ከ24ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች መካከል በጅማ ስታድየም የተከናወነው የጅማ አባ ጅፋር እና ሀዋሳ ከተማ ጨዋታ በ1-1 ውጤት ተጠናቋል።
ባለሜዳዎቹ ባሳለፍነው ሳምንት ከወልዋሎ ጋር አቻ ከተለያየው ስብስብ ውስጥ ሁለት ለውጦችን አድርገዋል። በዚህ መሰረትም መላኩ ወልዴን በከድር ኸይረዲን ብሩክ ገብረአብን በመስዑድ መሀመድ በመለወጥ በ4-3-3 አሰላለፍ ጨዋታውን ጀምረዋል። በተመሳሳይ በሐዋሳ በኩል በተደረጉ ሁለት ቅያሪዎች በሲዳማ ቡና ሽንፈት ካስተናገደው ስብስብ ውስጥ አክሊሉ ተፈራን በያኦ ኦሊቨር ሄኖክ ደልቢን ደግሞ በደስታ ዮሐንስ ለውጠው በ3-5-2 አሰላለፍ ወደ ሜዳ ገብተዋል። ዋና ዳኛ አማኑኤል ኃይለስላሴ እና ረዳቶቻቸው በጥሩ ብቃት መርተው ያጠናቀቁት ይህ ጨዋታ ከመጀመሩ አስቀድሞ በድገተኛ አደጋ ከዚህ ዓለም በሞት ለተለየችው የጅማ አባ ጅፋር ደጋፊ የህሊና ፀሎት ተደርጓል።
በዝናብ ታጅቦ የጀመረው የመጀመርያ አጋማሽ ሀያ ደቂቃዎች መሀል ሜዳ ላይ የተገደበ እንደ አየር ንብረቱ ሁሉ ቀዝቃዛ ጨዋታ የታየበት ነበር። ከዝናቡ ማባራት በኃላ በሁለቱም ቡድኖች ላይ መነቃቃት ቢታይም ወደፊት በመሄድ እና በተጋጣሚ ላይ ጫና በመፍጠር ረገድ ሐዋሳዎች የተሻሉ ነበሩ። በመስመሮች በኩል ለመጫወት ያሰቡ የሚመስሉት ጅማዎች በአመዛኙ በቀኝ መስመር በኩል አመዝነው በዐወት ገ/ሚካኤል በሚነሱ ተሻጋሪ ኳሶች ዕድሎችን ለመፍጠር በሚያደርጉት ጥረት ውጤታማ አልነበሩም፡፡ መሐል ሜዳ ላይ በቁጥር ብልጫ የነበራቸው ሐዋሳዎች የአጥቂውን እስራኤል እሸቱ እና የዳንኤል ደርቤን ፍጥነት በመጠቀም ከመሀል ከሚነሱ ተሻጋሪ ኳሶች ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል። በተለይ የጅማ ተከላካዮች የእስራኤል ፍጥነት ጨዋታውን አክብዶባቸዋል። በዚሁ መሰረት በ44ኛው ደቂቃ ከመሀል ሜዳ በግራ በኩል አስፍቶ ለቆመው እስራኤል የተሻገረውን ኳስ አጥቁው ፍጥነቱን በመጠቀም ወደ ሳጥን ውስጥ ሲያሻግር ዳንኤል ደርቤ በግንባሩ አስቆጥሮ ጨዋታው በሐዋሳዎች 1-0 መሪነት ወደ ዕረፍት አምርቷል።
ከዕረፍት መልስ የመጀመረያዎቹን አስራ አምስት ደቂቃዎች ሐዋሳዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው ቢጫወቱም በ58ኛው ደቂቃ ፍቅረየሱስ ከርቀት አክርሮ የመታውን ኳስ ዘርይሁን ታደለ እንደምንም ካወጣበት አጋጣሚ ውጪ ሌላ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። በጅማዎች በኩል አክሊሉን ዋለልኝን በብሩክ ገብረዓብ ቀይረው ካስገቡ በኃላ የጨዋታውን ፍጥነት መጨመር ቢችሉም ተረጋግተው ወደ ጨዋታው ምት የገቡት ከ60ኛው ደቂቃ በኃላ ነበር። በተደጋጋሚ በፈጠሩት ጫናም በ63ኛው ደቂቃ ላይ የተገኘውን የማዕዘን ምት መስዑድ መሀመድ አሻምቶት ኦኪኪ አፎላቢ በግንባሩ አስቆጥሮ ጅማዎችን አቻ ማድረግ ችሏል።
ከግቡ መቆጠር በኃላም ተጭነው የተጫወቱት ጅማዎች በተደጋጋሚ በቴዎድሮስ ታደሰ የፈጠሯቸውን የሚያስቆጩ ዕድሎች መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። በጨዋታው መገባደጃ ላይ ኦኪኪ አፎላቢ የአየር ላይ ኳስ በሚሻማበት ወቅት ወድቆ ምላሱ ወደላንቃው ውስጥ በመታጠፉ በቡድኑ ህክምና ባለሙያዎች ዕርዳታ ህይወቱ ሊተርፍ ችሏል። ትልቅ ምስጋና የሚገባው የሀዋሳው ግብ ጠባቂ ሶሆሆ ሜንሳህ አሰተውሎት የህክምና ጥሪ ባያደርግ ኖሮ ጨዋታው በአሳዛኝ ሁኔታ ይፈፀም ነበር፡፡ ኦኪኪ የህክምና ዕርዳታ ከተደረገለት በኃላ በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ለማረጋገጥ ችለናል፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡