ስትዋርት ሀል ከፈረሰኞቹ ጋር ሊለያዩ?

እንግሊዛዊው የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ከክለቡ ጋር የመለያያቸው ጊዜ ተቃርቧል።

ፖርቱጋላዊው አሰልጣኝ ቫስ ፒንቶን በመተካት ያለፉትን ስምንት ወራት የቅዱስ ጊዮርጊስ አለቃ ሆነው የቆዩት እንግሊዛዊው አሰልጣኝ ስትዋርት ሀል ከፈረሰኞቹ ጋር የመለያየታቸው ነገር እርግጥ ሊሆን ነው። አሰልጣኙ ከሰዓታት በፊት በ24ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ ግብር በሜዳቸው ከደቡብ ፖሊስ ጋር ያለ ጎል ነጥብ ተጋርተው ከወጡ በኃላ የሰጡት አስተያየትም ይህንን የሚጠቁም ሆኗል።

ስትዋርት ሀል ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ በሰጡት አስተያየት ለውጤቱ ኃላፊነቱን እንደሚወስዱ ገልፀው በልምምድ ሜዳ ላይ የሰሯቸውን ስራዎች ከተጫዋቾቻቸው በራስ መተማመን መውረድ እና የደጋፊን ጫና አለመቋቋም ምክንያት ሜዳ ላይ ማሳየት አለመቻላቸው እንዳሳዘናቸው መናገራቸው ቡድኑን ከዚህ በላይ በማሻሻሉ በኩል ተስፋ የቆረጡ አስመስሏቸዋል። አሰልጣኙ ሁሉንም የቡድኑን ተጫዋቾች በተለያየ ጊዜ ቢሞክሩም ለውጥ አለማምጣቱን ጠቅሰው በመጨረሻ “ክለቡን ወደ ፊት ለማራመድ እና ለክለቡ ጥቅም ስል ነገ የራሴን ውሳኔ እወስናለው ” ብለው መናገራቸውን ተከትሎም የመልቀቂያ ደብዳቤ በማስገባት ከፈረሰኞቹ ጋር ሊለያዩ እንደሚችሉ ተገምቷል።

ሶከር ኢትዮዽያ ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ምንጮቿ እንዳገኘችው መረጃ ከሆነ አሰልጣኝ ስትዋርት ሀል በፈረሰኞቹ ቤት የመቆየታቸው ጉዳይ ያከተመለት ይመስላል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡