የ24ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ዛሬ ሲቀጥሉ በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም ድሬዳዋ ከተማን ያስተናገደው ባህር ዳር ከተማ 2-1 አሸንፏል።
ባለሜዳዎቹ ባህር ዳር ከተማዎች በ23ኛ ሳምንት ወደ አዲስ አበባ አቅንተው አንድ ለምንም ከተሸነፉበት የመከላከያ ጨዋታ ሶስት ለውጦችን አድርገዋል። በዚህም ወንድሜነህ ደረጄ፣ ማራኪ ወርቁ እና ፍቃዱ ወርቁን በአቤል ውዱ፣ ዜናው ፈረደ እና ጃኮ አራፋት ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል። ተጋባዦቹ ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ ከድል ከተመለሱበት የወላይታ ዲቻ ጨዋታ ሁለት ለውጦችን አድርገዋል። በዚህም ኤሊያስ ማሞን እና ኤርሚያስ ኃይሉን በምንያህል ተሾመ እና ሳሙኤል ዩሃንስ በመተካት ለጨዋታው ቀርበዋል።
ከጨዋታው መጀመር በፊት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ህዝብ መዝሙር የተዘመረ ሲሆን የባህር ዳር ከተማ ደጋፊዎች ማኅበር ለቀድሞ ተጨዋቻቸው ሚኪያስ ግርማ እና ለድሬዳዋ ከተማ ክለብ ደጋፊዎች ስጦታ አበርክተዋል። ቀዝቀዝ ያለ አጀማመር የነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በተለይ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ቀልብን የሚገዛ አልነበረም። በ8ኛው ደቂቃ የመጀመሪያ ሙከራ ያስተናገደው ጨዋታው ተጋባዦቹ ድሬዳዋዎች ባገኙት የመዓዘን ምት ግብ ለማስተናገድ ተቃርቦ ነበረ። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ አስናቀ ሞገስ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ወሰኑ ዓሊ ከተከላካዮች ጀርባ በመገኘት ኳስ እና መረብን አገናኝቶ ባለሜዳዎቹ መሪ ሆነዋል።
ገና በጊዜ ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የተሻለ የተንቀሳቀሱት ቡርትካናማዎቹ በተለይ በቆሙ ኳሶች ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል። በዚህም በ14ኛው ደቂቃ አሌክስ አሙዙ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ ያገኙትን የቅጣት ምት ወደ ግብ ለመቀየር ጥረዋል። ከደቂቃ በኋላ በቀጥተኛ አጨዋወት ድጋሜ ወደ ባህር ዳሮች ግብ የደረሱት ተጋባዦቹ በምንያህል አማካኝነት ጥሩ ሙከራ አድርገው መክኖባቸዋል። ለጎሉ ወዲያው ምላሽ ለመስጠት ያሰቡ የሚመስሉት ድሬዎች በ19ኛው ደቂቃም ጥሩ እድል አግኝተው ነበረ። ኢታሙና ኬይሙኒ ከመሃል ሜዳ ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ ያገናኘውን ኳስ አግኝቶ ሊጠቀም ሲል ግዙፉ የባህር ዳር የመሃል ተከላካይ መስመር ተጨዋቹ አቤል ውዱ በፍጥነት በመሮጥ ተጨዋቹ ኳሷን እንዳይጠቀም አድርጎታል።
በቆሙ ኳሶች ጫና ማሳደራቸውን የቀጠሉት ድሬዳዋዎች በ24ኛው ደቂቃ ዘነበ ከበደ በመታው የቅጣት ምት አቻ ለመሆን ጥረዋል። በሚታወቁበት 4-3-3 አሰላለፍ ወደ ሜዳ የገቡት ባህር ዳሮች ግብ ካስቆጠሩ በኋላ በአንፃራዊነት ተቀዛቅዘው ታይተዋል። ነገር ግን በአንድ አንድ አጋጣሚዎች ፈጣኖቹን የመስመር አጥቂዎቻቸውን በመጠቀም ጥቃቶችን ሲሰነዝሩ ተስተውሏል። በ25ኛው ደቂቃም በፈጣን የመስመር ላይ ሽግግር ወደ ድሬዎች የግብ ክልል በዜናው አማካኝነት ደርሰው ጥሩ ሙከራ አድርገው ነበረ። በአመዛኙ ወደ መሃል ሜዳ አጥበው ሲጫወቱ የነበሩት ድሬዳዋዎች ሁለቱ የመስመር ተከላካዮቻቸ ነፃነት በመስጠት የጎል ምንጮችን ከየአቅጣጫው ሲሞክሩ ተስተውሏል። በ32ኛው ደቂቃም ሳሙኤል ዩሃንስ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ኢታሙና ኬይሙኒ ወደ ጎል ለመቀየር ጥሮ መክኖበታል። ደቂቃዎች እየሄዱ በመጡ ቁጥር ሙሉ ለሙሉ የተበለጡት ባለሜዳዎቹ ከተጋጣሚያቸው እየተሰነዘረ የነበረን ጫና መቋቋም አቅቷቸው ወደ ኋላ አፈግፍገዋል። በተለይ ደግሞ የድሬዳዋዎችን የቆመ ኳስ ለማስቆም ሲቸገሩ ታይቷል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሶስት ደቂቃ ሲቀረው ዳግም ወደ ባለሜዳዎች የግብ ክልል የደረሱት የአሰልጣኝ ስምዖን ተጨዋቾች አጋጣሚውን ወደ ጎልነት መቀየር ተስኗቸው የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።
ከእረፍት መልስ በተወሰነ መልኩ ተሟሙቆ የጀመረው ጨዋታው ገና በጅማሮ ግብ ለማስተናገድ እጅጉን ተቃርቦ ነበረ። ሃሪስተን ሄሱ ከግብ ክልሉ ወቶ የመታው ኳስ ብዙም ሳይርቅ ያገኘው ምንያህል ተሾመ ሃሪሰን ወደ ቦታው ከመመለሱ በፊት ግብ ለማስቆጠር ወደ ግብ ኳሱን መቶ ግብ ለማስቆጠር ቢጥርም አስናቀ ሞገስ ቦታው ላይ ደርሶ ኳሱን ከግብነት በግምባሩ ከልክሎታል። በእንቅስቃሴ ደረጃ በድሬደዋዎች ቢበለጡም ወደ ጎል በተደጋጋሚ ሲደርሱ የነበሩት ባህር ዳሮች በ53ኛው ደቂቃ ሁለተኛ ግብ ለማስቆጠር ሞክረዋል። ዜናው ፈረደ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ከወሰኑ ዓሊ የተቀበለውን ኳስ ወደ ግብ ከርቀት መቶ ወደ ውጪ ወጥቶበታል።
በዚህኛውም የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የቆሙ ኳሶችን እንደ ዋነኛ የግብ ማስቆጠሪያ አማራጭ አስበው ሲንቀሳቀሱ የታዩት ድሬዳዋዎች ቶሎ የአቻነት ግብ አስቆጥረው ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት አድርገዋል። በዚህም በ61ኛው ደቂቃ ዘነበ ከርቀት አክርሮ ወደ ግብ በመታው የቅጣት ምት አቻ ለመሆን ተቃርበው ነበረ። በአንፃራዊነት ወደ ግብ ክልላቸው አፈግፍገው ሲጫወቱ የነበሩት ባህር ዳሮች በ72ኛው ደቂቃ በቀጥተኛ አጨዋወት ግብ አስቆጥረው መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ አድርገዋል። በዚህ ደቂቃ የተገኘውን የቅጣት ምት አስናቀ ሞገስ ሲያሻማው የአማካኝ ስፍራ ተጨዋቹ ዳግማዊ ሙሉጌታ በጥሩ ሁኔታ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል።
ሁለተኛ ጎል ሳይታሰብ የተቆጠረባቸው ድሬዳዋዎች በቀሪው ደቂቃ በሙሉ ሃይላቸው አጥቅተው ተጫውተዋል። በዚህም ሁለተኛው ጎል ከተቆጠረባቸው ከሶስት ደቂቃ በኋላ ምንያህል ተሾመ የግል ጥረቱ ተጠቅሞ በሞከረው ሙከራ ወደ ግብ ደርሰው ነበረ። በተመሳሳይ በ83ኛው ደቂቃም ወደ ባህር ዳሮች የግብ ክልል በቁጥር በዝተው ያመሩት ድሬዳዋዎች ቀይረው ወደ ሜዳ ባስገቡት ኤርሚያስ ኃይሉ አማካኝነት የማስተዛዘኛ ጎል አስቆጥረዋል። በተለያዩ ምክንያቶች በዳኛው ፊሽካ አማካኝነት ሲቆራረጥ የነበረው የሁለተኛው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃ ጨዋታ ግልፅ የግብ ማግባት ሙከራ ሳይስተናገድ በባህር ዳር አሸናፊነት ተጠናቋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡