጨዋታ የዛሬው ዳሰሳችን የመጨረሻ ትኩረት ነው።

ከሊጉ መሪ የነበራቸው የነጥብ ልዩነት በማጥበብ የዋንጫ ፉክክሩን ይበልጥ አጓጊ ያደረጉት አፄዎቹ የነገው ወሳኝ ጨዋታ ማሸነፍ ይበልጥ መቐለ ላይ ጫና መፍጠር ስለሚያስችላቸው ይሄን ጨዋታ ከማሸነፍ ውጪ የተሻለ አማራጭ የላቸውም።

በአጥቂ ክፍል ተጫዋች እጦት ምክንያት እንደሚወስዱት ብልጫ እና እንደሚፈጥሩት የግብ ዕድል ግብ ለማስቆጠር ተቸግረው የቆዩት አፄዎቹ ከሁለተኛው ዙር መጀመር አንስቶ በአማካዮቹ እና የቦታ ለውጥ ያደረገው ሙጂብ ቃሲም አማካኝነት ግብ ማስቆጠር መጀመራቸው ለቡድኑ ጥሩ ዜና ነው። በኳስ ቁጥጥር ላይ ተመስርተው ለመጫወት የሚመርጡት ፋሲሎች በዚህ ጨዋታ በኳስ አመሰራረት ሂደታቸው ውስጥ ወሳኝ ሚና ያለው ሀብታሙ ተከስተን በጉዳት ማጣታቸው በአጨዋወታቸው ላይ መጠነኛ ለውጥ ያደርጋሉ ተብሎ ቢጠበቅም በመሰረታዊነት ቡድኑ ከሚታወቅበት አጨዋወትት የራቀ አጨዋወት ይኖረዋል ተብሎ ግን አይገመትም። አፄዎቹ በዚህ ጨዋታ መጣባቸው ሙሉ ፣ ሰለሞን ሀብቴ ፣ ፀጋአብ ዮሴፍ እና ሀብታሙ ተከሰተን በጉዳት አያገኙም።

ከጥሩ መነቃቃት በኃላ ተከታታይ ነጥብ ጥለው ወደ መሪዎቹ የመጠጋት ዕድላቸው ያጠበቡት ቢጫ ለባሾቹ በነገው ጨዋታ ከባለፉት ጨዋታዎች የተለየ አቀራረብ ይዘው ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል። ባለፉት ጨዋታዎች ከሚታወቁበት ጠጣር እና ጥንቃቄ የተሞላበት አጨዋወት ለየት ባለ አኳዃን ቀርበው የተሻለ የተንቀሳቀሱት አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ በነገው የሜዳቸው ውጪ ጨዋታ እንደባለፉት ጨዋታዎች አጥቅተው እና ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል ተጠግተው ይጫወታሉ ተብሎ አይጠበቅም።

አማኑኤል ጎበና በጉዳት ካጡ በኃላ ለአጨዋወቱ የሚሆን ሁነኛ ተተኪ አማካይ  ማግኘት ያልቻሉት ወልዋሎዎች በነገ ጨዋታም አማኑኤል ጎበናን በጉዳት ስለማያገኙ የመስመር ተጫዋቹ ዓብዱራሕማን ፉሴይኒን በአስር ቁጥር ሚና ላይ ያሰልፋሉ ተብሎ ይገመታል። ከዚህ በተጨማሪ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ከተለመደው የመስመር አጨዋወት ይልቅ ብቸኛው አጥቂ ሬችሞንድ ኦዶንጎን ዒላማ ባደረጉ ረጃጅም ኳሶች ለማጥቃት ጥረት ሲያደርጉ የታዩት ቢጫ ለባሾቹ በዚህ ጨዋታም ይህንኑ አካሄድ እንደሚመርጡ ይታሰባል። ወልዋሎዎች በጨዋታው ሳምሶን ተካ እና አማኑኤል ጎበናን በጉዳት የማያሰልፉ ሲሆን በስነ-ምግባር ችግር ከቡድኑ ጋር ልምምድ ያልሰራው ክሪስቶፈር ችዞባም ወደ ጎንደር አልተጓዘም።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ወልዋሎ ዓ/ዩ ወደ ሊጉ በገባበት ካሳለፍነው የውድድር ዓመት ጀምሮ ከተገናኙባቸው ሦስት ጨዋታዎች መካከል በወልዋሎ ሜዳ የተደረጉት ጨዋታዎች 2-2 እና 0-0 ሲጠናቀቁ አዲስ አበባ ላይ የተደረገው ጨዋታ ደግሞ በፋሲል 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። 

– ፋሲል ከነማ ሜዳው ላይ ያለሽንፈት የዘለቀባቸውን 11 ጨዋታዎች አድርጎ ሰባት ድሎች እና አራት የአቻ ውጤቶች አስመዝግቧል።   

– በዘጠኝ አጋጣሚዎች ከትግራይ ስታድየም ውጪ የተጫወቱት ወልዋሎዎች አራት ጊዜ በሽንፈት ሲመለሱ ሁለት የአቻ እና ሦስት የድል ውጤቶችን ማስመዝገብ ችለዋል።

ዳኛ

– ጨዋታውን ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ ይመራዋል። አርቢትሩ በእስካሁኖቹ 11 ጨዋታዎች 54 የማስጠንቀቂያ ካርዶችን ሲያሳይ አንድ ጊዜ በቀጥታ ቀይ ካርድ ሦስት ጊዜ ደግሞ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ተጫዋቾችን ለሜዳ አሰናብቷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ፋሲል ከነማ (3-4-3)

ጀማል ጣሰው

 ከድር ኩሊባሊ – ያሬድ ባየህ – አይናለም ኃይለ

ኤፍሬም አለሙ – በዛብህ መለዮ – ሱራፌል ዳኛቸው –አምሳሉ ጥላሁን 

ኢዙ አዙካ – ሙጂብ ቃሲም – ሽመክት ጉግሳ

ወልዋሎ ዓ/ዩ (4-2-3-1)

ዓብዱልአዚዝ ኬታ

ዳንኤል አድሀኖም – በረከት አማረ – ደስታ ደሙ – ብርሃኑ ቦጋለ

ብርሃኑ አሻሞ – አፈወርቅ ኃይሉ 

ፕሪንስ ሰቨሪንሆ – ዓብዱራሕማን ፉሴይኒ – ኤፍሬም አሻሞ 

ሬችሞንድ አዶንጎ