ፕሪሚየር ሊግ ፡ አወዛጋቢ እና አነጋጋሪ ክስተቶች ባስተናገደው 5ኛ ሳምንት አዳማ ከነማ መሪነቱን አስጠብቋል

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 5ኛ ሳምንት ጨዋታዎች አዳማ ከነማ በአሸናፊነቱ ሲቀጥል አስገራሚ ክስተቶች ፣ የቀይ ካርዶች ፣ ውዝግቦች እና ካለግብ የተጠናቀቁ ጨዋታዎች ተስተናግደውበታል፡፡

ወደ አርባምንጭ ያቀናው አዳማ ከነማ በድል ተመልሷል፡፡ ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት ሲያሟሙቅ ጉዳት ባጋጠመው ታፈሰ ተስፋዬ ምትክ የተጫወተው ሚካኤል ጆርጅ ከማእዘን ምት የተሸገረችውን ኳስ ተጠቅሞ በ50ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ግብ የአሸናፊ በቀለን ቡድን ለድል አብቅቶታል፡፡

በጨዋታው የመጀመርያ አጋማሽ አዳማ ከነማዎች የተሻለ መንቀሳቀስ ችለው የነበረ ሲሆን ያለቀላቸው የግብ እድሎችን መፍጠርም ችለዋል፡፡ በ2ኛው አጋማሽ ደግሞ አርባምንጭ ከነማ ተጭኖ በመጫወት ተደጋጋሚ የግብ እድሎችን መፍጠር ችለው ነበር፡፡

አዳማ ከነማ ድሉን  ተከትሎ ዛሬ የተሸነፈው ድቻ እና ነገ ጨዋታውን የሚያደርገውን ቅዱስ ጊዮርጊስ በ4 ነጥቦች ርቆ የሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ በ13 ነጥቦች መምራቱን ቀጥሏል፡፡

ወደ ይርጋለም የተጓዘው ወላይታ ድቻ በሲዳማ ቡና 1-0 ተሸንፎ ተከታታይ የማሸነፍ ጉዞው ተገትቷል፡፡ የሲዳማ ቡናን የድል ግብ በ53ኛው ደቂቃ በላኪ በሪለዱም ተቀይሮ የገባው አዲስ ግደይ በመጀመርያ ንክኪ ግብ አስቆጥሯል፡፡ ድቻ ከ3 ተከታታይ ጨዋታ ድል በኋላ ሽንፈት ሲገጥመው ሲዳማ ቡና ጥሩ ካልሆነ አጀማመር በኋላ ከ3 ጨዋታ 7 ነጥብ መሰብሰብ ችሏል፡፡

 

ተቀይሮ በገባበት ቅፅበት ግብ ያስቆጠረው የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ
ተቀይሮ በገባበት ቅፅበት ግብ ያስቆጠረው የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ

ዘንድሮ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ያደጉት ድሬዳዋ ከነማ እና ሀዲያ ሆሳእናን እርስ በእርስ ባገናኘው የድሬዳዋ ስታድየም ፍልሚያ ድሬዳዋ ከነማ 3-2 አሸንፏል፡፡

ሀዲያ ሆሳእናዎች በአበባየሁ ዮሃንስ የ8ኛ ደቂቃ እና በዱላ ሙላቱ የ33ኛ ደቂቃ ግቦች 2-0 ሲመሩ ቢቆዩም የፍቃዱ ወርቁ ሁለት ግቦች እና የፍቃዱ ታደሰ የማሸነፍያ ግብ ባለሜዳዎቹን ለድል አብቅቷቸዋል፡፡ የሆሳእናው ግብ ጠባቂ ጃክሰን ፊጣ የቀይ ካርድ እና የፍቃዱ ወርቁ ግብ ከጨዋታ ውጪ ነው በሚል ውዝግብ ተነስቶበታል፡፡ በጨዋታው መገባደጃ ላይ ከፍተኛ ውዝግብ የተከሰተ ሲሆን የእለቱ አርቢትርም ለሆሳእና ከነማው ሄኖክ አርፊጮ የቀይ ካርድ መዘዋል፡፡

ጎንደር ላይ ዳሽን ቢራ መከላከያን አስተናግዶ 0-0 አቻ ተለያይቷል፡፡ ጥሩ አጀማመር አድርጎ የነበረው ዳሽን ቢራ ሊጉ ተቀወርጦ በድጋሚ ከተጀመረ በኋላ ባደረጋቸው 3 ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው 9 ነጥብ ያሳካው 1 ብቻ ነው፡፡

ሀዋሳ ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ያስተናገደው ሀዋሳ ከነማ 0-0 አቻ ተለያይቷል፡፡ ከጨዋታ ይልቅ ሁለቱ ክለቦች ተቀራራቢ ማልያ ለብሰው ወደ ሜዳ መግባታቸው አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ ጨዋታው ከተጀመረ በኋላም የእለቱ ዳኛ ጨዋታው 5 ደቂቃ እንደተደረገ አቋርጠው ንግድ ባንክ ዋናውን የወይን ጠጅ ማልያ እንዲለብስ አስደርገዋል፡፡ ይህን ጨዋታ የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ተከታትለውታል፡፡

አዲስ አበባ ስታድየም ላይ በተደረገው የእለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ደደቢት ከ ኤሌክትሪክ 2-2 አቻ ተለያይተዋል፡፡ ጨዋታው በተጀመረ በመጀመርያው ደቂቃ ሳሚ ሳኑሚ ደደቢትን ቀዳሚ ሲያደርግ ዘንድሮ ክለቡን የተቀላቀለው ፍፁም ገብረማርያም በ37ኛው ደቂቃ ኤሌክትሪክን አቻ አድርጓል፡፡ ሳሚ ሳኑሚ በድጋሚ በ49ኛው ደቂቃ ደደቢትን መሪ ያደረገ ሲሆን ግቧ ከጨዋታ ውጪ ናት በሚል የኤሌክትሪክ ተጫዋቾች ከረዳት ዳኛው ጋር ጭቅጭቅ ሲፈጥሩ ተስተውሏል፡፡ በ81ኛው ደቂቃ በብሩክ አየለ ተቀይሮ የገባው ሀብታሙ መንገሻ ኤሌክትሪክን አቻ እድርጓል፡፡ ከግቧ በኋላ ኤሌክትሪኮች ጫና በመፍጠር ለግብ የቀረቡ ኳሶች የሞከሩ ሲሆን ማናዬ ፋንቱ ያስቆጠረው ግብ ከጨዋታ ውጪ ተብሎ መሻሩ እና በደደቢት የግብ ክልል በፍጹም ገብረማርያም ላይ የተሰራው ጥፋት የፍፁም ቅጣት ምት ያሰጣል በሚል የኤሌክትሪክ ተጫዋቾች ዳኛው ላይ ቅሬታ አሰምተዋል፡፡

የሊጉ 5ኛ ሳምንት ቀሪ አንድ ጨዋታ ነገ ሲደረግ በሃገሪቱ ታላቅ ደርቢ ኢትዮጵያ ቡና ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ 11፡00 ላይ ይፋለማሉ፡፡

ሊጉን አዳማ ከነማ በ13 ነጥቦች ሲመራ የደደቢቱ ሳሚ ሳኑሚ በ5 ግቦች የከፍተኛ ግብ አግቢነቱን ይመራል፡፡

ያጋሩ